Saturday, 13 December 2014 10:24

300 ኢትዮጵያውን በየቀኑ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ይያዛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

         በየቀኑ በአማካይ ወደ 300 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአፋር በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር ለመውጣት ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ተገለፀ፡፡ ሰሞኑን 70 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ የመን ባህር ዳርቻ ላይ ህይወታቸው ማለፉ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡
ከትናንት በስቲያ የክርስቲያን በጐ አድራጐት ማህበራት ጥምረት (CRDA) አስተባባሪነት በተዘጋጀ የአንድ ቀን ጉባኤ ላይ የአፋር ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተወካይ አቶ መሃመድ አንበሳ እንዳመለከቱት፤ በየቀኑ በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት የሚሞክሩ ወደ 300 የሚጠጉ ስደተኞች እየተያዙ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉትን ስደተኞች ለመመገብና የሎጅስቲክ ድጋፍ ለማድረግ ፖሊስ መቸገሩን ተናግረዋል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለእነዚህ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አስተዳደር የፍትህ ፖሊሲ ፕላኒንግና አተገባበር ሚኒስትር ዴኤታና ከሳውዲ ተመላሾች አቀባበል ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፤ የዜጎች ለስራና ለተለያዩ ጉዳዮች ከሃገር መውጣት በየትኛውም ሃገር ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጡ  ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚቻለውን ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ስደትን ለመቀነስ የስራ እድል ፈጠራን ማስፋትና አመለካከትን መቀየር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፈው አመት ከሳኡዲ  አረቢያ የተመለሱትን ኢትዮጵያዊያን በማረጋጋት በኩል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥሩ የሰሩ ቢሆንም የውጪ ሃገር ተስፈኝነት አመለካከትን በመቀየርና ስደተኞችን በማቋቋም ረገድ የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
መንግስት ህገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ የተለያዩ ሰራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ህጋዊ ጉዞን ለመጀመር የሚያስችለው ህግ የመጨረሻው ረቂቅ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በጉባኤው ላይ በቀረቡ ጥናቶች፤ በአሁን ሰአት የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር በሰሜንና በደቡብ ወሎ እየቀነሰ ቢሆንም ከሰሜን ሸዋ አካባቢ ያለው ፍልሰት የመጨመር አዝማሚያ ይታይበታል ተብሏል፡፡ በመድረኩ ላይ የአለማቀፉ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ያስጠናው ጥናት የቀረበ ሲሆን በጥናቱም  በህጋዊ መንገድ ከሃገር ከሚወጡት ዜጎች ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ የወጡት በእጥፍ እንደሚበልጡ ተመልክቷል፡፡ ባለፈው አመት ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ 170ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መካከል አሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰው የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አይኤልኦ ባስጠናው ጥናት ተጠቁሟል፡፡ አብዛኞቹ ተወላጆች በሀገሪቱ ሰርቶ መለወጥ የሚያስችል ነገር መኖሩን ቢያምኑም ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ድጋፍ ይጠብቃሉ ተብሏል፡፡ ከሳውዲ ሲመለሱ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተገባላቸው ቃል ተስፈኛ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ በአሁን ሰዓት አብዛኛዎቹ ተመላሾች ስልጠና የተሰጣቸው ቢሆንም በስኬታማ የስራ መስክ ላይ የሚገኙት አነስተኛ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የመጡት አቶ አደላሁ ፈንቴ፤ ከሳኡዲ አረቢያ ከተመለሱት ኢትዮጵያውን መካከል ወደ 43 ሺ 625 ገደማ የሚሆኑት የአማራ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ ስልጠና ወስደው ወደ ተለያዩ ስራዎች የገቡት ወደ 16 ሺህ ገደማ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ክልሉ ካሰበው አንፃር ወደ ስራ የተሰማሩት ቁጥራቸው ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ፤ በቀጣይ ወደ 40 ሺ የሚጠጉትን ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ አይኤልኦ ያስጠናው ጥናት፤ ወደ አረብ ሃገራት ለመጓዝ የሚሹ ዜጎች በተናጥል ለህገ ወጥ ደላሎች የሚያወጡትን ወጪም ይጠቅሳል፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡት ከትግራይ ክልል የሚጓዙት ሲሆን በነፍስ ወከፍ እስከ 22 ሺ ብር ገደማ ለመጓጓዣና ለደላላ ያወጣሉ፣ ከደቡብ አካባቢ የሚጓዙት ወደ 21 ሺ ብር፣ ከአማራ ክልል ወደ 19 ሺህ፣ ከኦሮሚያ ክልል የሚጓዙት ወደ 17 ሺህ ብር እንዲሁም ከአዲስ አበባ መነሻቸውን አድርገው የሚጓዙ ወደ 12 ሺህ ገደማ እንደሚያወጡ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጓዦች የገንዘብ ምንጫቸው ብድር ነው ይላል ጥናቱ፡፡ የተቀሩት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሃብት በመሸጥ የሚጓዙ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ወደ አረብ ሃገራት ሲጓዙም የሚያጋጥማቸው ትልቁ ችግር የቋንቋ ችግር ሲሆን ከተጓዦቹ ከ70 በመቶ በላይ የዚህ ችግር ሰለባ ይሆናሉ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን በህገ ወጥ መንገድ ወደ የመን ሊገቡ ሲሉ ባህር ላይ ከሞቱት ኢትዮጵያውያን መካከል የሃያ አንዱ አስክሬን መገኘቱን ዴይሊ ሜል የዘገበ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአደጋው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡

Read 3611 times