Monday, 08 December 2014 14:24

ከሞትና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ? ቢሉት፤ ሲያስብ ዘገየ የወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

        ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት እጅግ በጣም ክፉ ሚስት የነበረችው ገበሬ ነበረ፣ ይባላል፡፡ ይህች ሚስቱ ማታ ከእርሻ ተመልሶ፣ ሞተር ቀንበሩን ሰቅሎ ገና እፎይ ሳይል እንዲህ ትለዋለች -
“መጣህ፤ በል ምግቡን አሙቀው”
“እሺ የእኔ እመቤት” ብሎ ፍቅሩን ጭምር ገልፆላት፣ወጡን ምድጃ ላይ ይጥዳል፡፡
“በል ና እግሬን ደህና አርገህ እንድታጥበኝ ውሃ አሙቅ”
“እሺ” ይልና ውሃውን ጥዶ ጣባውን ያቀርባል፡፡ ከዚያም ውሃው ሲሞቅ እግሯን ያጥባል፡፡
“በል እንጀራ ከመሶብ አውጣ፡፡ ወጡን በሳህን አቅርብ” ትለዋለች፡፡
“እሺ የእኔ ቆንጆ” ይላል፡፡ ይበላሉ፡፡
“ጀርባዬን በስብ እሽልኝ” ትለዋለች፡፡
ይሄንንም ያደርጋል፡፡
ጠዋት ቁርስ አቀራርቦ አልጋው ላይ እንዳለች ባፍ ባፏ ያጐርሳታል፡፡ ከዚያ ሞፈር ቀንበሩን አውርዶ፣ በሬዎቹን ጠምዶ ወደ እርሻው ይሄዳል፡፡
ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡
አንድ ቀን ባለቤቱ በድንገት ታመመች፡፡ ከላይ ከታች አጣደፋት፤ትኩሳቷ በረታ፡፡ ሌሊቱን አረፈች፡፡
አዝኖ አልቅሶ በሥርዓት አስቀበራት፡፡
ከባለቤቱ ሞት በኋላ ሚስት ሳያገባ ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡ በኋላ አገሬው ሸምግሎት ሌላ ሚስት እንዲያገባ ተደረገ፡፡
ይህቺኛዋ ሚስቱ የቀድሞዋ ሚስቱ ፍፁም ተቃራኒ ሆነች፡፡ ደግ የደግ መጨረሻ፤ ታዛዥ የታዛዥ መጨረሻ!!
“እግርሽን ልጠብሽ?”
“ምን ሲደረግ! እኔ ነኝ እንጂ እማጥብህ!”
“ምግብ ላቅርብ?”  
“ምን ሲደረግ እኔ የት ሄጄ!” ትላለች፡፡
“በይ ጀርባሽን ልሽሽ!”
“ምን ቆርጦህ እኔ ነኝ እንጂ የማሽልህ!”
ፍቅር በፍቅር ይሆናሉ፡፡
ይህ ገበሬ የዚችኛይቱ መልዐክነት በጣም ስሜቱን ነክቶት ጧት ማታ ትገርመዋለች፡፡
ታዲያ አንድ ማታ እሷ ቀድማው ተኝታለች፡፡
ፀሎቱን ሲፀልይ እንዲህ አለ፤
“አምላኬ ሆይ፤ ከዚች እጅግ ደግ ከሆነች ባለቤቴ የበለጠች የምትመጣ ከሆነ ምነው እቺም በሞተች!!”
***
Human wants are unlimited ይላል በኢኮኖሚ ንድፈ - ሀሳብ አኳያ ፋና - ወጊ ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ የሆነው  Adam Smith (አዳም ስሚዝ)፡፡ ሰው በቃኝ አያቅም እንደ ማለት ነው - ከላይ እንዳየነው ገበሬ፡፡ የመጨረሻውን ሀብት፣ የመጨረሻውን ፍቅር፣ የመጨረሻውን ረዥም ዕድሜ ቢሰጠው በቃኝ አለማለት የሰው ልጅ ጠቅላይ - ባህሪ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ የሚስገበገቡ፤ በመመዝበር፣ በመስረቅና በመሞሰን የተካኑ ሰዎችን ማሰብ ያስደነግጣል - ይብስም ያሰጋል!
ሮበርት ግሪን የተባለው ድንቅ ፀሐፊ እንዲህ ይለናል፡-
“አንዳች የሀገር ችግር ጠሎ ጠሎ bአንድ ነጠላ ጠንካራ ግለሰብ ምክንያት የመጣ ሊሆን ይችላle፡፡ ያ ግለሰብ ዋና በጥባጭ፣ ዋና ትዕቢተኛ፣ ዋናው መልካሙን ሁሉ መራዥ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሰዎች የመንቀሳቀስ ዕድል ከሰጠሃቸው ብዙዎች ተከታዮችና በእነሱ ተፅዕኖ ሥር የሚወድቁ ሰዎች ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡ በእነሱ አማካኝነት የሚባዛውንና የሚራባውን ችግር በጭራሽ ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፡፡ በጭራሽ መደራደር አያስፈልግም፡፡ የማይመለሱ፣ የማይቀለበሱ፣ የማይድኑ ናቸውና፡፡ በማራቅ ወይ በማጥፋት ብቻ ነው ተፅዕኗቸውን ማሟሸሽ ወይም መገላገል የሚቻለው፡፡ የችግሩን ሥረ መሰረት ፈልገህ ምታ፤ ከዚያ አጃቢው መንጋ ይበተናል”
እንዲህ ያሉ ሰዎች መናኸሪያ አንድም ቢሮክራሲው፣ አንድም ደግሞ የስልጣን መንበር ዙሪያ ነው፡፡ አንዱን አውራ በመፍራት አያሌ የተነካኩ ሰዎች እንዳይጠየቁ፣ እንዳይጋለጡ ማድረግ ይዘወተራል፡፡ ተጠያቂዎቹ ሰዎች ብጤዎቻቸውን በንፍቀ - ክበባቸው ስለሚኮለኩሉ የአይነኬነት ምህዋራቸውን ያሰፋሉ፡፡ ማንም እንዳይደርስባቸው አጥር ያጥራሉ፡፡ ይሄን አይነት የተተበተበ የወገናዊነት፣ የእከክልኝ ልከክልህ፣ “እኔ - እያለሁ - ማንም - አይነካህ”፣ “ማ - ባቀናው - አገር - ማን - ይኖራል?” የሚል ባህል ዋና የመሰንበቻ ሙስና ነው፡፡ ከመንጋው በፊት አውራውን ማግኘት ግድ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ የቢሮክራሲ መረብ ከአስተዳደር ብልሹነት እስከ ፖለቲካዊ ዝቅጠት መቀፍቀፊያ ኢንኩቤተር ነው፡፡ በዝምድና መስራት፣ በፖለቲካ መሞዳሞድ፣ ንፁህ መስሎ ባደባባይ መጮህ፣ የአስተሳሰብ ንቅዘት፣ በመፈክር የልብ ባዶነትን መሸፈን ወዘተ … ነቀርሳ - አከል የሀገራችን ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮች በዋሉ ባደሩ ቁጥር ማጎንቆላቸው አይቀሬ ነው፡፡ አልፈው ተርፈው መለመዳቸውና “ይሄ‘ኮ ያለ ነገር ነው!” መባላቸው በተደጋጋሚ የታየ ነገር ነው፡፡ በግለሰብ፣ በቡድን አሊያም በፓርቲ ደረጃ የዕብጠትና የማናለብኝ አባዜ ሌላው ያፈጠጠ ጦር ነው፡፡ ይህን ይዞ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ላይ ነኝ ማለት ቢያንስ ራስን ማሞኘት ነው - “እኔ ባልኩህ መንገድ ብቻ ሂድ - አለዛ …” እያሉ ዲሞክራሲ የለምና!
ሌላው አሳሳቢ ችግር በአንድ ምህዋር ላይ መሽከርከር ነው፡፡ ፎቶ - ካሜራ ዐይን ውስጥ ያለ ሰው እራሱን አያይም ይባላል፡፡ ከምህዋሩ ወጥቶ በአንድ ቅኝት የሚሽከረከረውን ሰው ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለውጥ ለማምጣት የአዘቦቱን ነገር መተውና በተለየ ዐይን ማየት (out of the box እንዲሉ) ያስፈልጋል፡፡ ከቶውንም ዐይናችንን ሳናሽ መፈፀም፣ በተግባር ማሳየት ያለብንን የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ የፍትሕ መጓደል ጉዳይ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነገ ዛሬ ማለት የሌለብንን የሙስናና የማጭበርበር ጉዳይ ለአፍታም ቢሆን ሳይዘገይ በግልፅ እርምጃ ወስደን ማሳየት አለብን፡፡ አለበለዚያ “ከሞትና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ?” ቢባል፤ ሲያስብ ዘገየ፤ እንደሚባለው ይሆናል!

Read 4674 times