Monday, 08 December 2014 14:30

የ“ነፃ ቀን” መዘዝ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ (ከጋምቤላ)
Rate this item
(0 votes)

በጋምቤላ ወጣቶች ዘንድ  ከሚወደዱና ከሚናፈቁ ቀናት መካከል ዋንኛው እለተ ሰንበት (እሁድ)  ነው፡፡ ጋምቤላዎች ቀኑን Free day እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ይህንን የነፃነት ቀናቸውን በነፃነት ለማሳለፍ የጋምቤላ ወንድና ሴት ወጣቶች አመሻሹ ላይ ወጣ ወጣ ይላሉ፡፡ ይሄ የሚፈቀድላቸው እድሜያቸው ከ15 አመት በላይ የሆኑ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡ በእድሜ የገፉ ሰዎችም ወደዚህ ስፍራ መሄድ  አይፈቀድላቸውም፡፡
ኒውላንድ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር  የሚገኘውና የጋምቤላ ወጣቶች free zone እያሉ በሚጠሩት ሆቴል ውስጥ ነፃ ጊዜያትን በነፃነት ያሳልፋሉ፡፡ ስፍራው የአልኮል መጠጥ እንደ ልብ የሚገኝበት ሲሆን የዚያኑ ያህልም ጥንቃቄ የጐደለው ወሲብ በስፋት የሚፈፀምበት ቦታ ነው፡፡ በfree zone ውስጥ የተገኘ (የተገኘች) ወጣት፤ ከአልኮል መጠጥ እስከ ወሲብ ግንኙነት ድረስ በነፃነት የመፈጸም “መብት” ተሰጥቷል፡፡ ይህንን መብትም የጋምቤላ ወላጆች በአግባቡ ያከብራሉ፡፡
በfree day ማንኛዋም የጋምቤላ ወጣት ከፈለገችው ወንድ ጋር የማምሸት፣ የመጠጣትና የግብረስጋ ግንኙነት የማድረግ መብት የተከበረ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ያነጋገርኩት ሉክ አንድሮ የተባለ የጋምቤላ ወጣት፤ወላጆች ወጣት ሴት ልጆቻቸው ወደ ፍሪ ዞን ሲሄዱ የሚያሰሙት አንዳችም ተቃውሞ የለም፡፡ እነሱም በጊዜያቸው ያለፉበት ህይወት ነውና አይቃወሟቸውም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶቹ የተለያዩ የአልኮል መጠጦችን ጠጥተው፣ ደንሰውና ተዝናንተው የወሲብ ግንኙነት ለማድረግ አጋርፋ ወደሚባል ጫካ ውስጥ ይሄዳሉ፡፡ አብዛኛዎቹም ኮንደም የመጠቀም ፍላጐት የላቸውም፡፡ ስለ ኤችአይቪ በሽታ ስርጭትና የመተላለፊያ መንገድ ቢያውቁም ለመጠቀም ፈቃደኛ አይደሉም ብሎኛል፡፡
ጐንደር፣ ወሎ ሰፈር፣ ባሮ ሜዳ፣ አቦቦ ማዞሪያ፣ ደምቦስኮ፣ አዲስ ሰፈር፣ መቱ ማዞሪያ፣ መላንጐ አራት ኪሎ፣ ባሮ አኮቦ፣ አጠና ተራና ጥጥ መዳመጫ እየተባሉ በሚጠሩት የከተማው ሰፈሮች ሁሉ ወጣቶች የእለተ ሰንበት ምሽትን እየጠበቁ free zone ወደሚኝበት ኒውላንድ ይተማሉ፡፡ ስፍራው ወጣቶቹ በነፃነት የፈለጋቸውን ሁሉ የሚያደርጉበት “ነፃ” ግዛታቸው ነውና፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ በክልሉ የኤችአይቪ ስርጭቱ  ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ በጋምቤላ ከተማ ለሚታየውና አሳሳቢ ለሆነው የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ዋንኛ ምክንያቶቹ፣ የክልሉ ባህል የሆነው የውርስ ጋብቻና ይህ በፍሪ ዴይ የሚፈፀመው ልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት እንደሆነም ባለስልጣናቱ ደጋግመው ገልጸዋል፡፡ የኤችአይቪ /ኤድስ ስርጭትን የመግታትና የመቆጣጠር ሃላፊነት ያለበት የክልሉ የጤና ቢሮ፣ ማህበረሰቡ እንዲሁም በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ ትኩረት በማድረግ የጋምቤላን ወጣት ትውልድ ሊታደጉት ይገባል፡፡

Read 4753 times