Monday, 08 December 2014 14:32

የኤችአይቪ/ኤድስ ምርመራ በጋምቤላ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

ከፍተኛ የኤችአይቪ ስርጭት ከሚታይባቸው የአገሪቱ ክልሎች ጋምቤላ ቀዳሚ ነው
በቂ ግንዛቤ ሳይፈጠር ምርመራው በዘመቻ መካሄዱን የሚተቹ ወገኖች አሉ
ለስምንት ሰዓታት በተደረገ ምርመራ 82 ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሰዎች ተገኝተዋል

        የዘንድሮ አለም አቀፍ የኤችአይቪ ቀን በብሔራዊ ደረጃ ወደሚከበርበት ጋምቤላ ክልል ከተጓዙት ሰዎች መካከል አንዷ በመሆን ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ ነበር በስፍራው የደረስኩት፡፡ ፀሐይዋ ገና በጠዋቱ አናት ትወቅራለች፡፡ በዓሉ የሚከበርበት የጋምቤላው ስቴዲዬም በህዝብ ተጨናንቆ ነበር፡፡ የዘንድሮውን የኤችአይቪ ቀን ከወትሮው በተለየ መልኩ ለማክበር እንደታሰበ ቀደም ብሎ ተነግሮናል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስምንት ሰዓት ውስጥ ለ2ሺ ሰዎች የምክርና የምርመራ አገልግሎት በመስጠት በ “ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ” የተዘመገበውን ሪከርድ የመስበር እቅድ እንዳለም እናውቅ ነበር፡፡  
ስቴዲየሙ ገና በማለዳው የተጥለቀለቀውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከየአካባቢው በመጡ በጐ ፈቃደኞች ተራቸውን እየጠበቁ እንዲስተናገዱ የሚደረጉት ነዋሪዎቹ፤ በስቴዲየሙ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ተገጥግጠው በተተከሉት የተባበሩት መንግስታት ድንኳኖች ውስጥ የሚሰጠውን የምክርና የምርመራ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡
አናት በሚበሳው የጋምቤላ ፀሐይ ለረዥም ሰዓት መሰለፍ እጅግ አድካሚ ቢሆንም የጋምቤላ ነዋሪዎች ግን አድርገውታል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁሉ ህዝብ እንዴት ሊሰባሰብ ቻለ ስል በሥፍራው ከነበሩት የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች አንዱን ጠየቅሁት፡፡ ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ መሠራቱን፣ ህዝቡ ተመርምሮ ራሱን ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳለውና ይህንኑ አገልግሎት በአቅራቢያው ማግኘቱ ደስ አሰኝቶት መውጣቱን ነገረኝ፡፡ የጋምቤላ ክልል የኤችአይቪኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካንጋትዋ እንደተናገሩትም፤ የጋምቤላ ክልል በኤችአይቪ ወረርሽኝ ከአገሪቱ ግንባር ቀደም መሆኑን የሚያመለክቱ ጥናቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ዘመቻው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለመለየትና በሽታው ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ያስችላል ብለዋል፡፡
ለምርመራ ከቆሙት ወጣቶች መሀል አለፍ አለፍ እያልኩ “እንዴት ልትመጡ ቻላችሁ?” እያልኩ ጠየቅሁ፡፡ በስፍራው ካገኘኋቸው ወጣቶች አብዛኛዎቹ “ቲ-ሸርትና ሣሙና ይሰጣችኋል ተብለን ነው የመጣነው” ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ስለ በሽታው ሁኔታ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ቢገኝ መውሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ያውቁ እንደሆነ ለመጠየቅ ሞከርኩ፡፡ ብዙዎቹ ቀና ምላሽ አልሰጡኝም፡፡ ያመጣቸው ዋና ጉዳይ ራስን አውቆና ተጠንቅቆ መኖር ተገቢ መሆኑን ተረድተውት ሳይሆን ይሰጣችኋል የተባለውን ቲ-ሸርትና ሣሙና ፍለጋ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ በእርግጥ አብዛኛዎቹ ተመርማሪዎች ምርመራቸውን አጠናቀው ቲ-ሸርቱን ካገኙ በኋላ ውጤታቸውን ሳይወስዱ ነው የሄዱት፡፡
ሕዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት የተጀመረው በካሜራ የታገዘ የኤችአይቪ ምርመራ እንደ ወላፈን በሚጋረፈው የቀትር ፀሐይም አልተቋረጠም ነበር፡፡ በረሃብና በውሃ ጥም የተዳከሙት በጐ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ሲተጉ ተመልክተናል፡፡ ታቅዶ የነበረውም ሪከርድ የመስበር ጉዳይ በከፍተኛ ውጤት ተሳክቷል፡፡ በእለቱ በስምንት ሰዓታት ውስጥ 3ሺ 383 ሰዎች የኤችአይቪ ኤድስ ምክርና ምርመራ አገልግሎት እንዳገኙ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ከተመረመሩት ውስጥም 82ቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
አገሪቱን በጊነስ ቡክ የማስመዝገቡ ዕቅድም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤትና በዩኤንኤድስ የጋራ ትብብር እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡ ከጊነስ ቡክ ጋር መነጋገር ቢፈልግም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በዘመቻ መልክ እየተካሄደ የሚገኘው የኤችአይቪ ኤድስ ምርመራ ያልታሰቡ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት 6.5 በመቶ ሲሆን ይሄም ከአጠቃላይ የአገሪቱ የኤችአይቪ ስርጭት ስድስት እጥፍ ያህል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ህብረተሰቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ሳይኖረውና የባህርይ ለውጥ ሳያመጣ በዘመቻ የሚካሄድ ምርመራ ተገቢ አይደለም ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ያለ በቂ ግንዛቤ የሚገለጽ የኤችአይቪ ምርመራ ውጤት ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸውን ሰዎች ለተለያዩ የበቀል እርምጃዎች የሚያነሳሳና በሽታውን በቀላሉ ለማሰራጨት ዕድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ሰዎቹ በቂ የሥነልቦና ዝግጅት ስለማይኖራቸው በራሳቸው ላይ የሚወስዱት እርምጃም አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ አሣካሁት የምትለውን የኤችአይቪ ስርጭት ቁጥጥርን ጥያቄ ውስጥ ሊከት እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ በተገኙበት በጋምቤላ ክልል የተጀመረው የኤችአይቪ ምክርና ምርመራ አገልግሎት ለአንድ ሳምንት ቀጥሎ በነገው እለት እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

Read 3147 times