Saturday, 22 November 2014 12:10

ከፈረሱ ቤቶች የታነፀው ዘመናዊ መኖሪያ ቤት

Written by 
Rate this item
(12 votes)

አሀዱ ኣባይነህ የኪነ-ህንፃ ባለሙያ ነው፡፡ በሙያው ለአስራ ስምንት አመታት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በ90ዎቹ ዓመታት በዝቅተኛ ወጪ የዛፍ ላይ መኖሪያ ቤት ሰርቶ ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ በአዲስ አበባ ከፈራረሱ ቤቶች ላይ ከተሰበሰቡ የተለያዩ ቁሳቁሶች እየሱስ በመባል በሚታወቀው አካባቢ እጅግ ውብ የሆነ ቤት ሰርቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ የኪነ-ህንፃ ባለሙያውን በሰራው ቤትና በአጠቃላይ በሙያው ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡


ከቤቶች ፍርስራሽ አዲስ ቤት የመገንባት ሃሳብ እንዴት መጣ?
ቤቱን የሰራሁለት ሰው ዶክተር ኤርሚያስ ሙሉጌታ ይባላል፡፡ ጥንታዊ ቁሶችን በጣም ይወዳል፡፡ እናም በከተማዋ ከሚፈርሱ ቤቶች ላይ መስኮቶች፣ በሮች፣ ሸክላዎች፣ የወለል ጣውላዎችና የደረጃ ድንጋዮችን ከገዛ በኋላ፣ በእነዚህ ቁሳቁሶች ቤት እፈልጋለሁ አለኝ፡፡
የሥራው ሂደት ምን ይመስላል?
የመጀመሪያው ስራ ቁሳቁሶችን መለየት ነበር፡፡ በብዛት ትላልቅ ቢሞች፣ በሮችና መስኮቶች ነበሩ፡፡ መስኮቶቹና በሮቹ ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ እነሱን ወደ ንድፍ፣ ከዚያ ወደ ዲዛይን ለወጥኳቸው፡፡ የተሰበሰቡት በሮችና መስኮቶች ዲዛይኑ ላይ መለያ ተሰጥቷቸው ተቀመጡ፡፡ ቤቱን ዲዛይን አድርጌ ስጨርስ ደግሞ መስኮቶቹና በሮቹ በተሰጣቸው ስያሜ መሰረት እንዲገጠሙ ተደረጉ፡፡
የቁሳቁሶቹ አሰባሰብ እንዴት ነበር?
በየቦታው ቤት የሚያፈርሱ ሰዎች የዶክተር አድራሻ አላቸው፡፡ ቤት ሊያፈርሱ ሲሉ ደውለው እዚህ ቦታ ቤት ልናፈርስ ስለሆነ ናና የምትፈልገው ነገር ካለ ተመልከት ይሉታል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ቤት ከሰራሁ በኋላ፣ በተመሳሳይ መልኩ ከፍራሽ ቤቶች በተሰበሰቡ ቁሳቁሶች ሌሎች ቤቶችንም ሰርቻለሁ፡፡
ከወጪ አንፃር እንዴት ነው?
ወጪው ጥሩ ነው፡፡ አዲስ ቁሳቁሶች ከመግዛት ይረክሳል፡፡ አንዳንዶቹ በሮች የተገዙት ስምንት መቶና ዘጠኝ መቶ ብር ነው፡፡ አዲሱ ይገዛ ቢባል ወደ 20 ሺ ብር የሚጠጋ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን መስኮቶቹና በሮቹ ከተለያዩ ቤቶች ፍራሽ ላይ የተወሰዱ በመሆናቸው ቀለማቸው የተዘበራረቀ ነበር፡፡ ማፅዳቱና ወጥ የሆነ መልክ እንዲይዙ ማድረጉ ጊዜ ወስዷል፤ የተወሰነ ወጪም ጠይቋል፡፡ በሮቹና መስኮቶቹን ለማፅዳት በኦክሲጅን ቀለማቸው ተልጦ እንዲሸበሸብ ከተደረገ በኋላ፣ በብርጭቆ ወረቀት ታሽተው ቫርኒሽ ተቀብተው ነው ተመሳሳይ መልክ የያዙት፡፡ ሸክላዎቹም ሲመጡ ከሲሚንቶ ላይ ስለወጡ ነጭ ነበሩ፤ በብርጭቆ ወረቀት ታሽተውና ተቀብተው ነው ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡ የተለያዩ አይነት ድንጋዮችንም ተጠቅመናል፡፡ ከአምቦና ከትግራይም አስመጥተናል፡፡
ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ቁሳቁሶች እንዴት ሊጣጣሙ ቻሉ?
 እዚህ ቤት ላይ ሸክላና ድንጋይ እንዲሁም ሸክላና እንጨት ተቀላቅለው ተሰርተዋል፡፡ መጣጣሙ የመጣው ሁሉም የተፈጥሮ ስለሆኑ ነው፡፡ እዚህ ቤት ላይ አልሙኒየም ብንከት አንድነቱ አይጠበቅም፡፡ እንጨትና ድንጋይ አብሮ ይሄዳል፡፡ ተፈጥሮም እንደዚያ ነው የቀላቀለቻቸው፡፡ ዛፍ አፈር ላይ ነው የሚበቅለው፤ ስለዚህ ሸክላና እንጨት ላይጣጣሙ አይችሉም፡፡ ውበት ግኡዝ ነገር አይደለም፡፡ የሃሳቦች ውሁድ ነው፡፡ አንድ የሚያምር የፅጌረዳ አበባ ሳይ ያማረበት ምክንያት ምንድን ነው ብዬ፣ የቀለም ውህደቱንና አወቃቀሩን እማርበታለሁ፡፡ ዛፍ ስናይም በጣም ያምረናል፡፡ ለምን ያምረናል ስንል ምናልባት ከተፈጠርን ጊዜ ጀምሮ ስናየው ስለኖርን ይሆናል፡፡ ዛፍ ውስጥ ግን የምንማራቸው የተፈጥሮ ህግጋት አሉ፡፡ የዛፍ ቅርንጫፍ የት ጋ እንደሚወጣ አናውቅም፤ ግርምት ነው፤ ስለዚህ ከዛፍ የግንድ አበቃቀል አግራሞት የሚፈጥሩ ክስተቶች ተምሬያለሁ፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ልክ እንደ ዛፍ ግንድ ግርምት የሚፈጥሩ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን አስገብቻለሁ፡፡
ኪነ-ህንፃ ሳይንስ ነው አርት በሚል ስለሚደረገው ሙግት ምን ትላለህ?
ይሄ ፀሀይ ብርሀን ነው ሙቀት ብሎ እንደ መሟገት ነው፡፡ በጣም የተያያዙና የማይለያዩ ናቸው፡፡ ስለ አርት ስናወራ፣ አርቱ ያለ ሳይንሱ አይሆንም፡፡ ሳይንሱን ካየን ለአንድ ህንፃ ንፅህና አጠባበቅ የፍሳሽ ማስወገጃው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ውሀ ሪሳይክል ማድረግ ወይም ማጠራቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ብርሀን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እዚህ ቤት በማታ መብራቶቹ በርተው ብትመጪ አሁን ከምታይው ጋር በምንም አይገናኝም፣ በጣም የተለየ ነው፡፡ እኛ ሳይንስ የምንለው በአብዛኛው ከቴክኖሎጂ አንፃር ነው፡፡ ብርሀንን በቀለም  እንረዳዋለን፡፡ ይህ ቤት የጠዋት ብርሀን ሲያርፍበትና የማታ ብርሀን ሲያርፍበት ለቤቱ የሚሰጠውና የሚፈጥረው ቀለም በጣም የተለያየ ነው፡፡
አርቱን ካየን ደግሞ አሁን ለምሳሌ እዚህ ቤት ብዙ ቁሳቁሶችን ተጠቅመናል፡፡ እነዚህ ቁሳቁሶች ኮተት እንዳይመስሉ ግን ብዙ ለፍተናል፡፡ በይዘት፣ በመጠን፣ በቀለም ወዘተ… እንዲጣጣሙ በማድረግ ውበቱ እንዲጠበቅ እናደጋለን ይሄ ጥበብ ነው፡፡ እርስ በእርስ ሊስማሙ በሚችሉ ቁሳቁሶች መስራት ለአይን ሻካራ የሆኑ ነገሮች እንዳይኖሩ ያግዛል፡፡ መስኮት የቤት አይን ነው፤ ስለዚህ ነው እያንዳንዱ የዚህ ቤት መስኮት ሲከፈት አይን ጥሩ እይታ ያለው ነገር ላይ እንዲያርፍ የተደረገው፡፡
ከተለመደው የቤት አሰራር ሂደት በተለየ መንገድ ነው ቤቱን የሰራኸው፡፡ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?
እንደዚህ ቤት ነፃ ሆኜ የሰራሁት ስራ የለም፡፡ ከባለቤቱ ጋር እየተወያየንና እየተስማማን ነው የሰራነው፡፡ በጣም ነፃነት ስለነበረኝ እጅግ ደስ እያለኝ ነው የሰራሁት፡፡ ህንፃ ልክ እንደ ልጅ ነው፡፡ የኪነ-ህንፃ ባለሙያውና የሚያሰራው ሰው እንደ አባትና ልጅ ናቸው፡፡ ሁለቱ የማይስማሙ ከሆነ ልጁ ጥሩ አይሆንም፡፡ ተስማምተው በደንብ መስራት ከቻሉ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ ባለሙያው ቤቱን አምጦ የሚወልድ ቢሆንም ባለቤትም ቤቱ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል፣ በጀቱ ምን ያህል ነው  ወዘተ… የሚለውን ይወስናል፡፡ ጥሩ ስራ ስትሰሪ መተማመኑ ይመጣል፡፡ ከዚያ ደግሞ ነፃነት ይገኛል፡፡ ይህን ቤት ስሰራ አስቤ ያላደረግሁት፣ ነገር ግን ሌላ ስራ ላይ አደርገዋለሁ ብዬ ያሰብኩት ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ተነጋግሬ፣  የኪነ ህንፃ ተማሪዎች ሳይት ላይ መጥተው ከቁፋሮ ጀምሮ ባሉ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ነው፡፡
ለምንድነው ተማሪዎቹን ማሳተፍ የፈለግኸው?
ለምሳሌ የዚህ ቤት ስራ አራት አመት ነው የፈጀው፡፡ ከቁፋሮ ጀምሮ በዚህ ቤት ስራ ላይ የተሳተፈ ተማሪ፣ ትምህርቱን ጨርሶ ሲወጣ ነገሮችን የሚያይበት አይን የተለየ ይሆናል፡፡ አንድ የተሞላ ኮንክሪት ድሮዊንግ ላይ በቃ አንድ መስመር ነው፡፡ እዚያ አንድ መስመር ላይ ግን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብረት፣ ኮንክሪት፣ ኮንዲዩት፣ ፎርም ወርክ፣ የመብራት ኬብል፣ የመብራት መስመር፣ አሸዋ፣ሲሚንቶ፡ ጠጠር እንዲሁም ከዚያ በላይ ደግሞ ወዛደሩና ወዛደሯ አሉ፡፡ ከእነሱ መሀል ምሳ የበላ አለ፤ ያልበላ አለ፣ ከቤት ሰራተኝነት ወጥታ ይሄ ይሻላል ያለች አለች፣ ወደ ቀድሞ ብመለስ ይሻላል በሚል እያመነታች ያለች ትኖራለች፤ሁለቱም ያልተመቻት ደግሞ አለች፡፡ አንድ ተማሪ ይህንን ሁሉ አውቆ ከት/ቤት ሲወጣ ብዙ ነገሮችን ይዞ ይወጣል፡፡
ግቢው እጅግ ባማሩ አበቦችም የተሞላ ነው፡፡ ብዙ ጥረት እንደተደረገበት ያስታውቃል…
አዎ፤ በግቢው ውስጥ 300 የአበባ ዝርያዎች አሉ፡፡ ወደፊት የዕፅዋት አጥኚ (ቦታኒስት) መጥቶ ስለ ዝርያቸው የሚገልፅ ነገር እንዲሰራ ዶክተር እቅድ ይዟል፡፡

Read 7722 times