Saturday, 13 December 2014 10:23

ከ80 በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ለ5 ቀን ታስረው ተፈቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

ድብደባና እንግልት ተፈፅሞብናል ብለዋል
           ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ብጥብጥና ሁከት ለማስነሳት ከህግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ “የፓርቲዎች ትብብር” አመራርና አባላት ከትናንት በስቲያ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ፤ የግንቦቱን ምርጫ ለማስተጓጐል በህገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡
የትብብሩ አመራርና አባላት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንደጠየቀባቸው የሚታወቅ ሲሆን ከቀጠሮው በፊት ከእስር እንደተለቀቁ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ  የተለቀቁት የፓርቲዎች አመራርና አባላት ከ80 በላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከእስር የተለቀቁት አብዛኞቹ የፓርቲው አባላት በደረሰባቸው ድብደባ ወገባቸው ላይ መጐዳታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከትናንት በስቲያ ምሽት በህክምና ተቋማት የአልትራሳውንድ ምርመራ እንደተደረገላቸውና በተለይ ሴቶቹ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ 52 የሚደርሱ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች አመራሮች መደብደባቸውን እንዳረጋገጡ አቶ ዮናታን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹ ሰኞ ዕለት ፍ/ቤት ሲቀርቡ መደብደባቸውን ለፍ/ቤት እንዳመለከቱ የጠቆሙት ሃላፊው፤ ፍ/ቤቱ ድብደባው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቆ በተገቢው መንገድ ይያዙ የሚል ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የፓርቲዎቹ አመራሮች እስሩንና ድብደባውን በመቃወም የረሃብ አድማ አድርገው እንደነበርም ታውቋል፡፡
ቅዳሜ ረፋድ ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ከሚገኝበት እንደራሴ ሆቴል አካባቢ 150 ሜትር ያህል እንደወጡ፣ ከኋላም ከፊትም በደህንነት ኃይሎች ተከበው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ ሌሎቹም ከመስቀል አደባባይ አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ባለፈው አርብ ህዳር 26 ምሽት “የተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ የለም” የሚል መግለጫ በቴሉቪዥን ከሰጠ በኋላ እንዴት ከሰልፍ ልትወጡ ቻላችሁ? ስንል የጠየቅናቸው፣ ኃላፊው፤ የተሰጠው መግለጫ ህግን የጣሰ በመሆኑ ህግን ለማስከበር ነው የወጣነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም፣ ህገ-ወጥ ሰልፍ ያደረጉ ጥቂት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ በህገወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀ ሲሆን ግለሰቦቹ ህገወጥ ሰልፍ ለማድረግ ከመሞከራቸውም በላይ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ትንኮሳ ፈፅመዋል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ህዳር 29 በአሶሳ ከተማ በተከበረው 9ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ መንግስታቸው የግንቦቱን ምርጫ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሻዕቢያና ተላላኪዎቹን እንዲሁም ህገ ወጥነትን የሚያጣቅሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ለማምከን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ ትብብር የፈጠሩት ፓርቲዎች ሰማያዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያውን አንድነት ድርጅት፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሶዶ ጎርደና ህዝብ ዲሞክራሲዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ የኦሞ ህዝቦች ኮንግረስና የጌዴኦ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሲሆኑ ምርጫ ቦርድ ለትብብሩ ዕውቅና አልሰጠሁም ብሏል፡፡
 የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል የአንድ ወር የተቃውሞ ፕሮግራም አውጥቶ በየሳምንቱ የተቃውሞ ስብሰባ ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም አንዱንም ለማሳካት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

Read 4269 times