Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 11:08

ኢህአዴግ ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን እያጣቀሰ ነው ያለው ማነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሁለት ምርጫዎች ወግ” ደራሲ አጓጊ ልቦለድ ይፃፉልን

ኢህአዴግን እንኳን ከ”ናዳ” አተረፈህ እንበለው!

ቦታው አሜሪካ ነው፡፡ በሴፕቴምበሩ 9/11 አሸባሪዎች በፔንታጐን ላይ አሰቃቂ ጥቃት ሰንዝረው በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጐች ከሞቱ በኋላ የቻይና ጠ/ሚኒስትር ፕሬዚዳንት ቡሽን ለማፅናናት ስልክ ይደውላሉ፡፡ “ሚስተር ቡሽ፤ በደረሰው ጥቃት በጣም አዝኛለሁ፡፡ በጣም ትልቅ አሳዛኝ አደጋ ነው፡፡ ምናልባት   ከፔንታጐን ሰነዶች ከጠፉባችሁ ግን እኛ ጋ የሁሉም ኮፒዎች (ቅጂዎች) ስላሉ ሃሳብ እንዳይገባዎ”

አያችሁልኝ የቻይናን ነገር… የታላቋ ሃያል አገር አሜሪካ ወታደራዊ ሰነዶች በሙሉ ፎቶ ኮፒ ተደርገው እጄ ገብተዋል ነው የምትለው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ የአሜሪካ የጥናትና ምርምር ተቋም ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ የቻይና መንግስት በ600 የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ስለላ ማካሄዱ ተገልጿል፡፡ ቻይናዎት የስለላ ሊቅ ናቸው እንበል ይሆን?  እኔ የምለው ግን  ስለላ “ሽብርተኝነት” ነው ወይስ አይደለም? የህግ ባለሙያ ትንተና የሚሻ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር በቻይና የሚገኙ የቆንስላ ፅ/ቤቶቹን ቁጥር ወደ 3 ከፍ ማድረጉን አንብቤአለሁ፡፡ ነገሩ ክፋት የለውም፡፡ የቆንስላ ፅ/ቤቶቹን ወጪ የሚሸፍነው ግን ማነው? የቻይና መንግስት ስፖንሰር ቢያደርገው አሪፍ ነበር፡፡  አሁን ወደ አገራችን ገበና እንግባ፡፡ ትዝ ይላችኋል… የ97 ምርጫ ሰሞን! ፡፡ ያኔ እንኳን ከምርጫው በኋላ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቲቪ መስኮት ብቅ ብለው ለተቃዋሚዎች (ደጋፊዎችንም ይመለከታል) የሰጡትን ዱላ-አከል ማስጠንቀቂያ ማለቴ  ነው፡፡ “የውጭ አገር መንግስታት አያድኗችሁም!” ነበር ያሉት፡፡ ደንበኛ የአባት ቁጣ እኮ ነው የሚመስለው! ለነገሩ መንግስት አባት ነው ይባል የለ! “ፈጣሪ” ነው የሚሉም አሉ (እነዚህ የባሰባቸው ናቸው) እና… በማስጠንቀቂያው መጨረሻ ላይም ጠ/ሚኒስትሩ “ህጋዊነትና ህገወጥነትን እያጣቀሱ መቀጠል አይቻልም!” የሚል ብርቱ ማሳሰቢያ ለተቃዋሚዎች አስተላልፈው ነበር፡፡ ይሄን ማስጠንቀቂያ በወቅቱ የኢህአዴግ ደጋፊ ባልሆንም (አሁንም አይደለሁም!) በ”መርህ” ደረጃ ደግፌው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለምን ደገፍከው አትሉኝም? አያችሁ ወይ በህጋዊነት አሊያም በህገወጥነት መስመር ለይቶ ያልተሰለፈ ወገን ለአመራር ወይም ለአንዳንድ አይመችም፡፡ ህጋዊ ሲሉት ህገወጥ፤ ህገወጥ ነው ሲባል ህጋዊ እየሆነ (በጠ/ሚኒስትሩ አገላለፅ “እያጣቀሰ”) ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ መስመሩን ለይቶ መቆም ወይም መሰለፍ አለበት፡፡ በዚህ አቋም ነበር የያኔውን የምርጫ ማግስት ማስጠንቀቂያ የደገፍኩት፡፡ ዛሬ ግን ያችኑ አባባል ለኢህአዴግ ልጠቀምበት የሚያስገድደኝ ሁነኛ ጉዳይ ገጠመኝ፡፡ (አደራችሁን! ኢህአዴግን  የእጁን ነው ያገኘው ብላችሁ እንዳታበሽቁብኝ)  የኢህአዴግ የነጭ ካፒታሊዝም ተከታይነት የማይዋጥላቸው አንዳንድ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች “ኢህአዴግ ካፒታሊስት መንግሥት ከሚሆን ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይሻላል” እያሉ በተደጋጋሚ አሰልችተውኝ ነበር፡፡ (እንግዲህ በነሱ ቤት  ካፒታሊዝምና ፅድቅ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች!) በፊት በፊት ራሱ ኢህአዴግ የነፃ ገበያ ሥርዓት እንደሚከተል በአደባባይ እየለፈፈ የምን “ከጳጳሱ የበለጠ ካቶሊክ” ልሁን ባይነት ነው በሚል እሞግታቸው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የኢህአዴግ ነገረ ስራ አላምር አለኝና ዝምታን መረጥኩኝ፡፡ በተለይ የአዳማው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች እንደ ደርግ ዘመን “ጓድ… ኮምሬድ” ሲባባሉ ሰምቼ ውስጤ ቀርታ የነበረችው እንጥፍጣፊ ተስፋ ተሟጠጠች፡፡ በጉባኤው አዳራሽ አጠር አጠር ያሉ ቻይናዎች ውር ውር ሲሉ ያየሁ ጊዜማ “ተበላን!” ነበር ያልኩት - በሆዴ! (በቻይናዎች አይደለም የምንበላው፡፡ በደርግ ዘመን በምናውቀው “ሰው በላው” የሶሻሊዝም ሥርዓት ነው እንጂ!)

ሰሞኑን በኢህአዴግ ላይ የሰማሁት ሃሜት ደግሞ ለየት ያለ ነው፡፡ “ኢህአዴግ ካፒታሊዝምን እያጣቀሰ ነው” ብለው ሲያሙት ሰምቻለሁ፡፡ እኔ በሆዴ ምን አልኳቸው መሰላችሁ? “ውዥንብር ፊጣሪዎች!” (የኢህአዴግ ካድሬዎችስ ከዚህ በላይ ምን ሊሉ ይችላሉ?) ለማንኛውም ግን ይህችን ሃሜት ማጥራት አለብን የሚል ቁርጠኛ አቋም ይዣለሁ፡፡ ለምን … አትሉም? ላለፉት 20 ዓመታት የገዛን (የመራን) አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ ለመጪዎቹ 40 ዓመታትም አብረን እንዘልቃለን እያለን እኮ ነው! እናም   “ገዢው ፓርቲያችን የካፒታሊዝም ሥርዓት ተከታይ ነው ወይስ የሶሻሊዝም?” የሚለውን ማጥራት እንደ “አካሄድ” የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ ምናልባት እኮ ኢህአዴግ ከየትኛው ወገን እንደሆነ (ከካፒታሊዝምና ሶሻሊዝም) ገና አልወሰነ ይሆናል! ለነገሩ ምን  አስቸኮለው… ገና ድፍን 30 አመት ይጠብቀው የለም እንዴ? (ምን ለማለት እንደፈለኩ ላጥራላችሁ አይደል…) አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ሳላሰልፍ ብቀር ኢህአዴግ አይደለሁም ብሎ ሲምል አልሰማችሁትም? ለዚህ እቅዱ ደሞ የ40 ዓመት   የሥልጣን ጥያቄ ማመልከቻ ለህዝቡ አስገብቷል፡፡ እናንተዬ… የምን ሥልጣን ነው የማወራው፡፡ አጀንዳዬ እኮ ፈፅሞ ከስልጣን ጋር የሚገናኝ አልነበረም፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… የኔ አጀንዳ “ኢህአዴግ ካፒታሊስት ነው ሶሻሊስት?” የሚል ብቻ ነው፡፡

ምናልባት ከጀርባሀ ማን ቢኖር ነው ይሄን ጥያቄ ያነሳኸው? የሚለኝ “አክራሪ ካድሬ”  ካለ ምላሼ ምን መሰላችሁ … “ኢህአዴግ ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን እያጣቀሰ ነው” የሚል ሃሜት ስለሰማሁ ተቆርቁሬ እንጂ እንኳን ከጀርባዬ ከጐኔም ማንም የለ… ብዬ እምልለታለሁ፡፡ በእርግጥ ከ”ላይ” ኢህአዴግ እንዳለ አልክድም፡፡ ሰማይ ላይ ሳይሆን ሥልጣን ላይ፡፡ ከጀርባዬ ግን እንዳልኳችሁ ፈፅሞ ማንም የለም፡፡ ተቃዋሚ፣ የኒዮሊበራል አቀንቃኝ፣ የአብዮት ቀለም አራማጆች፣ “አሸባሪዎች” ወዘተ ማናቸውም ከጀርባዬ የሉም፡፡

አንድ ጥያቄ ላቅርብና ወደ ቀጣዩ አጀንዳዬ ልውሰዳችሁ፡፡ ጥያቄው ለፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደሆነ ይታወቅልኝ! (ለፈረንጆቹ ማለቴ ነው) “ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን እያጣቀሱ አገር መምራት ይቻላል እንዴ?” (ጠ/ሚኒስትሩ ህጋዊነትና ህገወጥነትን እያጣቀሱ መቀጠል አይቻልም ማለታቸውን ልብ ይሏል!) ለነገሩ ጊዜ የላቸውም  ብዬ እንጂ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ቢመልሱት በማን እድሌ ነበር፡፡

የሃሜቱ ነገር ይብቃንና በመረጃ ወደተደገፈ ጉዳይ እናምራ፡፡ ባለፈው ሳምንት አቶ በረከት ስምኦን ስለፃፉት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሃፍ ስናወጋ አንድ ነገር ዘንግቻለሁ፡፡ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግን “እንኳን ከ97ቱ ናዳ አተረፈህ!” አላልኩትም፡፡ የፈለገ የፓርቲው ደጋፊ ባልሆን ናዳን ከሚያህል አስከፊና አሰቃቂ አደጋ በተአምር ሳይሆን በሩጫ ነፍሱን ያተረፈውን ኢህአዴግ፤ “እንኳን ተረፍክልን” ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እንዴ… ፓርቲው የተረፈው እኮ ከመኪና ግጭት ሳይሆን ከናዳ ነው! በርግጥ ናዳው የተራራ ይሁን የካባ፣ የፎቅ ይሁን የሌላ … የታወቀ ነገር የለም፡፡ ብቻ   እንኳን ተረፈ፡፡ ትንሽ ግራ ያጋባኝ ኢህአዴግ ከናዳ ለመትረፍ የሮጥኩት ብቻዬን አይደለም፤ ህዝቡንም ነው ያሯሯጥኩት ማለቱ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በዓመት አንዴ ህዝቡ የሚሮጠው “ለታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ” (Great Run) ብቻ ነው፡፡ ወይስ  ሌላ የማናውቀው ህዝብ አለ? (የህዝብ definition ይነገረን!!)

ሌላም “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የሚለውን በምርጫ 97 እና 2002 ዙሪያ የሚያጠነጥን መፅሃፍ ዳግም እንዳነሳ ያደረገኝ ሁነኛ ምክንያት አለ፡፡ አቶ በረከት የ97ቱ ምርጫ ካስከተለው አደገኛ ናዳ ለማምለጥ አገራዊ ሩጫ አድርገው እፎይ ሲሉ መፅሃፋቸው የትችት ናዳ ይዞባቸው መጣ ብዬ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት በመፅሃፉ ላይ የቀረበ ዳሰሳ (review) ግን መፅሃፉ የትችት ናዳ ብቻ ሳይሆን የውዳሴ ናዳም እንደወረደበት አሳይቶኛል፡፡ በርግጥ ዳሰሳውን ያቀረቡት ፀሃፊ ትንሽ ግራ አጋብተውኛል፡፡ በአገሪቱ ታሪካዊ ክስተት የሚባለውን (በተለይ) የ97 ምርጫን የሚተርክ የፖለቲካ መፅሃፍን በጥበብ መነፅር ለምን ሊቃኙት (ሊመዝኑት) እንደመረጡ አልገባኝም፡፡ አቶ በረከትም ቢሆኑ ለጥበብ ሳይሆን ለሀቅ (ለታሪክ) ብለው እንደፃፉት  ነው የገባኝ፡፡ (መቼም የመፅሃፉ ገምጋሚ የፈጠራ ሥራ መስሏቸው እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡) በዚህች አጋጣሚ ግን ከጥበብ አፍቃሪ ወዳጆቼ ለአቶ በረከት የቀረበ ጥያቄ ባቀርብ ደስ ይለኛል፡፡  አቶ በረከት ጊዜ ሲያገኙ አጓጊ ልቦለድ (novel) ይፃፉልን የሚል ቅን ጥያቄ ነው፡፡ ወጋችንን ዘና በሚያደርግ ቀልድ እንደጀመርን ሁሉ በተመሳሳይ ስሜት እንድናጠናቅቅ ከነአውዳመት ምርቃቱ (bonus) ሁለት ቀልዶች እነሆ በረከት፡፡ መልካም የገና በዓል!!

***

አንድ መንግስታዊ መ/ቤት ነው፡፡ ከ1ሺ ያነሱ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ብዙዎቹ ግን በአንድ ወይም በሌላ የወንጀል ተግባር ስማቸው የቅሌት መዝገብ ውስጥ የሰፈረ ነው፡፡ እኔ የወንጀላቸውን አይነትና ብዛታቸውን እስከምነግራችሁ እናንተ የትኛው አገርና የማን መ/ቤት እንደሆነ ገምቱ (ሽልማት ግን የለውም!)

29ኙ የትዳር አጋራቸውን በማሰቃየት ተከሰዋል፡7ቱ በማጭበርበር በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

19ኙ ባዶ ቼክ በመፃፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

117ቱ ቢያንስ ሁለት የንግድ ኩባንያዎችን ለኪሳራ ዳርገዋል፡፡

3ቱ በግድያ ወንጀል ተይዘዋል፡፡

71ዱ በእዳ በመዘፈቃቸው ክሬዲት ካርድ ማግኘት አይችሉም፡፡

14ቱ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ በተመሰረተባቸው ክስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

8ቱ ከገበያ መደብር እቃ በመስረቅ ተይዘዋል፡፡

21ዱ በፍ/ቤት የተመሰረተባቸውን ክስ በአሁኑ ሰዓት እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡

በ1998 ዓ.ም ብቻ 84ቱ ጠጥተው መኪና ሲያሽከረክሩ ተይዘው ነበር፡፡

የትኛው አገር ውስጥ የሚገኝ መ/ቤት እንደሆነ ገመታችሁ? እስከ አሁን ካላወቃችሁት እኔ ልንገራችሁ፡፡ አገሪቱ የማርና የወተት መፍለቂያ የምንላት አሜሪካ ስትሆን መ/ቤቱ ደግሞ 535 አባላትን ያቀፈው የአሜሪካ ኮንግረስ (ም/ቤት) ነው፡፡ ይሄን መረጃ በኢንተርኔት ላይ ያቀረበው ግለሰብ ወይም ተቋም “ይሄው የኮንግረስ ቡድን ነው ቀሪዎቻችን በደንብና በሥርዓት እንድንመራ ህግ እያረቀቀ የሚያወጣልን” ሲል አሸሙሯል፡፡ ይሄ እንግዲህ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና በደንብ የተዋቀሩ ዲሞክራሲያዊ  የመንግስታት ተቋማት ባላት አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡ እንደኛ ባሉ እጅግ ወደኋላ በቀሩ የአፍሪካ አገራት ነገሩ የቱን ያህል የከፋ እንደሚሆን አስቡት፡፡ ለጊዜው ግን ክፉ ክፉውን ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ሌላ ዘና የሚያደርግ ጨዋታ ላካፍላችሁ፡፡ (አውዳመት እኮ ነው!)

ሰውየው ኒውዮርክ፣ ሴንትራል ፓርክ ውስጥ ዎክ እያደረገ ሳለ አንድ ውሻ አንዲት ትንሽ ልጅን ሲነክሳት ይመለከታል፡፡ ሮጦ ይሄድና ከውሻው ጋር ታግሎ በመግደል የልጅቷን ህይወት ይታደጋታል፡፡ ትእይንቱን ቆሞ ሲመለከት የነበረ ፖሊስ ወደ ሰውየው ጠጋ ይልና “ጀግና ነህ፤ ነገ ይሄን ጀግንነትህን በየጋዜጦቹ ላይ ታነበዋለህ” ይለዋል፡፡ እውነትም በነጋታው የእሱን የጀግንነት ተግባር ያልዘገበ ጋዜጣ አልነበረም፡፡ አንዱ ጋዜጣ “ጀግናው የኒውዮርክ ተወላጅ የትንሿን ልጅ ህይወት ታደጋት” ሲል ፃፈ፡፡ ሰውየው ርእሱን ካነበበ በኋላ “እኔ ግን የኒውዮርክ ተወላጅ አይደለሁም” አለው ለፖሊሱ፡፡

“ግዴለም የነገው ጋዜጣ ላይ ያስተካክሉታል” ሲል አፅናናው ፖሊሱ፡፡

በቀጣዩ ቀን ጋዜጣ ላይ ዘገባው ተስተካክሏል፡፡ “ጀግናው አሜሪካዊ የትንሿን ልጅ ህይወት ታደጋት”

ሰውየው ርዕሱን ካነበበ በኋላ “እኔ እኮ አሜሪካዊ አይደለሁም” አለው ለፖሊሱ፡፡

“ምንድነህ ታዲያ?”

“ፓኪስታናዊ ነኝ!”

በዕለቱ የምሽት ጋዜጣ ላይ እንዲህ የሚል ዘገባ ወጣ፡-

“አክራሪው ሰላማዊውን የአሜሪካ ውሻ ገደለ”

(ሚዛናዊ ካልሆነ ዘገባ ይሰውረን!)

 

 

 

Read 2336 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:18