Friday, 06 January 2012 11:23

ዛር እና አዶ-ከበሬ በዘፈን ሲከበር

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

ዕለቱ በዓለ-ልደት ነውና ስለወልድ እግዚአብሔር ማውጋቱ የተለመደ ነው፡፡ “ገና በሙክቱ፣ ሁዳዴም በሕልበቱ ይታወቃል” ይባል እንጂ አንዳንዴ እንደውም “ገና-ገና” በሚለው የመገናኛ ብዙሃን ወግ እና ዘፈን ነው የሚታወቀው፤ ሙክት ድሮ በመቅረቱ፡፡ዛሬ-በበዓለ-ልደተ-ክርስቶስ ዋዜማ የማጫውታችሁ ያልጠበቃችሁት እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ በዚች ቅድስት አገር ስለ ቅድስና ላይ-ታች ማለት የወግ በመሆኑ ገድሉ የሚሸፋፈን ነገር የለውም፡፡ ድብቁ - ምስጢሩ በተቃራኒው ያለው አገልግሎት ከእነሥነ-ሥርዓቱ ነው፡፡ የዛር፣ የአዶበሬ እና የልድ ልዩ መናፍስቱ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ትውፊታዊ ሐብቱን እንኳን ለማጥናት የደፈረ ምሁር አላጋጠመኝም፡፡

ብቻ ሟቹ ፀሐፌ ተውኔት ፍስሃ በላይ ይማም የካቲት መፅሔት ላይ ሁለት ተከታታይ መጣጥፎችን አቅርቦ ማስነበቡ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ዛሬ ቀኑ አይደለም ካላላችሁ በስተቀር ስለዚሁ ድብቅና ምስጢር ጉዳይ ጥቂት እንጨዋወት፡፡ የጨዋታችንን ቅጥ-አንባር ለማስጠበቅ ለመናፍስቱ ከሚቀርቡ መስዋዕቶች ውስጥ “ዘፈንን” ብቻ መሰረት አድርገን እንቀጥላለን፡፡እንደግንባረ ቦቃ በግ፣ እንደ ጥቁር ዶሮ፣ እንደ ሽቶና ቂጣ ሁሉ ዘፈንም የዛር፣ የአዶከበሬና የልዩ-ልዩ መናፍስት ግብር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተስፋፍቶ፣ ተንሰራፍቶ ለነበረው የልዩ ልዩ መናፍስት አምልኮ በዜማና በግጥማቸው ረቂቅነት የሚታይባቸው ዘፈኖች መስዋዕት ይቀርቡ ነበር፡፡ አዲስና ድብቅ የሚሆነው ምናልባት ለዚህ ዘመን ትውልድ ብቻ ነው፡፡ታስታውሱ እንደሆን በዚያ ሰሞን አውሊያና ከራማ አለብኝ ለሚለው ለታምራት ገለታ ሁለት ዘፈኖች እንደተቀነቀኑ ሲጠቆም አገር ሁሉ በግርምት አፉን ይዞ ቀርቷል፡፡ ፍርሃትም ታይቶበታል፡፡ የህዝቡ ድንጋጤ ግልፅ ነበር፡፡ ዘፈኖቹ ለገበያ የቀረቡ ስለነበሩ ልብ ሳይለው ለባዕድ አምልኮ የዳንኪራ መስዋዕት ያቀረበ ስለመሰለው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በተናፈሰው ወረተኛ ወሬ የተነሳ በዘፈኖቹ ላይ ጥርጣሬ ስለነገሰ እንጂ የአዶ ከበሬና የዛር ዘፈን ዘመናዊ ሙዚቃችን ውስጥ መካተቱ አዲስ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ እስኪ መጀመሪያ የብሔራዊ ቴአትሯ አርቲስት አሰገደች ቀደም ሲል ከሰው ተቀብላ ባለማወቅ ያቀነቀነችውን የዛር ዘፈን እንይ፡፡

“ሰውዬው፣ ሰውዬው በሶራው ላይ

ሰውዬው ሰውዬው በሶራው ላይ

ጋሻዬ በፈረስ ሲሄድ አየህ ወይ”

ይሄ ዘፈን ተቀባዮች አሉት፡፡ በተደጋጋሚ በሬዲዮ የምናዳምጠው ነው፡፡ የዘፈን ምርጫ ላይ ደጋግመን መርጠነዋል፡፡ ዘፈኑ በዜማና በግጥም የተደረሰው በዓመት ሦስት ጊዜ ለሦስት-ለሦስት ቀናት ለሚከበረው አዶ-ከበሬ ነው፡፡ የአዶ-ከበሬ ፈረስ የሆኑ ሰዎች ለዘመን መለወጫ፣ ለመስቀል በዓልና ለጥምቀት ሦስት ቀናት መንፈሱን ተዘጋጅተው ይጠብቁታል፡፡ አይቀርም ይመጣል፡፡ ያስጓራቸዋል፣ ይቀጠቅጣቸዋል፣ አንዳንዴም ድምፃቸው ይቀያየራል (ሴቷን የወንድ፣ የወንዱን የሴት) አልፎ-አልፎ ደግሞ የዛር ፈረሷ በደህና-ጊዜ ጆሮዋን ቢቆርጧት የማትሰማውንና የማትናገረውን ቋንቋ አቀላጥፋ ታንበለብለዋለች፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ እህል አይበላም፡፡

የአካባቢው ሰው ተሰብስቦ ለአዶ-ከብሬው ክብር ይዘፍናል፡፡ ከዘፈኖቹ አንዱ ከላይ በድምፅዊቷ የተቀነቀነው ነው፡፡ ለዚህ ዘፈን ልቡን ያልሰጠና ለመውረግረግ ያልሞከረ አይገኝም፡፡

ለአዶ-ከብሬ ሳናውቅ በስህተት፣ እያወቅን በድፍረት እንድንደነክር ካደረጉን ድምፃዊዎች መካከል አንዱን እንጨምር፣፣ ድምፃዊው ዘፈኑ የአዶ-ከብሬ መሆኑን ያወቀ አይመስለኝም፡፡ ብቻ ዘፍኖታል፡፡ ለአዶ-ከብሬ የተዘፈነውን መጀመሪያ እንመልከት:-

“ልጫወት ብዬ መጣሁ፣

ልጫወት ብዬ መጣሁ፣

ሎሚና ትርንጐ

ከቤቴስ መች አጣሁ” ይላል፡፡

ሎሜና ትርንጐ የአዶ-ከብሬ መንፈሶች መጠሪያ ነው፡፡ አንዳንዴ “ሎሚ” ይባላሉ፡፡ ሌላ ጊዜ “ትርንጐ”፡፡ ከስያሜ ባሻገር ግብራቸውም ሎሚ፣ ትርንጐና ሸንኰራ ነው፡፡ ሽቶና አረቄም አይቀርም፡፡ ይሄን የአዶ-ከብሬ ዘፈን አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ እንዲህ ሲል አቀረበልን - ከልሰው የሰጡትን:-

“አንቺን ፈልጌ መጣሁ

አንቺን ፈልጌ መጣሁ

ሸጋልጅ ቆንጆ ልጅ

ሰፈሬስ መች አጣሁ፡፡”

ይሄ ዘፈን የተከለሰው ግጥሙ እንጂ ዜማው አይደለም፡፡ ዜማው እንዳለ ነው፡፡

ይሄ የዛርና የአዶ ከበሬ ጣጣ ጨርሶ ባይጠፋም እጅግ-እጅግ እንዲቀንስ የተደረገው አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ እንደሆን ይነገራል፡፡ እንግሊዛውያን የህክምና ባለሙያዎችን ቀጥረው ዛርና አዶ ከብሬ ለጥምቀት ወደ ጃንሜዳ ሲሄድ ጠብቀው መርፌ እንዲወጋ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አምልኮው እጅግ ሊቀንስ ቻለ የሚሉ አሉ፡፡ አደባባይ መውጣቱን ትቶ በየቤቱ ተከትቶ በምስጢር መመለኩ አልቀረም የሚሉም አሉ፡፡ ለማንኛውም ባእድ አምልኮው እየቀነሰ እየተቀናነሰ እዚህ እኛ ዘመን ላይ መድረሱ አልቀረም፡፡

ስለጉዳዩ ከሚያውቁት እንደምንረዳው ተልከስካሽ መንፈሶች ሁሌም በዛርና በአዶ ከብሬ መልክ ብቻ አይመጡም፡፡ የሚገለጡበት አይነቱ ብዙ ነው፡፡ ግማሾቹ በተስቦ ይገለጣሉ - በጅምላ ጨራሽ በሽታ ከሚገለጡት መንፈሶች መካከል “ወተቴ” አንዷ ናት፡፡ “ወተቴ” በቆንጆ ሴት የምትመሰል መንፈስ ናት፡፡ “ወተቴ” ወደኛ የምትመጣበት ቃል ኪዳን አላት፡፡ እሱም ልጆቻችንን በፈንጣጣ ለመሸለም ነው፡፡ “ወተቴ” ከሚለው ማቆላመጫ በተጨማሪ ማሬ፣ ደሴ፣ ውሸኔ፣ ዘይቷ፣ ተጓዴ፣ በፍቴ… በሚሉ የማባበያ ስሞች ትወደሳለች፡፡

“ወተቴ” ታላቅ ናት ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይሄንኑ ለማሳየት በእውነታው ዓለም ከሚገኙ ታላላቅ ሰዎችና ገዢዎች ጋር በጋብቻና በዝምድና እንድትተሳሰር በማድረግ ቅጣቷን ለማቅለል ይሞከራል፡፡ በክብር የሚያጅቧት ወንድ መናፍስቶችም አሏት፡፡ “ጉባው”፣ “መርሶ”፣ “ዋጋው”… ይባላሉ፡፡ ለእሷ ክብር ሲባል ጭፍራዎቿ ይከበራሉ፡፡ “ጋሽዬ”፣ “እዬዋ” እየተባሉ ይቆላመጣሉ፡፡ “ወተቴ” የመጣችበትን ቃል ኪዳን ፈፅማ ወደ አድራሻዋ ስትመለስ በክብርና በደማቅ ሥነ ስርዓት ትሸኛለች፡፡

“ቡቃያሽ አምሯል ተስተካክሎ

አብቢልኝ ቶሎ ቶሎ፣

እሰይ ማሪቱ አብባለች

ሸልማ አገሯ ትሄዳለች” እየተባለ የሽኝት ይዘፈንታላታል፡፡

ዘፈኑ በፈንጣጣ መልክ መጥታ እስከምትሄድ የሚቀጥል ነው፡፡ እንግዲህ ለዚች መንፈስ የተዘፈነው ዘመናዊ ሙዚቃችንንና ድምፃዊዎቻችንን ጐብኝቷል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ (ሳያውቅ ይመስለኛል) ለዚች መንፈስ የተቀነቀነውን በፍቅር አልሶ ተጫውቶታል፡፡

“ኧረ ወተቴ ማሬ

ኧረ ወረቴ ማሬ፣

እመጣልሻለሁ

ቅርብ ነው ሀገሬ፣

እስከዚያው ጠብቂኝ

ናፍቆቴ ትዳሮ፡፡

ኧረ ወረቴ ማሬ፡፡”

ይሄ ዘፈን እንዳለ በግጥምና በዜማ ለመንፈስ የተቀነቀነ ነው፡፡ ዘፈኑ ከመጣፈጡ የነሳ ኩልል እንዳለ ጠላ የማይደጋግመው የለም፡፡

በዚህ ላይ በሙሉቀን ተሰጥኦና ክህሎት ሲቀርብልን ወጥመድነቱ ይከፋል፡፡ ያለምንም ማመንታት “ወተቴ”ን በዳንኪራ መስዋዕት፣ በውዝዋዜ ግብር… ማስደሰት ግድ ነው፡፡

“ወተቴ” በፈንጣጣ መልክ የሰፈረችበት ልጅ ቶሎ ቶሎ ቃልኪዳኗን ሞልታ እንድትለቀው ከዘፈን በተጨማሪ ሁለት ሌሎች ግብሮች ይሟሉላታል፡፡ አንዱ ለውበታቸውና ለጥሩ መአዛቸው ሲባሉ የሚቀርቡለት ተክሎች አሉ፡፡ አሪቲ፣ አሽኩቲ፣ ቀጠናዩ፣ እርጐለጋ፣ አላሹሜ፣ ጠጅሳር፣ ቄጠማ፣ ሎሚ፣ ትርንጐ፣ አበባ፣ ሽቶ… ሌላኛው ግብር ደግሞ ገፈራ የሚባለው የስንዴ፣ የገብስና የሽንብራ ድብልቅ ቆሎ በማሽላ ፈንድሻና በኑግ ልጥልጥ ነው፡፡ ዳቦ፣ ቂጣ፣ ጠላ፣ ብርዝ… የመሳሰለውም አለ፡፡ ከዛማ ወዲያ “ወተቴ”ን ለማስደሰት መለማመጫና ማባበያ ዘፈኖችን ማንቆርቆር ነው፡፡

ለወተቴ ከተቀነቀኑት ውስጥ በዘመናዊ ዘፈን በኩል የደረሱን ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚያ ውስጥ ድምፃዊ ውብሸት ፍስሃ ያቀነቀነው አንዱ ነው፡፡ ውብሸት እንዲህ እያለ ሲዘፍን “ወተቴ”ን እያገለገለ እንደነበር ይወቅ አይወቅ አላውቅም፡፡

“ማርዬ ማር ወለላ፣ ማርዬ ማር ወለላ

ታሳምራለች የልጅ ገላ

ማርዬ ማር ፍትፍት፣ ማርዬ ማር ፍትፍት

ታሳምራለች የልጅ ፊት

እጥፍ-ዘርጋ፣

እንዳለንጋ

ተወርወሪ

እንደ ሎሚ

እንደ ማሽላ

ሆ-ሆ-

ፍኪልኝ፡፡”

በዚህ መንፈስ መለማመኛ ዘመን ድፍን ከተማ ተውረግርጓል፡፡ የሚያውቁ ግን አማትበዋል፡፡ ድምፃዊ ውብሸት ፍስሃ ዘፈን ውስጥ ያለውን ግጥም ላክልላችሁ፡፡

“ወተት ናት ማር እንጐቻ

ወተት ናት ማር እንጐቻ

ታዳብራለች የልጅ ጡንቻ

አገሯ ከበረሃ - አገሯ ከበረሃ

ለጠጣት የማር-ውሃ”

ይሄንን ደግሞ ቀለብ አድርገው አዲሶቹ ዘፋኞች እንዳያቀነቅኑት በዚሁ ይብቃን፡፡ ለፅድቅ ያልነው ለኩነኔ እንዳይሆን በማለት፡፡ በዓለ-ልደት ወልደ እግዚአብሔርን ተገን አድርገን ፍራቻ ሳያድርብን ይቺን ያህል ከተጨዋወትን ይብቃን፡፡

መልካም በዓለ-ልደተ-ክርስቶስ ይሁንልን አሜን!!

 

 

 

 

Read 6346 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:31