Saturday, 22 November 2014 12:15

አበረታች መድኀኒቶችና የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(26 votes)

ነባሩን መላምት የሚያፈርስ የጥናት ውጤት ተገኝቷል

አበረታች መድኀኒቶች መጀመርያ የተሰሩት የደም ማነስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ታስቦ ነበር፡፡ መድኀኒቱ የደም ማነስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ያመጣው ለውጥ፣ ቀይ የደም ሴላቸውን ቁጥር በመጨመር የተሻለ አቅምና ብርታት ለማግኘት የሚፈልጉ ስፖርተኞችን ቀልብ ሳበ፡፡ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች የሚሳተፉ ስፖርተኞች ለበለጠ ውጤታማነት አበረታች መድኀኒቶችን መጠቀም ጀመሩ፡፡ መድኀኒቱ የቀይ የደም ሴሎችን ቁጥር በመጨመር፣ ደም ኦክሲጅን የመሸከም አቅሙን የሚያሳድግ ሲሆን ስፖርተኛው በተሻለ ኃይል ውድድሩን እንዲያጠናቅቅና ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ ዝናን የተቀዳጁ ስፖርተኞች፤ ከአበረታች መድሃኒቶች ጋር በተገናኘ የስኬት ማዕረጋቸውን ተነጥቀው ለሃፍረት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በተለይ የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች በመልክአ ምድሩ አቀማመጥ የተነሳ ከሌሎች አገራት አትሌቶች በተለየ ቀይ የደም ሴሎቻቸው መጠን ከፍ ያለ በመሆኑ አበረታች መድሃኒቶቹን ቢጠቀሙም ባይጠቀሙም በውጤታቸው ላይ ለውጥ አያመጣም የሚል መላምት ሲቀነቀን ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በኬንያ በተካሄደ ጥናት ግን ይሄን መላምት የሚያፈርስ ውጤት ተገኝቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ድረስባቸው ኃይሌ በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ተመራማሪዎች አንዱ ናቸው ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአበረታች መድኃኒት ዙሪያ ጥናት አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ድረስባቸው ኃይሌን  በጥናቱ ዙሪያ አጭር ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል፡፡

አበረታች መድሃኒት ስንል ምን ማለታችን ነው?
የቀይ የደም ሴሎች ቁጥርን በመጨመር፣ ደም ኦክስጂን የመሸከም ብቃቱን የሚያሳድጉና ሃይል በመስጠት ውጤታማነትን /performance/ የሚጨምሩ መድሃኒቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና አትሌቶች በስፋት የሚጠቀሙበት ራስፓንቲን (epo) የሚባለው አይነት ነው፡፡  መድኀኒቱ ቀይ የደም ሴሎች ቁጥራቸው እንዲጨምር ለማድረግ ይረዳል፡፡ ሌሎችም የተከለከሉና አንድን ሰው አበረታች መድኀኒቶችን ተጠቅሟል የሚያሰኙ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የራሱን ደም ወይንም ተመሳሳይነት ያለውን የሌላ ሰውን ደም ወስዶ ፍሪጅ ውስጥ በማስቀመጥ ለውድድር ሲቀርብ ቢወስደው፣ ይህም ሰውየውን አበረታች መድኀኒት ወስዷል ሊያሰኘው ይችላል፡፡
ሌሎችም የተከለከሉና ብርታትን ወይንም አቅምን የሚያሳድጉ አበረታች መድኀኒቶች አሉ፡፡ እነዚህን መድኀኒቶች መውሰድ ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን የተወዳዳሪውን ውጤት ከማሰረዝ ጀምሮ ከስፖርቱ ዓለም እስከ ማሰናበት ሊደርስ የሚችል እርምጃ የሚያስወስዱም ናቸው፡፡
ደምን በፍሪጅ ውስጥ አቆይቶ መውሰድ ስንል ምን ማለታችን ነው?
ደም ኦክስጅን የመሸከም ብቃቱን ከጨመረ ፐርፎርማንስ ይጨምራል ይህንንም በተለያየ መንገድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ደምን በፍሪጅ አቆይቶ መውሰድ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ደም ከአትሌቱ ይቀዳና ፈሳሹ ይደፋል፡፡ ከታች የዘቀጠው (ቀይ የደም ሴል) ማለት ነው ፍሪጅ ውስጥ ይገባል፡፡   አትሌቱ ወደ ውድድር ከመግባቱ ከሁለትና ከሦስት ቀናት በፊት በመርፌ ይሰጠዋል፡፡ ይህም ከመድኃኒቱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ውጤት አለው፡፡ የቀይ የደም ሴሎች ቁጥር እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡  
አንድን መድሃኒት የተከለከለ ነው የሚያሰኘውና ከአበረታች መድሃኒቶች ተርታ የሚያስመድበው ምንድን ነው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ አንድ መድኀኒት በህግ በተከለከሉ መድኀኒቶች ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ሶስት መስፈርቶችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም መድኀኒቱ ለአትሌቱ ጤና ጠንቅ መሆኑ በሳይንስ መረጋገጥ፣ ውጤታማነትን የሚጨምርና የስፖርት መንፈስን የሚቃረን መሆኑ (መርሁ፤ አንድ ሰው በተፈጥሮውና ባለው ነገር ብቻ መወዳደር አለበት የሚል ነው) ናቸው፡፡ መድኀኒቱ እነዚህን ሶስት መስፈርቶች ሲያሟላ ወይንም ሁለቱን አሟልቶ ሲገኝ አበረታች መድኀኒት ነው ልንል እንችላለን፡፡
መድሃኒቱ ለአትሌቶች/ለተጠቃሚው ጤና ጠንቅ ነው የሚባለው እንዴት ነው?
መድኀኒቱ ቀይ የደም ሴሎች ቁጥርን ይጨምራል፡፡ በዚህ ጊዜም ደም ይወፍራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መድኀኒቱ ብዙ ላብ እንዲወጣን ያደርጋል፡፡ ላብ ከሰውታችን በሚወጣበት ጊዜ ደግሞ  ደማችን የበለጠ እየወፈረና እየረጋ ይሄዳል፡፡ የወፈረ/የረጋው ደም በቀጫጭኖቹ ደም ማመላለሻ ቱቦዎች ውስጥ እንደ ልብ መመላለስ ያቅተዋል፡፡ ይህ ደግሞ አትሌቱን ለሞት ሊዳርገው ይችላል፡፡ አበረታች መድሃኒቶች በአንድ ወቅት የአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ትልቅ ፈተና ሆነው ነበር፡፡ ኮሚቴው አበረታች መድሃኒቶች እየወሰዱ ለህልፈት የሚዳረጉ አትሌቶችን ሁኔታ መቆጣጠር ሲያቅተው፣ እ.ኤ.አ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ World Anti doping Agency (EADA) የተባለው ድርጅት ተቋቁሞ፣ በአበረታች መድሃኒቶች ቁጥጥር ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ ድርጅት ድጋፍ በቅርቡ በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ላይ አንድ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ እስቲ ስለ ጥናቱና የተገኘው ውጤት ይንገሩኝ?
የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በተለይም የኢትዮጵያና የኬኒያ አትሌቶች መፍለቂያ ቦታዎች ከባህር ወለል 2500 ጫማ በላይ መካከለኛ ከፍታ ወይም High Attitude መግቢያ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እዚህ አካባቢ በመኖራቸው ብቻ ቀይ የደም ሴላቸው መጠን ከፍ ያለ ነው፡፡ እናም አበረታች መድሃኒቶች በእነዚህ አትሌቶች ላይ ያለው ውጤታማነትን የመጨመር አቅም ከሌላ ቦታ (እንደ ስኮትላንድና ዩናይትድ ኪንግደም) ከሚመጡ አትሌቶች ጋር እኩል ሊሆን አይችልም ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ ይሄ ሃሳብ ትክክል ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ነበር ጥናቱ የተደረገው፡፡ ጥናቱ በመጀመሪያ ሊካሄድ የታሰበው በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ነበር፤ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀረና ከኬኒያ 20 አትሌቶች፣ ከስኮትላንድ እንዲሁ 20 አትሌቶች፤ በድምሩ 40 አትሌቶች የተሳተፉበት ጥናት ተካሄደ፡፡ ጥናቱ አስር ሳምንታት የፈጀ ነው፡፡
የኬንያ አትሌቶች ቀይ የደም ሴል መጠን ከስኮትላንዶቹ በተፈጥሮው ከፍ ያለ ነበር፡፡ መድሃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ግን የሁለቱም አገራት አትሌቶች እኩል ሆኑ፡፡ ውጤታማነታቸው (ፐርፎርማንስ) በእኩል ደረጃ አደገ፡፡ ሁለቱም 3ሺህ ሜትሩን ይሮጡበት የነበረው ጊዜ በ6 በመቶ ተሻሻለ፡፡ መድሃኒቱን ካቆሙ ከ4 ሳምንታት በኋላ ምን እንደሚፈጠር ለማወቅ በድጋሚ ለካናቸው፡፡ ውጤቱ እንደሚያሳየው፤ የሁለቱም ውጤታማነት (ፐርፎርማንስ) ከመጀመሪያው በ3 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የጥናት ግኝታችንም፤ የኬኒያና የስኮትላንድ አትሌቶች በመድሀኒቱ እኩል ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያንና ኬኒያውያን አትሌቶች ከመድሃኒቶቹ አይጠቀሙም የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠ ነበር፡፡ ይህንኑ ውጤትም ባለፈው ዓመት በአሜሪካ Collage of Sport Medicine ስብሰባ ላይ ያቀረብነው ሲሆን የ”ኢንተርናሽናል ስኮላር” ሽልማት ተሸላሚ አድርጐናል፡፡      
ጥናቱ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ሊደረግ ከታሰበ በኋላ ወደ ኬንያውያን አትሌቶች እንዲሻገር የተደረገበት ምክንያት ምንድነው?
ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለማየት ብንሞክር፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአበረታች መድሃኒቶች መጠቀም ጋር በተያያዘ ስማቸው አይነሳም፡፡ ነገር ግን በርካታ ኬንያውያን የአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ኬንያውያን አትሌቶች ለጥናትና ምርምሮች በጣም ተባባሪዎች ናቸው፡፡
ጥናቱ እነሱን ሊጠቅም እንደሚችል ካመኑ፣ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ወደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስንመጣ፤ ጥናትና ምርምር እንዲደረግባቸው ፈቃደኛ በመሆን በኩል ብዙ ይቀራቸዋል፡፡
ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ አትሌቶቻችን ቀደም ሲል የነበራቸውን የስኬት ደረጃ አስጠብቆ ለማቆየት ከተፈለገ፣ በጥናት የታገዘ ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአትሌቶቹ ተባባሪነት ወሳኝነት አለው፡፡

Read 3531 times