Saturday, 13 December 2014 10:38

የተቀመጠች ወፍ ሆዷን ስትዳብስ የበረረች ወፍ አፏን ትዳብሳለች

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንዲት ቀበጥ ልጅ ከእናቷና ከሴት አያቷ ጋር አብራ ትኖር ነበር፡፡ ከቀበጥነቷም በላይ የሥራ ዳተኝነቷ አስቸጋሪ ነበር፡፡
እናትና አያት ይወያያሉ፡-
አያት - እንደው የዚችን ልጅ ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?
እናት - እረ እኔም ከዛሬ ነገ እጠይቅሻለሁ እያልኩ ስፈራ ስቸርኮ ነው የቆየሁት፡፡ የአያት አንጀት ሆኖብሽ ስለምታቆላብሻት እንዳትቀየሚ ብዬ ታገስኩ፡፡
አያት - እረ የምን ቅያሜ ነው እሱ?
እናት - እንግዲያው ለምን ቁጭ አድርገን ነገረ-ስራዋ ሁሉ እንዳልጣመንና ከእንግዲህ ቤቷን ቤቴ ብላ በስነ ሥርዓት እንድትኖር እናስጠንቅቃት፡፡
አያት - አዎ፤ መቼም የሙት ልጅ ናትና አባቷ ከሞተ ወዲህ ሀዘኗም ብስጭቷም በዝቶቦታል ብለን ብዙ ታገስናት፡፡ አሁን ግን በዛ!
እናት - መብዛት ብቻ! ተንዛዛች እንጂ! ምግብ በልታ ውልቅ! ጠዋት የወጣች አገሩን ስታካልል ውላ መምጣት! እራቷን በልታ ክልትው!
አያት  አዲስ ሀሳብ አመጡ:-
“ቆይ እስቲ ዛሬ መቼም አዕምሮ አላት፡፡ ታስብበትና ወደ ቀልቧ ትመለስ ይሆናል”
እናት - ምን አድርገሽ ቀልብ እንዲኖራት ታደርጊያታለሽ?
ምን እናድርግ ትያለሽ?
አያት - ወደ አልጋዋ እንጠጋና ወለሉን እኔ ልጥረግ እኔ ልጥረግ እያልን እንጣላ፡፡ ለመጥረግ እንታገል፡፡ ስትነቃ ተዉት እኔ እጠርጋለሁ በማለት ይሉኝታ ይይዛትና ትነሳለች፡፡
እናት - በጣም ድንቅ ሃሳብ! በይ ነይ እንሂድ፡፡
እናትና አያት እንደተባባሉት፤ አንድ መጥረጊያ ለሁለት ይዘው፤
አያት - ተይ ዛሬ እኔ ነኝ የምጠርገው?
እናት - ምን ሲደረግ!? አንቺ አርፈሽ ቁጭ በይ!
አያት - አብደሻል ስንት ዘመን አንቺ ልትጠርጊ ነበርኮ?
እናት - አይሆንም አልኩ አይሆንም!
ትግሉ ቀጠለና ልጅቱ ነቃች፡፡
ከአልጋዋ ቀና አለችና፤
“ለምን ትረብሹኛላችሁ? ቤቱን ለመጥረግ ይሄን ያህል ትግል ምን ያስፈልጋል? አንዳችሁ ዛሬ ጥረጉ፤ አንዳችሁ ደግሞ ነገ ጥረጉ” ብላ ተመልሳ ተኛች፡፡
***
የሥራ ሥነምግባር መሰረቱ ግብረገብነት ነው፡፡ ለእናት ለአባት መታዘዝ ነው! ጥቃቅኖቹን ትዕዛዛት በማክበር ማደግ የእድገትን ቁልፍ መጨበጥ ነው፡፡
“አጓጉል ትውልድ
ያባቱን መቃብር ይንድ”
የሚባለው በዋዛ አይደለም፡፡ በጥንቱ ዘመን “ያልተቀጣ” “አሳዳጊ የበደለው!” የሚል ስድብና እርግማን ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ በምርቃትም ደረጃ “ትምህርትህን ይግለጥልህ!” ማለት የምርቃት ሁሉ ምርቃት ነው፡፡ ከወላጅ ማክበር ወደ መምህር ማክበር፤ ከዚያም ወደ አለቃ ማክበር ማደግ፤ ለአንድ ወጣት ትውልድ ትልቅ እሴት ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች የሀገር ባህል አይናቄ መሰረቶች ናቸው፡፡ የግብረገብነት ባህል ሲያዩት ወይም ሲያወሩት ቀላል፤ ሲመረምሩት ግን ጥልቅ ነገር ነው፡፡ የትምህርት ባህል፣ የሥራ ባህል፣ የአስተዳደር ባህል፣ የፖለቲካ ባህል፣ የኮሙኒኬሽን ባህል፣ የውይይት ባህል፣ የመቻቻል ባህል… የሁሉ ነገር መሰረት ናቸው፡፡
ዴቪድ ቦህም የተባለ ፀሀፊ፡-
“…በውይይት ሂደት መንቃት በተካፋዮቹ በተሳታፊዎቹ መካከል የሚፈጠር የትርጉም መረዳዳት ፍሰት ነው፡፡ በመጀመሪያ ተሳታፊው ሁሉ የየግሉን አቋም/ጐራ ይይዝና ይሄን ብለቅ ሞቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ እያደር ግን ከየግል ደረቅ አቋም ይልቅ የወዳጅነት ስሜት የበለጠ እንደሚሆን እየታየ ይመጣል፡፡ ምንም አይነት የወዳጅነት ቀረቤታ ሳይኖር መግባባት ብቻ ድንቅ ባህሪ ይሆናል…” ይለናል፡፡
አንዳችም ልዩና መሰረታዊ ዓላማ ከጀርባው ሳይኖር ወዳጅነትን መፍጠር መባረክ ነው፡፡ ለሀገር ለወገን የሚበጅ እፁብ ነገር ነው፡፡ ስብዕና፣ ዕውቀት፣ ምጥቀተ-ህሊና፣ የጋራ-ቤትን ማፍቀር፤ መሰረታዊ መነሻዎችና ማደጊያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ከመሰረት ከንጣፉ እኒህን ጉዳዮች ማወቅና መገንዘብ መቻሉ ደርዝ ያለው ነገር ነው፡፡ መተሳሰብ፤ መወያየት፣ ማንበብና መናበብ፣ በሥርዓት መኖር፤ የጋራ ምጥቀተ-ህሊና (Consciousness) ያስፈልገዋል - የሀገራዊነት መሰረቱ ይሄው ነውና!
ወጣቱን ሳይዙ ጉዞ ምን ተይዞ ጉዞ ነው፡፡ ወጣቱ ሲባል ደግሞ ለትምህርት ዝግጁ የሆነው፣ ለመንቃት የሚተጋው ራሱን ምንጊዜም ለመለወጥ የሚታትረው፣ አርቆ ማስተዋል ጐዳና ላይ ያለው ነው፡፡ በእርግጥ አገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ካለብን ከቤተሰብ አስተዳደግ፣ ከትምህርት ቤት መታነፅ፣ ለአካለ - ሥራ መብቃት ጋር የተሳሰረ ወጣት ይዘን መሄድ ይኖርብናል፡፡
የዕውር የድንብር አለመሄድ ትልቁ ጥበብ ነው፡፡ ወጣቱ ህይወትን የሚቃኝበት ኮምፓስ ያሻዋል፡፡ ሌሎችን የሚማርክበት ማግኔት ያለው እንዲሆንም እንጠብቃለን፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን መረጃ - የለሽ ትውልድ እንዳይፈጠር ሁሉም ዜጋ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይገባል፡፡
የጥበብ ዐይኑ የተከፈተ ወጣት የበለፀገ ዕይታ ይኖረዋል፡፡ በኪነጥበብ እንዲጠነክር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በቅጡ ማወቅ የአንድ ህብረተሰብ የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለዕለት - እንጀራ መፈለጊያ የሚበቃ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ምሉዕነት ያለው የዕውቀት ቀንዲል ለመጨበጥ እንዲነሳሳ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡
እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተባሉ የአገራችን ደራሲ ስለአቴናውያን ሲፅፉ፤ “እሊህ አቴናውያን የነበራቸው አዲስ ነገር ለመስማትና ለመናገር መጓጓት ንጹሕ ሰብዓዊ ስሜት ነው፡፡ ወደፊት ለመራመድ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በማናቸውም የአውሮፓ ሥልጣኔ ክፍሎች ዘንድ የነሱን ማህተም ያልተሸከመ ነገር አይገኝም፡፡ ጫፉን ለመጥቀስ ያህል በሳይንስ ረገድ እነ ዲሞክሪቶስ እስከ አቶምፊዚክስ ድረስ የደረሱ ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ረገድ እስከ ዲሞክራሲ የደረሱ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ የሥልጣኔ ሀብታት መገኛ ለመሆን የቻሉት በንጹህ ሰብዓዊ ጠባይ እየተመሩ አዲሱን ነገር በመመኘት ስለዚያም በመናገርና በመስማት ነው” ይሉናል፡፡ አዲስ ነገር ለማየት የሚጓጓ ትውልድ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ማለት ግን መነሻውን፣ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ የዕውቀት ውርሱን በመመርመር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ “ማናቸውም የህሊና ተግባር በህገ - ምክንያት የተመሠረተ (Causalities) መሆን አለበት” ይሉናል የጠቀስናቸው ፀሐፊ፡፡
ብርሃናማ ነገ እንዲኖር ዛሬ ብርሃናማ ትውልድ የሚወራረሰው የጽሑፍም ሆነ የአፈ - ንግርት ቅርስ እንዲያፈራ፤ ምሁራን በተለይም ፀሐፍት የወጣቱን ዐይን ሊከፍቱለት ይገባል -በዚህ ረገድ የራሳቸውን መክፈልት ሊከፍሉ ይገባል፡፡ እንዲያው በደፈናው ትውልድን መራገም ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ሃዋርያና ደቀመዝሙር መሆን አለባቸውና፡፡ ተቀምጠን ከምናላዝን ተንቀሳቅሰን ለነገ ለውጥ እናምጣ ነው ጉዳዩ! “የተቀመጠች ወፍ ሆዷን ስትዳብስ የበረረች ወፍ አፏን ትዳብሳለች” ማለት ይሄው ነው፡፡  

Read 5081 times