Monday, 08 December 2014 14:34

“የአንጀት እንጂ የሰው ትርፍ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንዳንድ ጊዜ ሚኒባሶች ውስጥ ሰዉ ጣል የሚያደርጋቸው ነገሮች አይገርሟችሁም! ህዝቤ እኮ ‘ሳት እያለውም’…‘ሳት ያለው እያስመሰለም’ የልቡን ጣል ማድረግ እየተለመደ ነው፡፡ አገር ምን ይላል ለማለት ‘ሪሶሉሽን’፣ ወላ አቋም መግለጫ… ምናምን ነገር አያስፈልግም — በአዲስ አበባ ሚኒባሶች መጓዝ ይበቃላ!
በቀደም የሰማኋትን እናንተም ስሙኝማ…የታክሲው ረዳት ከተፈቀደው በላይ ተጨማሪ ሰዎች ማሳፈር ይፈልጋል፡፡ (አሁን፣ አሁንማ እንደ ሰጋቱራ ይጠቀጥቁን ጀምረዋል!) እናላችሁ…ረዳት ሆዬ ሾፌሩን “አንድ ትርፍ ሰው ልጨምር?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ሾፌሩ ምን አለ መሰላችሁ… “ዝም ብለህ ጫን፣ የአንጀት እንጂ የሰው ትርፍ የለውም፡፡” አሪፍ አባባል አይደለች!
እኛንም የቸገረን እንደ ‘ትርፍ’ መቆጠራችን ነው፡፡
‘ትርፍ’ ማለት ያው ‘ትርፍ’ ነው፡፡ ‘የከተማ ትርፍ ቤት’ አይነት ነገር፡፡
እናላችሁ…እኛንም የቸገረን እንደ ‘ትርፍ’ መቆጠራችን ነው፡፡
የምር እኮ ግርም የሚል ነው…ብዙ ቦታዎች ‘እንደ ትርፍ’ ትቆጠራላችሁ፡፡ ለምሳሌ እናንተ ቀድማችሁ መጥታችሁ አገልግሎት ማግኘት ሲገባችሁ… አለ አይደል…ሌሎች ‘ስታዲዮሙ ከተዘጋ በኋላ የደረሱ ሯጮች’ ሲስተናገዱ ‘እንደ ትርፍ’ ታይታችኋል ማለት ነው፡፡ እግረ መንገዴን… ይሄ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም…” ምናምን የሚለው ነገር ብዙ ቦታ አይሠራም፡፡ ዘንድሮ በየቦታው ከልጅ ልጅ ‘እንክት’ አድርጎ ይለያላ! አንደኛው ልጅ እንደ ትርፍ ይቆጠራላ! የአንጀት ብቻ ሳይሆን ‘የሰው ትርፍም’ ያለ የሚመስለን መአት ሰዎች አለና!
ከአንድ ከሁለት ወር በፊት አንድ ወዳጄ የሆነ ምርጦች (‘ዘ ሰሌክትድ ፊው’ እንዲል ፈረንጅ…) የሚበዙበት ሠርግ ላይ የግብዣ ወረቀት ደርሶት ወደዚያው እንደ አቅሙ ሽክ ብሎ ይሄዳል፡፡
እናላችሁ… የፈለገ ቂቅ ቢባል.. አለ አይደል… የፈለገ የሎሽን አይነት ብንለቀለቅ ‘ዓመዳችን በትንሹም ቡን’ ማለቷ አይቀርም አይደል… መግቢያ በር ላይ የእሱም ‘ዓመድ’ ትንሽ ቡን ብላ አሳበቀችበት መሰለኝ… ከአስተናጋጆቹ አንደኛው የጥሪ ወረቀቱን አገላብጦ ካየ በኋላ እሱንም ‘አገላብጦ’ ያየዋል፡፡ በዚህ መሀል ‘ዘ ሴሌክትድ ፊው’ ከሚባሉት የተወሰኑ ሲመጡ ‘መንገድ እንዲለቅ’… አለ አይደል… ‘ገፋ’ ይደረጋል፡፡ (ገፋ በመደረግ ቢያልፍልን ደህና…የቸገረን እኮ ጭራሽ ከመንገዱ ተስፈንጥረን እንድንወጣ መደረጉ!) እናላችሁ…ደስ ሳይላቸው አስገቡት… ትርፍ ነዋ!
እኛንም የቸገረን እንደ ‘ትርፍ’ መቆጠራችን ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሚኒ ባስ ውስጥ ከረዳቶቹ ጋር ያለው ክርክርም ‘የትርፍነት’ ነገር አለበት፡፡ እናንተ ‘ተራ ዜጎች’ ከሆናችሁ የመንጓጠጡ፣ የመዘለፉ ነገር ለብቻ ነው፡፡ “ታክሲውን የገዛኸው መሰለህ!”  “ከፈለግሽ ውረጅና በሀይገር ሂጂ…”  ምናምን የተለመዱ ናቸው፡ ረዳቶቹ በተዘዋዋሪ እንደ ትርፍ ነገር ያደርጉናላ! እኛም (የፈለገ “ፈሪ ፈራና እጉድባ ቢተኛ…” ምናምን ተብሎ ይዘፈንብን እንጂ…) ረዳቶቹ ወደ ‘ፕላቲኒየም’ ደረጃ ስድብ እንዳይሸጋገሩ… “አይ ጊዜ፣ የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል…” ምናምን እየተረተን፣ “ዝም አይነቅዝም…” እያልን ጭጭ ነው፡፡
እናላችሁ…በዚሀ መሀል ግን “ዋ! ታርፍ እንደሁ እረፍ! በኋላ እንዳታለቅስ! የዳቦ ቆሎ ሊጥ ነው የማስመስልህ…” አይነት ነገር የሚል ሰው ብቅ ሲል… አለ አይደል… “ማን በዓይኑ ሙሉ አይቶኝ!” አይነት ነገር ሲያደርገው የነበረው ረዳት ኩምሽሽ ብሎ፣ ምን አለፋችሁ… መርፌ መሰኪያ ደም ስር እንኳን በፍለጋ የማይገኝበት ሆኖ ቁጭ! ተናጋሪው ‘ትርፍ ሰው’ ላይሆን ይችላላ! ‘የዘመኑ ሰው’ ሊሆን ይችላላ!
ስሙኝማ…ለጠቅላላ እውቀት ያህል…‘የዘመኑ ሰው’ የሚባል አገላለጽ አለላችሁ፡፡ በቃ የዘመኑ ሰው ነው ከሚለው ዓ/ነገር በስተጀርባ የዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ገጽ የልብ ወለድና የኢ—ልብወለድ ትረካ ስላለ አደብ እንገዛለን! (በቀድሞ ጊዜ… “አንተ ሰውዬ፣ አርፈህ ልጆችህን ማሳደግ አትፈልግም!” ይባል እንደ ነበረው ማለት ነው፡፡) ሀሳብ አለን…እኛ ዘንድ ‘የዘመኑ ሰው’ ስንል የሚኻኤል ሌርሞንቶብ ድርሰት የሆነው ‘የዘመናችን ሰው’ አይነት ማለታችን ስላልሆነና በአፍሪካም፣ በዓለም ‘የመጀመሪያው’ መሆኑ ታውቆ (ቂ…ቂ...ቂ…) ታውቆ  በ‘ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ’ ይስፈርልንማ፡፡ እናላችሁ…“ቀጪም ተቆጪም የለውም እንዴ የሚያሰኝ ሰው ሲገጥመን በጥቅሻም፣ በሹክሹክታም “የዘመኑ ሰው ሳይሆን አይቀርም… አይነት ነገር መባባላችን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ‘ታሪካዊ ሀቅ’ ይሆናል፡፡
(የታሪክ ነገር ሲነሳ፣ ወዳጄ… “እኚህ ሰው በዘንድሮው ምርጫ ይወዳደራሉ እንዴ?” ተብሎ ተጠየቀ ያልከኝ ነገር እንደተመቸኝ ነገር!)
እባብ ዘለግለጋ እግር የለው እጅ
ጊዜ የጣለው ሰው የለውም ወዳጅ
የሚሏት ነገር አለች፡፡ ልጄ… ጊዜ ከሚጥልስ ጠጅ ቢጥል ይሻላል! ጊዜ ከጣለ በቃ ጣለ ነዋ!
እናማ… ጊዜ አይጣለን! አንደ ጊዜ በጀርባ ከተንጋለሉ በኋላ… ታሪክ የለ፣ “በአምስቱ ዓመት ወረራ ሚስቴን፣ ድስቴን ሳልል…” ምናምን ብሎ ነገር የለ… “ወታደሮቹን ከአራት ኪሎ ለማስወጣት ወጣትነቴን ከፍዬ…” ምናምን ብሎ ኦቶባዮግራፊ የለ… “የሰፈሩን ዕድር ለሠላሳ ዓመት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳልል ሳገለግል ኖሬ…” ምናምን ብሎ ነገር የለ… ብቻ ጊዜ አይጣላችሁ፡፡
እናማ…ጠጅ ጥሎ ካስተኛ በእንቅልፍና በ‘ሹሮ ፍትፍት’ ማባበል ይቻላል…ጊዜ ካስተኛ ግን፣ በቃ ‘አስተኛ’ ነው! “ሁሉም ዜሮ፣ ዜሮ…” ያኔ ነው፣፡ እናላችሁ… ጊዜ ከጣለ… አለ አይደል…  ‘የዲስኩር አፍ መፍቻ’ መሆን ነው፡፡ አበው…
ሌሊት ከጭቃ ላይ ፈረስ ቢጥልህ
ወንድሜ አትናደድ ማንም አላየህ
ይልቁን ተጠንቀቅ ቀን እንዳይጥልህ፣
ሲሉ የነበረው ጊዜ በጣለው ላይ የሚወርደውን ናዳ ስለሚያወቁ ነው፡፡
በሰዎች ነገር ምንስ አግብቶኝ
እኔስ ብርቅ ነው የሚሻለኝ
ኋላ ሊስቁ ቀን ሲጥለኝ
ተብሎ ተዚሟል፡፡ ቀን ሲጥል ምን እንደሚኮን ይታወቃላ!  ታሪካችን ውስጥ ሊረሱ የማይገባቸው ሥራዎች ሠርተው ‘ቀን ጥሏቸው’… አለ አይደል… ‘የማርያም ጠላት’ አይነት ነገር የሆኑ ምስኪኖች አይተናላ! የወጡበት መሰላል ቁልቁልም እንደሚያወርድ ረስተው…ኋላ ላይ ‘ቀን ዘጭ’ ሲያደርጋቸው አይተናላ! ካዝናው የማይመናመን፣ ጎተራው የማይቀንስ እየመሰላቸው ኋላ ላይ ‘ቀን ዘጭ’ ሲያደርጋቸው ዕጣ ፈንታቸውን አይተናላ! ብቻ…ቀን አይጣላችሁማ!
እናማ… “የአንጀት እንጂ የሰው ትርፍ የለውም፣” አሪፍ አባባል ነች፡፡ እኛ ዘንድ ስትመጣ ‘ሎካል ከለር’ እየተሰጣት የተገላቢጦሽ ሆነች እንጂ!
የምር እንግዲህ…ጨዋታም አይደል…በዚህ ‘ሰለጠነ’ በተባለ ዘመን (“መስታወት ህንጻዎች የስልጣኔ ‘ብቃት ማረጋገጫ’ በመሰሉበት ዘመን…” ማለትም ይቻላል…) ሰው ከሰው የማበላለጥ፣ አንዱን ‘ዋና’ አንዱን ‘ትርፍ’ አድርጎ የማየት…አይነት ነገሮች ስታዩ ታዝናላችሁ፡፡ ልክ ነዋ…አብዛኞቻችን ወይ በስልጣን፣ ወይ በሀብት ደረጃ፣ ወይ በ‘ቦተሊካ’ አመለካከት፣ ወይ በትምህርት ደረጃ፣ ወይ በ‘አገር ልጅነት’…ምናምን ሰውን ‘ዋና’ እና ‘ትርፍ’ አድርገን የመመልከት ደዌ ይዞናል፡፡ (“ቢሆንም፣ ባይሆንም ፌጦ መድኃኒት ነው…” የሚል ‘ፈዋሽ’ ይላክልንማ!) አለ አይደል…አፍ አውጥተን “አንተ እኮ ትርፍ ነህ…”  ምናምን አንበል እንጂ አመለካከታችንና ብዙ ጊዜም ተግባራችን አንዳንድ ሰዎችን እንደ ‘ትርፍ’ እንደምናያቸው ያሳብቁብናል፡፡ ሰዎችን ‘እንደ ትርፍ’ ከማየት ‘ትርፍ’ አስተሳሰብ ይሰውረንማ!
ከ‘ዋናነት’ ወደ ‘ትርፍነት’ ከመውረድም ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3156 times