Saturday, 13 December 2014 10:27

ፒያሳ የመንገድ ላይ “ፖፖ” አቅርባለች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(59 votes)

ወጣቶች በ”አንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” አልመዋል

     በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ስር የሚገኘውና በተለምዶ “አላሙዲን ያጠረው” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ለአመታት በሽንት፣ በሰገራና በመጥፎ ሽታ ተበክሎ ብዙዎችን ለበሽታ ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለትና ሶስት ወራት ወዲህ ግን አካባቢው በመጠኑም ቢሆን እየተለወጠ መጥቷል፡፡
ፒያሳ  መንገድ ላይ ለሚሸኑ መንገደኞች ፖፖ በማቅረብ “እናንተ ወደ ፖፖው ካልሄዳችሁ፣ ፖፖው ወደ እናንተ ይምጣ” የሚል ሽሙጥ የጀመረች ትመስላለች፡፡
ቸርነት መኮንን ይባላል፤ ውሎውን ፒያሳ ካደረገ ረዘም ያለ ጊዜ እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ ፒያሳ ያልሞላ ታክሲ እስኪሞላ ሰዎችን በመጥራት፣ ዕቃ በመሸከምና ሌሎች ስራዎችን እየሰራ ኑሮውን ሲገፋ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ከእለት ወደ እለት የአካባቢው መቆሸሽና መጥፎ ጠረን መባባስ ለስራም ሆነ ለጤና እክል እንደሆነባቸው ይናገራል - ለእሱና ለጓደኞቹ፡፡ እናም በመንገድ ላይ መሽናትና ለመከላከል መላ ዘየዱ፡፡
“ሃሳቡን ያመነጩት ታሪኩና ሙራድ የተባሉ ጓደኞቻችን ናቸው፤ ስምንት ሆነን እንሞክረው በሚል ተስማማን” ይላል ቸርነት፡፡ ከዚያም ሃሳቡን ይዘው ወደ ወረዳ አንድ ፅ/ቤት መሄዳቸውን ገልፆ፤ ህገ-ወጥ መኪና አጣቢዎች ለውሃ መቅጃ ይጠቀሙበት የነበረውንና  ቀበሌው በህገ-ወጥነት የወረሰውን የተወሰኑ ጀሪካኖች እንደሰጣቸው፣ እነሱም አዋጥተው ተጨማሪ ጀሪካን መግዛታቸውን ይናገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት 15 ጀሪካኖችን ለአላፊ አግዳሚው በማቅረብ አካባቢው ላይ ሽንት እንዳይሸና መከላከል በመቻላቸው ከዚያ መጥፎ ጠረን እፎይታ መገኘቱን ቸርነት ገልጿል፡፡ በአካባቢው አራት ቦታ ላይ ሶስት ሶስት ጀሪካኖችን ደርድረው ያስቀምጣሉ፡፡ 25 ሊትር ውሃ የሚይዘው ጀሪካንም አንገት አንገቱ ተቆርጦና ክፍት ሆኖ ወገቡ ላይ በቀይ ቀለም “ሽንት መሽናት ይቻላል” የሚል ፅሁፍ ተፅፎበታል፡፡ ጀሪካኖቹ የተቀመጡበት የቆርቆሮ አጥር ላይ ደግሞ “እባካችሁ ጀሪካኑ ላይ በመሽናት ተባበሩን” የሚል ተማፅኖ አከል ማስታወቂያ ይታያል፡፡
“መቼም እንደ ስራ ከቆጠርነው አይቀር ብለን 50 ሳንቲምም አንድ ብርም ክፈሉ እንላለን፤ የሌለውን ግን አናስጨንቅም፤ ፍላጐታችን አካባቢው ንፁህ ሆኖ እኛም በሰላም ውለን እንድናመሽ ነው” የሚለው ወጣት ቸርነት፤ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያስፈራሯቸው፤ ማነህ ምንድነህ የሚሏቸው እንዲሁም ሊደበድቧቸው የሚጋበዙ፣ አንዳንዴም እላያቸው ላይ ሊሸኑ የሚቃጣቸው ሰዎች እንደሚያጋጥማቸው ይናገራል፡፡ “ይሁን እንጂ አላማ ይዘን እስከተነሳን ድረስ ሁሉንም በትእግስት እናልፋለን” የሚለው ወጣቱ፤ አንዳንድ ስልጣን አለን የሚሉ ግለሰቦችና ሊያግዙን የሚገባቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ሳይቀሩ ሥራችንን ያውኩብናል ብሏል፡፡
“በተቃራኒው ስራችንና ሞራላችን አስደስቷቸው 10 ብርም አምስት ብርም ሰጥተው አበረታተውን የሚሄዱ አሉ” ያለው ቸርነት፣ በዚህ ሁሉ መሃል መጠነኛ ለውጥ እያመጡ መሆናቸው እንደሚያስደስታቸው አጫውቶኛል፡፡ በአካባቢው አበባ በመትከል፣ ውሃ እየገዙና እየተሸከሙ በማጠጣት አካባቢውን ንፁህና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረትም ወጣቱ አሳይቶኛል፡፡የክልል ከተሞች መንገድ ላይ ሶፍትና የማስቲካ ወረቀት መጣል አቁመው በዘመኑበት ወቅት የአፍሪካ መዲና የምትባለው ከተማ፤ እንዲህ መቆሸሿና የሚያቆሽሿትም በአብዛኛው አውቆ አጥፊዎች መሆናቸው እንደሚያሳዝነው ጠቅሶ፤ አንዳንዱ ሰው ጀሪካን ላይ ሸንቶ ክፈል ሲባል ለአንድ ብርና ለ50 ሳንቲም ደረሰኝ ሲጠይቀን ሳቃችን ይመጣል ብሏል፡፡
ስራውን እውቅና አግኝታችሁ ለመስራትና ራሳችሁን ከአንዳንድ ህገ-ወጦች ጥቃት ለመጠበቅ ለምን ከወረዳው ድጋፍ አትጠይቁም? በማለት ላነሳሁላቸው ጥያቄ ወጣቶቹ ሲመልሱ፤ በቀጣይ ተደራጅተው፣ የደንብ ልብስና መታወቂያ ኖሯቸው፣ ወረዳውም የዋጋ ተመን አውጥቶላቸው ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡
ወጣት ሃዱሽ ወርቅነህ በዚህ ስራ ላይ ከተሰማሩት ስምንቱ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ፒያሳን መዋያው ካደረገ ሰባት አመታት እንደተቆጠሩና ስራውን አምኖበት እንደሚሰራው፣ ሽናት ተሸክሞ በመድፋቱም የሚሰማው ነገር እንደሌለ ይናገራል፡፡ “በዋናነት የምንሰራው ስራ አለን፤ ከሰራን አይቀር ደግሞ ሳንቲም እናግኝ ብለን እንጂ ትኩረታችን አካባቢውን ማፅዳት ነው” ይላል፡፡ ስራው ፈተና ቢኖረውም ተስፋ በመቁረጥ ወደ ኋላ እንደማይሉ የገለፀው ወጣት ሃዲሽ፤ ጀሪካን ሙሉ ሽንት ተሸክሞ ቱቦ ውስጥ ሲደፋ የሚጠየፉት፣ የሚያላግጡበትና የሚያሽሟጥጡት ቢኖሩም እሱ ግን በስራውና በአካባቢው መፅዳት ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማው በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡
በቀን ምን ያህል ገቢ ታገኛላችሁ? ስል የጠየቅኩት ወጣት ሃዱሽ፤ “ገና ስራውን እንደጀመርን ጥሩ ገቢ ነበረን፤ ቢያንስ ዙሪያውን 12 ጀሪካን አስቀምጠን፣ በቀን እስከ 300 ብር ገቢ እናገኝ ነበር፤ አሁን አሁን ግን ሰው ከእኛ ጋር እየተላመደ ከሚከፍለው የማይከፍለው እየበዛ፤ ገቢው ቢቀንስም እኛ ግን አካባቢውን ለማፅዳት ያለን ቁርጠኝነት አልቀነሰም” ብሏል፡፡ ሽንቱን የምትደፉበት ቱቦ ሌላ ብክለት አይፈጥርም ወይ ስል ተጨማሪ ጥያቄ አነሳሁበት፡፡ ቱቦው ሰፊና በደንብ የሚያወርድ ከመሆኑም በላይ  ሽንቱ ከተደፋ በኋላ፣ ውሃ ስለሚለቀቅበት ለብክለት እንደማይጋለጥ ወጣቱ ያስረዳል፡፡
በአካባቢው የተከሏቸውን አበቦች ሲኮተኩት ያገኘሁት ሌላው የቡድኑ አባል ሙራድ፤ “ቀን ቀን መንገድ ላይ መሽናት ቀርቷል፤ ምክንያቱም በየቀኑ አንድ ሰው ተራ እየገባ ዙሪያውን ይጠብቃል” ብሏል፡፡
“መንገድ ላይ እሸናለሁ፤ አትሸናም” በሚል በተፈጠረ ሙግትም በአንድ ግለሰብ መፈንከቱን ሙራድ ነግሮኛል፡፡ ወጣቶቹ መጀመርያ ላይ ቀበሌው እንዳገዛቸው ባይክዱም ተገቢውን ትኩረት አልሰጠንም ይላሉ፡፡ እንደ ታክሲ ተራ አስከባሪ፣ የደንብ ልብስ፣ መታወቂያና ሌሎች መለያዎች ቢዘጋጅልን ጥሩ ነው፤ እያገዝን ያለነው እኮ መንግስትን ነው ይላሉ - ወጣቶቹ፡፡
ቀደም ሲል ተንቀሳቃሽ የወንዶች መጸዳጃ ቤት እንደነበረው የሚናገረው አንድ የአካባቢው ነጋዴ፣ እኔ ጋ 50 ሳንቲም ላለመክፈል ከጎኔ አጥር ስር የሚሸኑ መንገደኞች ነበሩ፤ በዚህ የተነሳ መረረኝና ዘጋሁት ብሏል፡፡ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ “ወጣቶቹ እየሰሩ ያሉት ጊዜያዊ ስራ የሚያመጣው ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፤ መንግስት ዘላቂ መፍትሄና የአመለካከት ለውጥ ላይ አተኩሮ መስራት አለበት” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ጽ/ቤት  ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል ተብለን ወጣቶቹን በማገዝ፣ ዘላቂ መፍትሄ በማምጣትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ወደ ጽ/ቤቱ ብንመላለስም “ስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ አንዳንድ ያነጋገርናቸው የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ግን ጉዳዩ በቀጥታ አይመለከተንም ብለዋል፡፡ “ከተማዋ ከአፈጣጠሯ የታቀደ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የላትም፤ በዚያ ላይ አካባቢው መጠጥ የሚዘወተርበትና የብዙ ቦታዎች መነሻና መድረሻ በመሆኑ ችግሩን ከፅ/ቤቱ አቅም በላይ አድርጎታል” ባይ ናቸው - የፅህፈት ቤቱ ሠራተኞች፡፡
እስከመቼ እንደሚዘልቅ መገመት ቢያዳግትም እስከ ጊዜውም ቢሆን የአካባቢው ንፅህና ጉዳይ በስምንቱ ወጣቶች ትከሻ ላይ ያረፈ ይመስላል፡፡ ገንዘብ የሌላቸው አገልግሎቱን ለማግኘት ክፈሉ እንደማይባሉ የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ ነገር ግን ቢያንስ ህብረተሰቡ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶና ጥረታችንን በቅንነት ተመልክቶ ጀሪካን ላይ ቢሸና፣ አንዳንድ ግለሰቦችም ሊተናኮሉን ባይሞክሩ እስካሁን ከታየው የላቀ ለውጥ ለማምጣት እንችላለን ብለዋል  - ወረዳው ከለላ እንዲሰጣቸው በመማፀን፡፡  


Read 12895 times