Monday, 08 December 2014 14:22

የፓርቲዎች ትብብር “የአዳር ተቃውሞ” ማወዛገቡን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

“የፓርቲዎች ትብብር” በሚል ስያሜ በዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመሠረተው ቡድን፤ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል መርህ የተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል - ምንም እንኳን ያለፈው ሳምንት ዕቅዱ ሳይሳካ ቢቀርም፡፡ ዛሬና ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያካሂደው የ24 ሰዓት የአዳር ተቃውሞ፣ እስከ 150ሺ ሰዎች ይሳተፋሉ ብሎ እንደሚጠብቅም ትብብሩ ጠቁሟል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ተቃውሞውን በመስቀል አደባባይ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ፈቃድ አላገኘም፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመንግስት ተቋማት የሚበዙበት እንዲሁም ልማት የሚካሄድበት ሥፍራ በመሆኑ ቦታውን እንድንቀይር በደብዳቤ ተገልጾልን ነበር ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የትብብሩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ ተቃውሞውን የሚያደርጉት መንግስት እንዲሰማቸው በመሆኑ የቦታ ለውጥ እንደማያደርጉ ለመስተዳድሩ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከኢንጂነር ይልቃል ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ፤ ዛሬና ነገ እናካሂደዋለን ባሉት የአዳር ተቃውሞ፣ በግንቦቱ ምርጫና በሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ስልትና ፖሊሲ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡  
ከኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
መስተዳድሩ ለመስቀል አደባባይ የተቃውሞ  ስብሰባ እውቅና አልሰጠም  

  • ትብብሩ፤ “እውቅና የመስጠትና የመከልከል ሥልጣን የለውም” ብሏል
  • “አባቶች ይፀልዩ ስንል ኢህአዴግ በፀሎት ይወርዳል ማለት አይደለም”
  • መንግስት አልሰማ ስላለን፣ ብርድ እየመታን ጥያቄያችንን እናቀርባለን

        ትብብሩ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ለ1 ወር የሚዘልቅ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የሚል የተቃውሞ መርሃ ግብር እንደቀረፀ አስታውቆ ነበር፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ምን ስኬትና ኪሳራ ገጠማችሁ?
ስኬት እንግዲህ አተያዩ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ሚዲያውን በማግኘት፣ በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በመሆን እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብና ለሚመለከተው አካል ጥያቄያችን ምን እንደሆነ በማሳወቅ በኩል ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተናል፤ ስኬታማ ነበርን ማለትም ይቻላል፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴያችን የአለማቀፉን ማህበረሰብም ሆነ የሚዲያዎችን ቀልብ መያዝ ችለናል፡፡ ሌላው ያቀድናቸው የአደባባይ ስብሰባዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ይሄን ለማድረግ ስንነሳ የመንግስት ጫና ተባባሰ፡፡
የጫናው መብዛት ነፃነት የለም የሚባለው ትክክል መሆኑን ያሳያል፤ መንግስትም ፈርቷል ማለት ነው፡፡ ምንም አይነት የተለየ አማራጭ ማየት ስለማይፈልግ፣ ከእለት እለት ሸምቀቆውን እያጠበቀ መጥቷል፡፡ ይሄም ከምርጫው በፊት ነፃነት እንደሚያስፈልግ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ መንግስት የአደባባይ ስብሰባዎችን ለማሰናከል የሄደበት ርቀት፣ ጥንካሬያችንን እንዲሁም ጥያቄያችን ትክክል እንደነበር ያሣያል፡፡ ከምርጫው አንዳች ነገር በቀላሉ ይገኛል ብሎ የሚገምት የዋህ ካለም፣ ምንም ነገር እንደማይገኝ የተረጋገጠበት ሂደት ነው፡፡
አሁን ህዝቡም ከእኛ ጋር መሆን እንዳለበት የተገነዘበ ይመስላል፡፡ እኛም የመንግስት ፍርሃትና ጭንቀት መጨመሩን ተገንዝበናል፡፡ ይሄ ፍርሃቱ ወደ በለጠ ጭካኔ ይወስደዋል ወይስ ህዝቡ እንዲተነፍስ ነፃነቱን ለቀቅ ያደርግለታል? በራሱ በኢህአዴግ ምርጫ መልስ የሚያገኝ ጥያቄ ነው፡፡
በዘመቻ መልክ ተቃውሞ ከማድረግ ይልቅ በድርድር ጫና መፍጠር የተሻለ እንደሆነ የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ በእናንተ እምነት ከመደራደርና በዘመቻ የአደባባይ ተቃውሞ ከማድረግ  የትኛው ተጨባጭ ውጤት ያመጣል ትላላችሁ?
የፖለቲካ ድርድር የሚመጣው ከነባራዊ ሁኔታዎች ተነስቶ ነው፡፡ ከድርድሩ ሁሉም ሃይል እጠቀማለሁ ብሎ ሲያስብ ነው፡፡ ወደ ድርድር ለመግባት የሚቻለው በዚያኛው ወገን ያለው አካል አማራጭ የፖለቲካ ሃይል መሆናችንን ሲያምንበትና እውቅና ሲሰጠን ነው፡፡ ለመደራደር የድርጅት የድጋፍ ሃይልና ተቀባይነት ወሳኝነት አለው፡፡ በመሠረታዊ ሃሳብ ደረጃ ግን እኛ ወደ አደባባይ ለመውጣት ከማቀዳችን በፊትና ስምምነቱም ከመፈረሙ አስቀድሞ 12 ፓርቲዎች ሆነን፣ ለምርጫ ቦርድ መጀመሪያ በደብዳቤ የጠየቅነው ድርድር ነው፡፡ ከጊዜ ሠሌዳው በፊት ቦርዱ ገለልተኛነቱ እንዲረጋገጥ የሚመለከታቸውን ወገኖች ያወያይ ብለን ጠይቀን ነበር፡፡
ነገር ግን በመንግስትም ሆነ በምርጫ ቦርድ በኩል ለጥያቄያችን መልስ መስጠት አልተፈለገም፡፡ እኛ ቲያትረኛ ወይም የአርት ሰዎች አይደለንም፤ ዝም ብለን መጮኽ ምን ያደርግልናል?
የፖለቲካ ግብ አለን፤ ግባችንን ከዳር ለማድረስ መወያየት እንዳለብን አምነን፣ በዚያ መንገድ ተጉዘን ነበር፤ ሆኖም አልተሳካም፡፡
ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም እያላችሁ በምርጫው ሂደት እንደምትሳተፉ ገልፃችኋል፡፡ ባላመናችሁበት ጉዳይ ላይ መሳተፉ አንዳንዴ ራሳችሁ እንደምትሉት “ኢህአዴግን” ወይም ሂደቱን ማጀብ አይሆንም?
በፖለቲካ ውስጥ ወቅታዊ መሆንና ያለውን እድል ተጠቅሞ የጠበበውን እያሰፉ መታገል ተገቢ ነው፡፡ አኩራፊና ተስፋ ቆራጭ ህብረተሰብ፣ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ አይሆንም፡፡ ዲሞክራሲ የሚመነጨው ከህዝብ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ከውጤት በላይ ለሂደት ይጨነቃል፡፡ ለምሣሌ ሰሞኑን የምርጫ ምልክት ውሰዱ ተብሏል፤ አንወስድም ብለን ብንቀመጥና ጥርና የካቲት ላይ ነገሮች ቢስተካከሉ ተመልሰን ምልክት የምንወስድበት አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ በሂደቱ መቆየት ነገሮቹ ከተስተካከሉ፣ ካለንበት ቦታ ሆነን ለመቀጠል ያስችለናል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን እንኳን ምርጫ ሊታሰብ፣ ሰው ተሰብስቦ መነጋገር አልተቻለም፡፡
ኢህአዴግ በህዝብ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት ስላለቀ፣ ያለ ማፈርና ያለ ይሉኝታ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ በኩል ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ግን ህዝቡ ለነፃነቱ የቆመ መሆኑን ካረጋገጠ፣ ብዙ ነገሮች ይለወጣሉ የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ስልጣን የሚያሳጣው ነገር እንዳለ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ይሟሟታል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ “ስልጣኑ የኔ ነው፤ እፈልገዋለሁ” ካለ፣ ኢህአዴግ ሳይወድ በግድ ወደ ድርድር ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በምርጫው ሂደት የምንሳተፈው ሂደቱን ለማስተካከል እንጂ በአሁኑ አያያዝ ነፃ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት የለንም፡፡
እስቲ ያለፉትን ሁለት አገራዊ ምርጫዎች ከዘንድሮ  ቅድመ ምርጫ ሂደት ጋር ያነፃፅሩልኝ?
በቀላል ቋንቋ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ ብለን ስንመለከት፤ በኢህአዴግ የውስጥ ባህሪ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ “አምባገነን”ና የፈለግሁትን አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ አገዛዝ ነው፡፡ ነገር ግን በ1997 ምርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በአለማቀፍ ደረጃና በአፍሪካ ጉዳዮች ከፍ ከፍ ብለው የታዩበት ወቅት ነው፡፡ በቶኒ ብሌር የተመሠረተው የአፍሪካን ፓርትነርስ ኢንሼቲቭ ሰብሳቢ ሆነው ነበር፣ በG-8 እና G-20 ስብሰባ ላይ ይጠራሉ፣ የአፍሪካ የአዲሱ ትውልድ መሪ እየተባሉ ይሞካሻሉ፡፡ ያ ጊዜ ደግሞ የተቃዋሚው ሃይል ደካማና የተከፋፈለ ነው የሚል ግምት ስለነበራቸው፣ ምርጫውን የራሳቸውን ክብር ለማሳደግ ሲሉ ክፍት አደረጉት -“እንከን የለሽ ምርጫ” አሉት፡፡ በዚያች በተከፈተች ቀዳዳም የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶት በማያውቀው ሁኔታ የተማሩና በማህበራዊ ደረጃቸው የተከበሩ ሰዎች ዘው ብለው ወደ ምርጫው ገቡበት፡፡ የኢህአዴግ ተሳስቶ በሩን መክፈትና የነዚያ ትላልቅ ሰዎች በምርጫው ላይ መሳተፍ፣ ያልተጠበቀ ክስተት ፈጠረ፡፡ ያኔ ኢህአዴግ ተደናገጠ፡፡ ከዚያም በድንጋጤ በሩን ጥርቅም አድርጎ መልሶ ዘጋው፡፡ ተቃዋሚዎችን እስር ቤት ከተተ፣ አፋኝ ህጐችን ማውጣት ጀመረ፡፡ በዲሞክራሲ መቀለድ አይቻልም ተባለ፡፡
ኢህአዴግ ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ ሰየመና በ99.6 በመቶ ድምጽ ማሸነፉን አበሰረን፡፡ ይሄ ውጤት “ዲሞክራሲያዊ ነኝ በሚል ስርአት ውስጥ የማይጠበቅ ነበር፡፡ ውጤቱ ድንጋጤ ሲፈጥርባቸው፣ እድገትና ትራንስፎርሜሽን የሚል እቅድ አመጡ፡፡ ያ የተለጠጠ እቅድ ግን  መፈፀም የማይቻል ሆነ፡፡ የሰብአዊ መብት ጥቃቱ ተባብሶ ቀጠለ፣ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት፣ የዜጐች መፈናቀል፣ ስራ አጥነት-- እያየለ  መጣ፡፡ በዚህ የተነሳ አሁን ህዝቡ “ከኢህአዴግ ውጪ የትኛውም አካል ይምጣልኝ” የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይሄን ደግሞ ኢህአዴግም ህዝቡም ተገንዝበውታል፡፡ ከፍርሃቱ የተነሳም ተቃዋሚዎችን ወደ ማፈን ተሸጋግሯል፡፡ ይሄኛውን ዘመን ለየት የሚያደርገው፣ ህዝቡ ለውጥ መፈለጉ ነው፡፡ ኢህአዴግ አሁን በመርህ ደረጃ  ተሸንፏል፡፡ የመውጫ መንገድ የማጣትና የመፍራት ነገር ነው የሚታየው፡፡
ኢህአዴግ በመርህ ደረጃ ተሸንፏል ከተባለ፣ ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች በምርጫው ውጤት ማምጣት ይችላሉ?
ስለ ሌሎቹ ፓርቲዎች ብዙ ማለት አልችልም፡፡ ሰማያዊ ግን የሚቻለውን ሁሉ እየጣረ ነው፤ ከነ አስቸጋሪ ሁኔታዎቹ ማለቴ ነው፡፡ ወጣት ሃይል ወደ ፖለቲካው እንዲገባ እያደረገ ነው፤ በውጪም በሀገር ውስጥም ያሉ ዜጐች ፖለቲካውን እንዲቀላቀሉ እየተጋ ነው፡፡ ግን ሀገሪቱ ካለችበት ሰፊ ችግር አንፃር “በቂ ነው ወይ?” ከተባለ፣ ጥርጥር የለውም በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት መንገዱን ይጠርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
የምርጫው ሂደት እናንተ በምትፈልጉት መንገድ ቢሆን፣ አሁን ባላችሁ አቋም የግንቦቱን ምርጫ የምታሸንፉ ይመስልዎታል?
ማሸነፍ ብቻ አይደለም፤ ያኔ ኢህአዴግ ያስመዘገበው 99.6 በመቶ ውጤት፣ ዞሮ እኛ ጋ እንደሚመጣ ነው የምናስበው፡፡ ምክንያቱም ምህዳሩ ከተከፈተ “ለኢህአዴግ ልቡን ሰጥቶ የሚመርጠው ማን ነው?” ተብሎ ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ሙስሊሙ፣ ክርክስቲያኑ፣ ወጣቱ፣ የተማረው ያልተማረው ፣ የመንግስት ሠራተኛው… የትኛው ነው የሚመርጠው? በእኔ እምነት የራሱም አባሎች ከዚህ በኋላ አይመርጡትም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የተሸነፈ ድርጅት ነው፡፡ መንገዱ ከተከፈተ ምንም ጥርጥር የለውም እናሸንፋለን፡፡ ለዚያም የሚሆን ነገር እንደ አቅማችን እየሠራን ነው፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ  የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረግ ውጪ ህብረተሰቡ ፖሊሲውን እንዲረዳለት ያከናወነው ሥራ አለ ብለው ያምናሉ?
የፖለቲካ ፓርቲ ሲኮን አንደኛ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት የተሳሳታቸውን ነገሮች እንዲያርምና ማሻሻያ እንዲያደርግ ግፊት የማድረግ ስራ ነው ያለው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ መንግስት ቢሆን የሚሠራውንና ያለውን አማራጭ ማቅረብ ነው፡፡ ሁለቱም ተለያይተው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ተቃውሞን አንዳንዶች እንደ መንቀፍና እንደ ማጥላላት ያዩታል፤ ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገሮች የመንግስትን ጉድለቶች የማስታወሻ ደንበኛ ስራ ነው፡፡ ፖሊሲውን ማስተዋወቅ በስፋት የሚሠራው በቃለ መጠይቅ፣ በስልጠና፣ በአዳራሽ ስብሰባዎች ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ  ፖሊሲውን በዚህ መልኩ አስተዋውቋል፡፡
በሁሉም ጉዳዮች ላይ ያሉንን ፖሊሲዎች ምሁራንን በሚገባ አወያይተናል፡፡ በፓርቲው ልሣን አስተዋውቀናል፡፡ ሁልጊዜ ቅዳሜ በፖሊሲያችን ላይ ውይይት አለን፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ፖሊሲያችንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው የብሔር ብሔረሰቦችን ሉአላዊነት የማይቀበሉ፣ የድሮ ስርአት ናፋቂዎች የሚለን፡፡ እንደውም እኛ የምንታማው የአይዲዮሎጂ ቀኖናዊነት ያጠቃቸዋል እየተባልን ነው፡፡
የፓርቲያችሁ ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
እኛ “ሞደሬት ሊበራሊዝም” የተሰኘ አይዲዮሎጂ ነው ያለን፡፡ በሂደት መንግስት ከኢኮኖሚ ውስጥ እየወጣ የሚሄድበት ፖሊሲን የሚያበረታታ ነው፡፡ መንግስት በሂደት ከኢኮኖሚው እጁን እየሰበሰበ ውስንነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲ ደግሞ መንግስት ሁሉን ነገር ይቆጣጠር የሚል ነው፡፡ በኛ ፖሊሲ መሬት የግል ይሆናል፣ ፌደራል ስርአቱ ዘርን መሠረት ያደረገ ብቻ ሳይሆን አኗኗርን፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የመሳሰሉትን መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ በፓርላማ አወቃቀር፣ የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤቶች እንዲሁም ሴኔት ይኖራሉ፤ የሚፈጠረው ስርአት ፕሬዚዳንታዊ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ብዙ ዝርዝር የፖሊሲ ጉዳዮች አሉን፡፡
ህዳር 7 ቀን ልታደርጉት በነበረው የአደባባይ ስብሰባ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንዴት ገባችሁ? በወቅቱ የተወዛገባችሁበት ጉዳይስ ምንድን ነው?
ሰልፍ ስናደርግ የደብዳቤ ምልልሱ ሁልጊዜም አለ፡፡ ወይ ቦታና ቀን ቀይሩ ይላሉ ወይ የፀጥታ ሃይል የለንም ይላሉ፡፡ እንዲህ ሲሉ እኛም መልሳችንን እንጽፋለን፡፡ አሣማኝ በሆነ መልኩ መልስ ከሰጡን ችግር የለብንም፤ ነገር ግን ደብዳቤውን ተቀብለው መልስ ካልሰጡን ማወቃቸው ብቻ በቂ ነው፡፡ ሌላ እወቁልን አትወቁልን የሚል ጣጣ ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡ ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ግን መብታችንን ስንጠቀም የሌላውን መብት እንዳንጐዳ የፀጥታ ሃይል መመደብ የመሳሰሉትን ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ከሆነ የሚያጣላን ሌላ ነገር የለም፡፡ መከልከል ከተፈለገ ግን ምንም ማድረግ ይቻላል፡፡
ኢህአዴግ የሃሰት ወንጀል እየፈበረከ የፓርቲ አመራሮችን በሚከስበት አገር፣ ሰማያዊ ፓርቲ ህግ ተላልፎ ምህረት ይደረግለታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፤ ወይ ኢህአዴግ ካልሆንን በስተቀር፡፡ እንደው “ሰባሁ እረዱኝ” አይነት ነገር ብናደርግ ምን ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ችግሩ ምንድን ነው? መንግስት እስከ መጨረሻው ቢሄድ የተለዋወጥነው ደብዳቤ ሃቁን ያወጣዋል፤ ያንን ስለሚያውቅ ነው እኛ እንደ ጀብደኛ እንድንታይ ከሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ ያለፈ እርምጃ ሳይወስድ የሚቀረው፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድስ በምን ምክንያት ነው የአደባባይ ስብሰባው ያልተካሄደው? ጥያቄያችን ተቀባይነት ቢያጣም ለስብሰባው ከመውጣት ወደ ኋላ አንልም ብላችሁም ነበር ..
ደብዳቤውን በፖስታ ቤት ላክን፣ የሚቀበለው አጣ፣ መልስም እኛ ጋ አልመጣም፡፡ እነሱ ጋ ስንሄድ ደርሶን በፖስታ ቤት መልሰነዋል አሉን፡፡ ሆኖም መልሰናል ያሉት ደብዳቤ ለኛ አልደረሰንም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ተቃውሞ መውጣት ተገቢ አይሆንም፡፡ ምንም አይነት ህጋዊ መሠረት የለንም ማለት ነው፤ ስለዚህ በመጣው ሰውም ሆነ በፓርቲዎቹ ላይ እርምጃ ቢወሰድ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ተከፍሎ ትግሉን ወደ ኋላ ሊመልሰው ይችላል፡፡
እኛ ዋጋ ስንከፍልም አንዲት ህጋዊ ልታደርገን የምትችል ነገር ይዘን ነው፡፡ ህጋዊ የሚያደርገንን ነገር ይዘን እንዳንወጣ ካሰብነው ቀን አሣልፈው በ22 ደብዳቤውን አምጥተውልናል፡፡ እሁድ ለማድረግ ለተጠየቀ ስብሰባ ሰኞ መልስ ተሰጠ ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራሲ አለ፣ ምርጫ አለ፣ እያለ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ላይ ሰው ተሰባስቦ መነጋገር ካልቻለ፣ ገጠር ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ በዚህ ሁኔታ ነጻ ምርጫ ይኖራልን? የሚለውን ጥያቄ ለህዝቡም ሆነ ለኢህአዴግ በተዘዋዋሪ መንገድ እያቀረብን መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢህአዴግን በዚህ መንገድ ማጋለጥም የተቃዋሚዎች አንዱ ስራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ዛሬ እና ነገ  ለሚደረገው የአዳር ስብሰባ ግን አስፈላጊውን ዝግጅት የጨረስን በመሆኑ ይካሄዳል፡፡
ጥያቄያችሁ ተቀባይነት አግኝቷል ማለት ነው?
ደብዳቤያችንን በፖስታ ቤት በኩል አድርሰናል፡፡ እንዲህ ያደረግነው መስተዳድሩ በአካል ደብዳቤ ይዘን ስንቀርብ ስለማይቀበል ነው፡፡ አሁን ደብዳቤው እንደደረሳቸው ከፖስታ ቤት ማረጋገጫ አግኝተናል፡፡ ደብዳቤው ከደረሳቸው ህጋዊ ነን ማለት ነው፡፡
ለደብዳቤያችሁ ምላሽ ተሰጥቷችኋል?
አዎ! መልስ ሰጥተውናል፤ እኛም የመልስ መልሱን ልከንላቸዋል፡፡
ምንድን ነው የተሠጣችሁ መልስ?
የመረጣችሁት አካባቢ ልማት የሚካሄድበት፣ የመንግስት ተቋማት የሚበዙበት ነው፤ አለማቀፍ ድርጅቶች አሉበት የሚል አስተያየት ሰጥተው “አልፈቀድንም፤ እውቅና አልሰጠንም” ብለዋል፡፡ እኛ ደግሞ አዋጁን ጠቅሰን “እውቅና መስጠት ያለ መስጠት የእናንተ ስልጣን አይደለም፡፡ ቀንና ቦታ ቀይሩ ማለት እንጂ እውቅና ሰጪ መሆን አትችሉም፤ በመንግስት ተቋማት ስለምታልፉ ለተባለው በመሠረቱ ሰልፍ የሚደረገው የመንግስት አካላት እንዲሰሙት ነው” ብለን መልስ ልከናል፡፡ “በታሰበው ጊዜና ቦታ ሰልፉንና ስብሰባውን እንደምናካሄድ አውቃችሁ፣ አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉልን” ብለን ጠይቀናቸዋል፡፡
የ24 ሰአት ሰልፍ እናደርጋለን ስትሉ ምን ማለት ነው?
እንግዲህ እስከ ዛሬ ብዙ ጮኸናል፤ ሰሚ አላገኘንም፡፡ አሁን ደግሞ ምርጫ ብላችሁናል፤ ምርጫ እንዲኖርም ሆነ ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲያገኙ ብርድ እየመታንም ጥያቄ እናቀርባለን፤ ስሙን የሚል አቤቱታ ለማሰማት ነው፡፡ ለሰአታት የምናደርገው ሰልፍ ውጤት ስላላመጣ እዚያው መስቀል አደባባይ አድረን፣ ብርድ እየመታን ድምፃችንን እናሰማለን፡፡ “የምናደርገው ስብሰባ ከዚህ ሰአት እስከዚህ ሰአት ነው፤ ከዚያ ውጪ ያለውን ሃላፊነት አንወስድም” ብለንም ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል፡፡
ምን ያህል ህዝብ ይገኛል ብላችሁ ነው የምትጠብቁት?
ከ100ሺ እስከ 150ሺ ህዝብ ይገኛል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ለመንግስት አካል ስናመለክትም ይሄን ሁሉ አካትተናል፡፡
ከዚህ በፊት ሰማያዊ ፓርቲ በጠራቸው ሰልፎች ላይ የተገኘው ከፍተኛ የተሳታፊ ቁጥር ስንት ነበር?
አንዳንዶች ከ70 ሺ እስከ 100 ሺ በማለት ዘግበውታል፡፡ ነገር ግን በ10 ሺዎች የሚገመቱ እንደተገኙ መገመት ይቻላል፡፡
እንዳሰባችሁት በ100 ሺ የሚቆጠር ህዝብ ቢመጣ የምግብ፣ የመፀዳጃና ሌሎች  አገልግሎቶች ተዘጋጅተዋል?
ሁሉም ሰው ቀለል ያሉ ደረቅ ምግቦችንና የታሸጉ ውሃዎችን በየግሉ ይዞ እንዲገኝ በመግለጫዎቻችን ስናስታውቅ ከርመናል፡፡ መፀዳጃ ቤትን በተመለከተ ሰው እዚያው ታግቶ ይውላል አልተባለም፡፡ ከስብሰባው እየወጣ አገልግሎት በሚገኙባቸው ቦታዎች ተጠቅሞ መመለስ ይችላል፡፡ ተጨማሪ ምግብና መጠጥ የሚፈልግም እንደዚያው ማድረግ ይችላል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በፀሎት ያስቡን--- ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
የኢትዮጵያ ህዝብ አማኝ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሃገራቸው ይፀልዩ ለማለት ነው እንጂ ፀሎት ተደርጐ ኢህአዴግ ይወርዳል ማለት አይደለም፡፡ አላማው የሰውን ልብና አዕምሮ ማግኘትና የውይይት አጀንዳ ማድረግ ነው፡፡ በየቤተክርስቲያኑ ወይም በየመስጊዱ ምህላ ይደረግ ለማለት አይደለም፡፡

Read 4989 times