Saturday, 29 November 2014 10:55

ከጐንደር እስከ ጉዋሣ የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከአበባው መላኩ ጋር ስለጐንደርና ስለ ጉዋሳ የተጨዋወትነው

“ከግጥም ከመሰንቆ ልጆች ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ?” አልኩት፡፡
“ግጥም በመሠንቆዎች ስለ ፓኤቲክ ጃዝ የሚያውቁት ነገር የአለ መሰለኝ፡፡ ወርሃዊውን ዝግጅት የመካፈል ልማድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ በመጀመሪያ የሰማሁት የግጥም በመሰንቆ ቡድኖች ለግጥም በጃዝ ስጦታ ለመስጠት ይፈልጋሉ - ነው፡፡ በ3ኛ ዓመት ዝግጅት ሰዓት ሳይሆን መድረክ መስጠት ይቻላል…ከጐንደር ድረስ መጥተው፣ የጐንደርን ስም ጠቅሰው እንዴት ብለው ይመለሳሉ? ሌላም የሽልማት ፕሮግራም አለንና ያንን መጠቀም ይችላሉ አልን፡፡ መጡ ተገኙ ነገር ግን በራሳቸው ምክንያት ስጦታውን ሊያከናውኑ አልቻሉም” አለኝ፡፡ እኔ የጐንደሮቹን ግጥም በመሰንቆ ቡድኖች ጠይቄያቸው ቴክኒካል ችግር ለሁኔታው አለመመቻቸት ምክንያት ሆኗል ነው ያሉኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ስጦታው በበረከት በኩል እንዲደርሳቸው አድርገናል ነው ያሉት፡፡ መንፈስ ለመንፈስ ግን ተግባብተዋል ብዬ ዘለልኩት፡፡
“ዋናው ነገር ተገናኝተናል፡፡ መስከረም ላይ እኔን ጋበዙኝ፡፡ በረከትን ጠየኩት “ለግጥም የተሰጡ ልጆች ናቸው” አለኝ፡፡ “የግጥም አገልጋዮች ናቸው” አለኝ፤ አለ አበባው፡፡
የግጥም ዲያቆናት፣ ምዕመናን - ማለቱ ነው፡፡
“ወጪያችንን ችለን ለምን እንደግሩፕ አንሄድም?” ተባባልንና ሁላችንም የፓኤቲክ ጃዝ አባላት ሄድን፡፡ አንዳንዶቹ ጐንደርን አይተው ስለማያውቁ ደስ አላቸው፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ የምናውቀው እኔ በ98 አውቀዋለሁ ግሩሜም ያቀዋል - ምሥራቅና ምህረት ናቸው የማያውቁት፡፡ አቀባበላቸው ግሩም ነበር! በጣም ደስ ብሏቸው ነበር…ግጥም ንባቡን በዋናነት እኔ ደጋገምኩ እንጂ ሁላችንም አቅርበናል! አዳራሹ ግጥም ብሎ ነበር! ብዙ ህዝብ ነበር፡፡ የቆመው ከተቀመጠው ይበልጥ ነበር! እኔ እንደዚህ አልጠበኩም፡፡ በአውሮፕላን ችግር ፕሮግራም ተሰርዞ፣ ባዲስ መልክ አዘጋጅተውት ያለቀኑ ተዋውቆ በፌስቡክ፣ በአንዳንድ ቦታ ብቻ አስተዋውቀውት ነው፡፡ ብዙ ሰው መጣ! እነሱም ተደምመው ነበር፡፡ በጣም መልካሙ ነገር ጥሩ የሚሰሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ያየነውንም ትዝብት ተናገርን ጐንደርን ያህል አገር ይዘው፣ በውስጡ ያለውን ታሪክ፣ ላለፉት 250 ዓመት ዘመን ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ትምህርት፣ የአስተዳደር መዲና የሆነች አገር ይዘው ያን ያን እሚሸት ነገር የሌለበት ነገር ትርፉ  ድካም ነው፡፡ ዘጥ ዘጥ ነው፡፡ ዞር ዞር በሉ - ወላጆቻችሁን ጠይቁ፡፡ ወደአቅራቢያችሁ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ጐራ በሉ - መዛግብቱን እዩ፡፡ መዛግብቱ ምን ይላሉ፡፡ በዚያ መጠን ሥሩ፡፡ ታላላቆቻችሁን ጋብዙ - ከዚያ ምን ተገኘ የሚለውን እዩ!...መከርን፣ ሸጋ ነው!
“የባህል ቤቱን እንዴት አገኛችሁት?”
“…ዘመናዊውን ዘፈን እንኳ ወዝ ይሰጡታል፡፡ ሐማሌሌን እንኳ አሳምረው ነው የሚዘፍኑት፡፡ ሕብረ - ብሔራዊ ስሜት አላቸው፡፡ የሁሉ እናት የመሆን ስሜት ነው ያላቸው!... በጣም ቆንጆ ነው! ሴቶች ድራም ይዘው ማየት በጣም ትፍስህት ሰጥቶኛል፡፡ የመጨረሻ ሙድ አለ፡፡ የግጥሞቹ ይዘት ላይ እኔ ትንሽ ያዝ አድርጐኛል! ስሞች እያነሳች ታወድሳለች! ቀረርቶ ሽለላዋ መልካም ነው - ሌላው ግን የሥነ - ቃሉ የግጥሙ ባለቤቶች ሆነው ምንም አዳዲስ ይዘት የላቸውም ወይ? ብያለሁ!” አለኝ፡፡
“የስቴጅ ግጥም አንባቢዎችንስ ብስለት ነገር እንዴት አየኸው?”
“ከ12 ዓመት በፊት ፑሽኪን አዳራሽ ይቀርቡ የነበሩ ግጥሞች ነበሩ! በወጣቶች፣ በሁሉም አቅጣጫ ወጣት ናቸው! ነጠላ ሀሳብ ላይ የማተኮር ችግር አያለሁ! ያንን ጊዜ ያስታውሰኛል፡፡ የተወሰኑ ተስፋ የሚጣልባቸው ነበሩ - በተለይ የዕይታ ነገርን ያበሰሉ ገጥመውኛል…የመለመልነውም ልጅ አለ - ከውስጣቸው፡፡ ልሣን ይባላል፡፡ Talent Hunt ነው፡፡
ከየቦታው ለፓኤቲክ ጃስ ከምነመለምላቸው ለምሣሌ ከወሎ አካባቢ ሼህ ቡሽራ የሚባሉ ናቸው መንዙማ አዋቂ ጋብዘን ሆቴላቸውን አበላቸውን ችለን ነበር - ሌላ መንግሥቱ ዘገየ” ቀብድ የበላች አገር” የሚል መጽሐፍ የፃፈ ነበር - መጽሐፉን አይተን በአድራሻ አገኘነው! እሱንም ቀለቡን ችለን ጋብዘናል! ሀሳቦች አሉን፡፡ ለምሳሌ ደብረዘይት አካባቢ ቶራ ቡላ የሚባል የሥ/ጽሑፍ ማህበር ነበር፡፡ እነሱም እንዲያቀርቡ አስበን ነበር፡፡ እነ ምንተስኖት ማሞን የደብረዘይቶቹን ነግረን ነበር፡፡ ወደ አዋሳ አካባቢም “60 ሻማ” እሚባል ማህበር ነበር፡፡ ይሄ ሃሳብ እያለ ነው እንግዲህ ጐንደሮች ሲጠሩን የሄድነው! እንደነሱ በአውሮፕላን ባይሆን በመኪና ነው!”
በበኩሌ አልኩት፤ “የናንተ አዳራሽ - የእኔ ኦፕን - ኤር ነው! ልዩነቱ ያ ነበር፡፡”
የጉዋሣ ነገር
በረዶ አገር ሄጄ አቃለሁ - አውሮፓ፡፡ እንደ ጉዋሣ ያለ ቀዝቃዛ ቦታ በህይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በነገራችን ላይ ዘፈኑ ግጥም ላይ
“አገሯ ዋሳ መገና፤ አገሯ ዋሳ መገና
ምነው አልሰማ አለች፣ ብጣራ ብጣራ”
“ዋሣ” ይመስለን የነበረው “ጉዋሣ” ነው፡፡ “መገና”ም የመሰለን “መገራ” መሆኑን ልብ እንበል፡፡
ከአዲሳባ ለተነሳ ሰው ወደ ደብረ ብርሃን ይኬድና፤ ጉዶ በረትን አልፎ ወደ ደብረ ሲና አምርቶ (ደብረሲና እንግዲህ ዳኛቸው ወርቁ በአደፍርሱ “እግዜር አገሮች ሰርቶ ሰርቶ የተረፈውን ኮተት ያከተባት ከተማ” ያላት ናት) ጣርማ በር ጋ ሲደረስ ወደ ግራ እጥፍ ነው፡፡ 180 ኪ.ሜ ላይ ማለት ነው፡፡ መዘዞና ባሽ ይቀጥላል፡፡ ወደ ግራ ቢሉ ሞላሌ አለ፡፡ ቀጥታውን ሲኬድና ሲቀጠል ግን ይጋም (Yigam) ይገኛል፡፡ ይጋምን ሲያልፉ ጉዋሣ አጥቢያ ይደርሷል፡፡ በዚያ ወደቀኝ ወደ ካድሉ ወደ አጣዬ ያስኬዳል፡፡ ግራ ግራውን ማህል ሜዳ እንግዲህ ዙሪያ ገባውን አለ፡፡ በማህል ሜዳ ተሻግሮ ወደ ግሼ ይዘለቃል፡፡ እኛ ግን ወደ ማህል ሜዳ ስንሄድ ሰፌድ - ሜዳን አልፈን ነው፡፡
ይሄ ሙሉቀን የዘፈነለት ጉዋሣ ለአዲሳባ ሰሜን ነው፡፡ የቅዝቃዜውን ነገር አለማንሳት ነው፡፡ ከባህር ወለል በላይ ከ3200 -3700 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ የተሰባበረ ተራራ ይታያል፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን “በአንኮበር” ግጥሙ “የፈፋ አነባበሮ” ያለው ነው፡፡
ወደ ምዕራብ የሚጓዙና ሰንጥቀውት የሚያልፉ ስምጥ ሸለቆዎችና የባህር ሸለቆዎች አሉ፡፡ በአባይና በአዋሽ ማህል ያለ ውሃ ማገቻ ነው፤ ቢባል ድፍረት አይሆንም፡፡ የጉዋሣ ምሥራቃዊ ወገን ተረተሩን ቁልቁል ወደሸለቆው ልኮ ታላቁን ስምጥ ገደል ድንገት ሲተረትር ከመነሻው ይርቃል፡፡ ከፍታው መርገብ ይጀምራል፡፡ በ50 ኪ.ሜ ርቀት ውስጥ በ2600ሜ ዝቅታ ደረጃ ባንዴ ውርድ የሚል ታምረኛ ሥፍራ ነው፡፡ ከዚያ ወደ አዋሽ ግርጌ ወርዶ የታላቁን ስምጥ ሸለቆ ወለል ይቀላቀላል፡፡ የጉዋሣ ምዕራብ ደግሞ በድልዳላዊ አካሄድ ወደማህል ሜዳ ይገባል (3000 ሜትር ግድም) መልክዐ - ምድሩና ሠፈሩ እንግዲህ ይሄ ነው፡፡
ከጉዋሣ የግቻ ሣር (Afro alpine) [በአፍሪካ የራሳችን የሣር - ዝርያ ነው] እና በተራራው ትዕይንት መካከል የጉዋሣ ማህበረሰብ ሎጅ (ማረፊያ - መናፈሻ) አለ፡፡ ለዚያ ቦታ እንደወፍ ጐጆ ማለት ነው፡፡ ክፍሎቹ፤ በትልቅ ቅጽ ተገነቡ እንጂ በልማዳዊ መንገድ የተሠሩ የወፍ ጐጆዎች ማለት ናቸው፡፡ የጉዋሣ ማህበረሰብ ነው የሚያስተዳድራቸው፡፡ አራት ባላመንታ - አልጋ ክፍሎች (“ጭላዳ”፣ “ቅልጥም - ሰባሪ”፣ ቀይ ቀበሮ” የሚባሉ የከፋ ቀን በአገሩ በሚገኙት ብርቅዬ እንስሳት የተሰየሙ) አይቻለሁ፡፡ ከኒህ በተለየ፣ የእሳት መሞቂያን ያካተተ እልፍኝ፤ ምግብ - ቤትና ማድቤት ያለው ትልቅ የእንግዳ  ማረፊያ ክፍል አለ፡፡ የትምህርትና የመረጃ ማዕከል ባንድ ወገን ያለ ሲሆን፤ የመታጠቢያና መፀዳጃ ያለው ዘርፍ - ክፍልም አለ፡፡ ለካምፕ አመቺ ቦታ አለው፡፡ የገዛ ድንኳን ይዞ አሊያም ከማህበረሰቡ ቱሪዝም ማህበር ተከራይቶ ደንኩኖ መሥፈር ይቻላል፡፡ ሰው የገዛ ምግቡን ሸክፎ መምጣት እንዳለበት መቼም ግልጽ ነው፡፡
የጉዋሣ ማህበረሰብ አካባቢ ጥበቃ አጥቢያ በመኪና መንገድ የሚደረስበት ነው፡፡ ከአዲሳባ ማህል ሜዳ በሚሄደው ህዝብ ማመላለሻ ሽር ማለት ይቻላል፡፡
ጉዟችን መጀመሪያ ከደብረ - ብርሃን 15 ኪ.ሜ የምትገኘው “አማፂዎቹ” የተባለ ቦታ ቁርስ በመብላት እንደሚጀምር የጉዞ - መሪያችን አብስሮናል፡፡ “አማፂዎቹ”ን ለማወቅ መቼም ከስማቸው መረዳት ነው ዋናው” ነው ያለን ጉዞ መሪው፡፡ በኋላ የደረስነው አንድ ጉብታጋ ነው፡፡ ከዚያ ሆነው ቁልቁል ሲያዩ የሚያምር መልክዓ ምድራዊ ትርዒት አለ፡፡ የኢትዮጵያ አብያተ - ክርስቲያናትና ቤተ - መንግሥቶች ለምን ከፍታ ላይ እንደሚሠሩ ተወያየን፡፡ ከፍታ አንድም ለማየት አንድም ለመታየት ነው - ተባባልን፡፡
ከዚያ እንግዲህ ጣርማ - በር ላይ ታጥፈን ማረፊያ - መናፈሻው (Lodge) ጋ ደረስን፡፡ ምሣ በላን፡፡
ከዚህ ወዲያ ነው ጉዱ! የእግር ጉዞ ተጀመረ፡፡ የእግር ጉዞ ታሪክ አስረጂ አጠገባችን አለ፡፡ እኔ ብዙም ሳልራመድ ዳገቱ ያደክመኝ ገባ፡፡ አንዴ አረፍኩ፡፡ ትንሽ ሄጄ ልቤ ያለልክ ትመታ ጀመር፡፡ “በቅሎ ቢመጣልኝ ይሻላል” አልኩ፡፡ መቼም ከተሜዎች ናቸውና መድከማቸው አይቀርም ብለው ነው መሰል፣ አገሬው በቅሎ እየነዳ ይከተለናል፡፡
አንዷን በቅሎ አመጡልኝ፡፡ በበቅሎ ተጉዤ አላውቅም፡፡ እንዴት ልውጣ? ወደ አንድ ከፍ ያለ አፋፍ በቅሎዋን አስጠጉልኝና ተደጋግፌ ወጣሁ፡፡ በቅሎዋን የሚስቡልኝ አንድ አጭር ቆፍጣና አዛውንት ናቸው፡፡ ነገረ- ዕንቆቅልሹ ገረመኝ፡፡ እኒህ የ81 ዓመት ሽማግሌ መንገዱን እንደወጣት ይሸነሽኑታል፡፡ እኔ ደግሞ ከሳቸው በጣም በዕድሜ የማንሰው ዘመኔኛ በቅሎ ላይ ነኝ! የበቅሎ አነዳድ መመሪያ ተሰጠኝ:-
ዳገት ሲሆን ወደ ኮርቻው ቀዳማይ ድፍት!
ቁልቁለት ሲሆን ወደኋላ ልጥጥ ማለት!
“ቁልቁል መሳብ፣ ሽቅብ መሳብ” እንዳለው ደራሲው፤ ወጣነው፡፡ ወረድነው፡፡ አሥራ ሰባቱን ኪሎ ሜትር ተጓዝነው!
መኪናችን ዕቃችንን ሸክፎ ቀድሞን ደርሷል፡፡ ቀድመው ለጥናት የመጡ ፈረንጆች እዚሁ ግድም መሥፈራቸውን ምልክት አየን፡፡
ሰው ሁሉ ደረስን ብሎ እፎይ ማለት ሲቃጣው፤ “ፍራሽና አንዳንድ የመኝታ ዕቃ ይዛችሁ ሽቅብ ውጡ፤ መድረሻችን ገና ነው” ተባለ፡፡ ያዳሜ ወሽመጥ ቁርጥ አለ! እዚሁ አይቀር ነገር ሁሉም አንዳንድ ፍራሽና የመኝታ ዕቃ እየያዘ ዳገቱን ተያያዘው፡፡ እንዳይደረስ የለም ተደረሰ፡፡ እኔ ሙላዬ ተላቋል፡፡ ብሽሽቴ ቀልቷል!
ካምፕፋየር ሊደረግ እሳት ተያያዘ፡፡ ፍልጥ ተደመረ፡፡ ነደደ፡፡ ሙቀት መጣ፡፡
ጉሙን ግን ማን በግሮት፡፡ አርድ አንቀጥቅጥ ነው፡፡ አገሬው አሁንም ዕቃ ያመላልሳል፡፡ ብርዱ -10 (ኔጋቲቭ 10) ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፡፡
ስለ ጉዋሣ ለማወቅ አፈ - ታሪካዊ ትውፊቱን አንብቤያለሁ፡፡
እንደቀበሊኛው አፈ ታሪክ ከሆነ ጉዋሣ የተፈጠረው አንድ መነኩሴ ከተራገሙ በኋላ ነው፤ ብሎ ይጀምራል፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ ቦታ እጅግ የበለፀገ የግብርና ቦታ ነበር ይባላል፡፡ በጣም ምርጥ የተባለ ጤፍ ይመረትበት ነበር፡፡ አንድ መልካምና ብልህ የሆኑ አቼ ዮሐንስ የተባሉ መነኩሴ እዚያ ቦታ ይኖሩ ነበር፡፡ ሥራቸውን በሚገባ እያከናወኑ መሬቱንም ባርከውት ነበር፡፡ ሆኖም አንዲት ሴት ከመነኩሴው ልጅ ፀንሻለሁ ብላ በማውራቷ በመነኩሴውና በአገሬው ፊት አረጋግጪ ተብላ ሸንጐ ፊት ቀረበች፡፡
“ዋሽቼ ከሆነ ድንጋይ ያድርገኝ” ስትል ማለች፡፡
ወዲያውኑ ወደ ድንጋይ ተቀየረች፡፡ መነኩሴው ግን በዚህ ብቻ አልረኩም፡፡ ሰው እሷን በማመኑም በጣም ቅር ተሰኙ፡፡ ስለዚህም ያንን ቦታ
“አንተ ቦታ ከእንግዲህ የተረገምክ ሁን!! የመጨረሻ ቀዝቃዛና ጨፍጋጋ ሁን!! የበለፀገው የግብርና ምርትህም ከእንግዲህ ግቻ ይሁን!!” ብለው ረገሙት፡፡ ይህን ሲሉ ወዲያው የአካባቢው አየር ተለወጠ፡፡ መሬቱም ዛሬ የሚታየው የጉዋሣ ቦታ ሆነ፡፡ አፍሮ አልፓይን የሣር ዘር መሆኑ ነው፡፡ ያ መርገምት መንደሩን ደሀ አደረገው፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ያገር ሽማግሌዎች ይቅርታ ብንጠይቅ ይሻላል ተባባሉ፡፡ እኒያን መነኩሴም ፍለጋ ያልሄዱበት ቦታ የለም፡፡ ሆኖም መነኩሴው ከረዥም ጊዜ በፊት አርፈው ኖሯል፡፡ ሰዎቹ ግን አፅማቸውንም ቢሆን መፈለግ አለብን ብለው ፍለጋቸውን ቀጠሉ፡፡ የመነኩሴው መንፈስ ቢታደገን እንኳ ብለው በአጥቢያቸው አፅማቸውን ሊያሣርፉ አስበው ነው፡፡ አፅማቸው ተገኘና ፍሩክታ ኪዳነ ምህረት ዳግመኛ ተቀበሩ፡፡ ለሠራኸው ጥፋት የምትከፍለው ብዙ ነው! መንፈሣዊ ፀጋ ድህነትን ለማሸነፍ አስፈላጊ ነው!
ሰዎቹ ራሳቸውን በመውቀስ የድህነታችን ዕንቆቅልሽ ታሪኩ ይሄ ነው ይላሉ፡፡     
እንግዲህ ከአበባው ጋር ወደ ጓሣ አብረን ሄደናል፡፡ “ስማ፤” አልኩት፡፡ እርግጥ ካንተ የምለየው፤ እኔ ጉራጌ አገር ዘሙቴ ማርያም ነበርኩ፤ ከዚያ ጐንደር ከዚያ ጓሣ መሄዴ ነው! የእኔ የጓሣ አመለካከት አለ ያንተስ? አልኩና ጠየኩት፡፡
“እኔ የሀረር ሰው ነኝ - ደጋ አደለም - ቆላ ነው - የሚስማማኝም ቆላ ነው!
ከመሄዳችን በፊት የተሰጡኝን ማስገንዘቢያዎች አንብቤአለሁ! አለባበስ -የእጅ ጓንት ወዘተ ያንን ማሳሰቢያ በአክብሮት ካነበቡት አንዱ እኔ ነኝ! እኔ ብርድ በኃይል እፈራለሁ - ለምን እንደሆነ አላውቅም! መድረስ አይቀርም ደረስኩ፡፡ ከከፍታ በላይ ከፍታ ላይ አስደንጋጭ ቪው ነው ያየሁት! ዓለምን በተዛማጅ ከፍታ ማየታችን እየተፈታልኝ ነው የተጓዝኩት - ደስ ብሎኛል፡፡
ቦታው አስደናቂ እንደሆነብኝ ጓሤዎችም አስደንግጠውኛል! ሰው መውደዳቸውና ትህትናቸው! ሁለተኛ እርስ በርስ ያላቸው መግባባትና መከባበር! በተፈጥሮአችን እኛ ከተሜዎቹ እራሳችንን እንለይና የበዛብን ሲመስለን በጣም አጉረምራሚዎችና ተናዳጆች፤ በተለመደው መከባበር፣ ጠባይ ውስጥ አደለም ሥራችንን የምናከናውነው! ብሶተኛ ይበዛል - ፉከራው ይበዛል! ያ ነገር እዚያ የለም! ሸክም ተሸክመው በቅንነት ይኖራሉ እነሱ! ሰዎችን ለማገልገል፣ ለመርዳት ያላቸው ጉጉት፤ መመራመር ሳያስፈልግ እነሱ ተፈጥሮን ተገዳድረውታል ብዬ እላለሁ! ሠርፀው ገብተዋል፡፡ በቅሎ ላይ መውጣቴ፤ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በቅሎ ላይ የወጣሁትና፤ ደስ ብሎኛል! ለመጀመሪያ ጊዜም ነው 3700 ከፍታ ላይ የወጣሁት እዚህ ስገኝ!
በቅሎ ላይ መውጣቴ ጥቅሙ በእግሬ እንቅፋት እያየሁ መሄዴ ቀረና በቅሎ ላይ ሆኜ አካባቢውን አያለሁ፡፡ ዞር ስልም የጓደኞቼ ቅፍለት በጉም ውስጥ የሚጓዙ ከሌላ ፕላኔት ድንገት የተከሰተ ስዕል ይመስላል፡፡ በቅሎ ላይ ሆነን ቁልቁለት ወገብ መለመጥ፣ ዳገት ማቀርቀር ነው ዘዴው፡፡ የበቅሎ ጉዞ ስርዓቱ! ወሳኝ መመሪያ! ላለመውደቅ ለማሸነፍ ለመድረስ! የህይወት ልምድ ተመክሮ ነው!
መቼም ውቴል የሚባል ነገር የለም፡፡ እንግዳነታችን ለተፈጥሮ ነው፡፡ የሚያስተካክለንም ተፈጥሮ ነው፡፡ በተፈጥሮ ዳገት ላይ ጉምና ብርድ ለብሶ ለማደር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
አንድ ሁለቴ ውሃ ተጐንጭቻለሁ፡፡ በቅሎዋ ላይ ሆኜ ጉም ግን እየዳበሰኝ ያልፍ ነበር፡፡ ጢሜ እርጥበት ጤዛ አለው፡፡ ገርሞኝ አገሬውን ጠየኩ፡፡ “ይህ የጉም ሽንት ነው አሉኝ!” ጉሙ ሸናብኝ መቀበል አለብኝ! ይሄ የመጀመያዬ ቀዝቃዛ አገር ነው” አለኝ፡፡
“የእኔ የአውሮፓ ልምድ ይለያል፡፡ መኪናው በረዶ ለብሶ ባካፋ ይዛቃል፡፡ ትልቁ ልዩነት እዚያ ቤት ስትገባ ባየር ማረጋጊያ ሙቅ አየር አለ፡፡ ኮትህን ማውለቅ ይጠበቅብሃል፡፡
ሁሉንም አንድ ላይ እናስበው፡፡ ከNTOው ገላጭ ሌላ አገሬውም ይግለጥልን፡፡ እኔን የመሩኝ ሰውዬ “ነዶና ሰው ተጣላ፤ አዝመራው እምቢ አለ” አሉኝ፡፡
ሌላ እንደኔ ገርሞህ ከሆነ ህፃናትና ሴቶች አላየንም (ውሻም አላየንም ብዬ ነበር) የህብረተሰቡ Pillar የሚባሉትን ሁለት አካላት ህፃንና እናት አላየንም፡፡ ለምሣሌ ዘሙቴ ማርያም ስሄድ ግብዳ ግብዳ ሻንጣችንን ጩጬ ጩጩ ልጆች ናቸው አንከብክበው ዳገት ቁልቁለቱን ፉት ያሉት! ምናልባት ማህል ሜዳ እሚባለውጋ ገብተን ባለመሆኑ ሊሆን ይችላል! ወንድ ይበዛል - ምናልባት ሴቶችና ልጆች እንዴት ነበር ልናገኝ እንችል የነበረው? ቆይ አዘጋጁን እጠይቀዋለሁ፡፡ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሽማግሌዎች በቅሎ መሳባቸው ገርሞኛል፡፡ እኔ በቅሎ ላይ ሆኜ ስጠይቃቸው ዞርም ቀናም ሳይሉ፣ ወግ ባይን ይገባል ሳይሉ፤ መልስ እየሰጡኝ ወደፊት ይገሰግሣሉ በቃ! ተፈጥሮን እኔ አደንቃለሁ፡፡ ለነሱ ተፈጥሮ ተፈጥሮ ነው በቃ! የኑስ የተባለው መንገድ ገላጫችን ያስረዳን የፀሐይ መውጣት መግባት ለነዚህ ሰዎች ጉዳይ አደለም፡፡ ስለ ኢሮብ ሰዎች ስለአዲግራት ሳወራቸው ነበር መኪና ውስጥ ሆነን፡፡ ኢሮቦች ምን ይላሉ መሰለህ “አናንተ ከደርግ ሸሽታችሁ ለመጠለልና ለመዋጋት ነው እዚህ የምትመጡት፡፡ እኛ ግን እንኖርበታለን፡፡ ኑሯችን ይሄው ነው!”
እዚህ አገር ጅቡ እንዳንተ አገር እንደ ሐረር ለትርዒት አይታይም፡፡ ጉልበተኛና ከመጣ የማይመለስ ነው አሉ! ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቅልጥም - ሰባሪ፣ ቀይ ቀበሮ እንደሚኖርበት ጅብም ጓሣኛ ሆኗል!
ማታ ካምፕ ፋየር አደረግን፡፡ ዘቡ መሣሪያ ይዘናል ሳይል ሽለላ ጀመረ፣ ዋሽንት ነፋ ጣሰው! ቅዝቃዜ መሸነፍ ጀመረ፡፡ ይህ ነገር ቢቀረፅ እንዴት አሪፍ ነበር፡፡ ቆጨኝና “እኛን ዓይነት ሰዎች አምጥታችሁ፣ በጥበብ የማርያም መንገድ ምንም ሊፈጠር እንደሚችል እያወቃችሁ፣ ምንም የዶክመንቴሽን ሥራ አለመሠራቱ በጣም ያሳዝናል፡፡
የመጀመሪያ ትምህርታችሁ ይሁን!” ብዬዋለሁ ለሀላፊው ለኤፍሬም (ኤፍሬም ከበቅሎ ቀድሞ ዳገት አፋፍ የሚወጣ፣ ቁልቁለት ወርዶ ቀድሞ ሜዳውን የሚረግጥ፤ ሰው ደከመኝ ብሎ ሲያርፍ እሱ ድንኳን ተከላና ሸከማ የሚጀምር፣ ቀጭን ትዕዛዝ በትህትና መስጠት የሚችል እንደ ኤስኪሞ ጀቦንቦን የለ ልብስ የለበሰ አምበሳ ኃላፊ ነው!)
ለላው ደግሞ ከአገሬው ጋራ መዋሃድ፣ ገብሱ ከየት እንደሚመጣ ማየት ነበረብን፡፡ እንደገጣሚ ይሰማኛል፡፡ ሰውን ስታውቅ ነው ተፈጥሮ ሙሉ የሚሆነው፤ አልኩኝ በልቤ፡፡ “ሎጁ ላይ ገለፃውን ሳናዳምጥ አቋርጠን መሄዳችን ቅር ብሎኛል” አለ አበባው፡፡ ልጁ፣ ገላጩ ዐረፍተነገሩን እንኳ ሳይጨርስ ነው መንገድ የጀመርነው፡፡ አሰቅቀነዋል - እኛም ሙሉ ሳንሆን ነው መንገድ የጀመርነው ማለት ነው፡፡ ዕውነት የሚመጣው የሰው ትንፋሽ ሲጨመርበት ነው - እኔ በዚህ አምናለሁ - አልኩት፡፡ ጆሮህ ቅላፄ ይናፍቃል - መፃፍ ማለት ያ ነውና! እኔ ቁጭት ነው ያለኝ!...Next time መምጣታችን አይቀርም ግን 1st Impression is last Impression የሚባለውን የሚያክል የለም! ገላጩ ልጅ እንደዛ ተገናኝተን ተዘጋጅቶ ካፉ የሚወጣውን ሳንሰማ ሄድን! ሰውየውን ከነቃናው ከነትንፋሹ ማግኘት ነበረብን፡፡ መግባባት ማለት ያ ነውና! የታሪክ ነጋሪውንም History የሚናገረውን በመንገድ ላይ ሙሉ ነገር አላገኘንም! በዚያም አንፃር ጐሎብናል! እንደወዳጅ ቀርበነው ማውጋት ነበረብን! ያ ጅምላውን ነገር ሙሉ አያደርገውም፡፡ እንደ ጋዜጠኛም እንደ Poetም ይመለከተኛል!…ገበሬው ጋ ችግር እንዳለ በቅሎ ሳቢው ነዶና ሰው ተጣላ ካሉኝ በኋላ የዘይት ዋጋ፣ የጨው ዋጋ የኢኮኖሚ ችግር እያልን ከተማ የምናወራውን From The Horses Mouth ከግብርናው ጌታ ሰማነው፡፡ ዕድገት አለ የለም ያኔ ትወስናለህ!
እንደተመክሮ ድንቅ ነገር ነው! ሪፖርት ሳይሆን ህይወት ሊኖረው ይገባል! ስሜቴን ልቀጥልልህ:-
ጣሰው ስለዋሽንት ቢነግረኝ በጣም ድንቅ ይሆናል! ጠባቂዎቹ እንደወታደር ጠባቂ ነን ብለው አልራቁንም - አብረውን ካምፕ ፋየር አደረጉ፡ የዕውነት ህዝባዊ ስትሆን ልባዊ - ህዝባዊ ነው የምትሆነው! መሣሪያውም፣ እኛም፣ ጠባቂዎቹም፣ ዋሽንቱም…እኩል እሳት የሚሞቅበት ነው ጉዋሣ! ህዝባዊነት፣ ቱሪስትነት፣ የአካባቢ ጥበቃና ጥበብ ሁሉም ማዕቀፋቸው እሳት ነው! እሳት ወይ አበባ እዚህም አለ፡፡ ለዚህ ነው በየፓርኩ ግጥም ይነበብ የሚለው ሃሳብ ትርጉም የሚኖረው! እንደማሳሰቢያ፤ ለአዘጋጆቹ ይህን እላለሁ:-
ቅድመ - ማስገንዘቢያ ቢኖር፡፡ ከከባዱ ወደ ቀላሉ ከመሄድ ለአፍቃሬ - ግጥሙ የፓኤቲክ ጃዝ ተከታታይ ከቀላሉ ወደ ውስብስቡ ቢኬድ (Law of dialectics)፡፡ ብቁ ዶክመንቴሽን (ምስለ - ዘገባ) ቢኖር፡፡ የማህበረሰቡ ተሳትፎ በቂ ቦታ ቢያገኝ፡፡ የማህበረሰቡ ክህሎት ተጠንቶ ከገጣሚያኑ ቢዋሃድ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር መጣረርም ኅብር - መፍጠርም የጥበብ አካል መሆኑ ልብ ቢባል፡፡ የቴክኖሎጂ ግብዓት ከተፈጥሮው ሁኔታ ጋር መጣጣሙ ቢታሰብበት የተሻለ ታሪክ የመዘገብ አቅም ይኖረናል!


Read 4083 times