Saturday, 20 December 2014 12:04

ኤሪክሰን ለዜድቲኢ ከተሰጠው የኔትዎርክ ማስፋፊያ አራቱን ለመስራት ተስማማ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ የተጠቃሚው ቁጥር 40ሚ. ይደርሳል

የስውዲኑ ኤሪክሰን ኩባንያ ለዜድቲኢ ከተሰጠው ስድስት የኔትወርክ ማስፋፊያ አራቱን ለመስራት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በሂልተን ሆቴል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡ ኤሪክሰን ስራውን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያጠናቅቃል ተብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው አመት በመላ አገሪቱ የሚገኙትን 13 የኔትዎርክ ማስፋፊያ ቦታዎች ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች (ዜድቲኢና ህዋዌ) እንዲሰሩት የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ከድርጅቶቹ ጋር ስምምነት ተፈራርሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ኃላፊዎች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ ከ13ቱ የኔትወርክ ማስፋፊያዎች ሰባቱን ህዋዌ፣ ስድስቱን ደግሞ ዜድቲኢ እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሰው ዜቲኢ ስራው ከ150 እስከ 200ሚ ዶላር ያስወጣናል በሚል ስምምነቱን መተግበር ባለመቻሉ አራቱ  የማስፋፊያ ቦታዎች ለኤሪክሰን መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ማክሰኞ የተፈረመው ስምምነትም በዚሁ ላይ ያተኮረ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ኤሪክሰን ኩባንያ ለዜድቲኢ ተሰጥተው ከነበሩት ስድስት የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያዎች መካከል አራቱን ፡- ደቡባዊ፣ ደቡብ ምዕራባዊ፣ ደቡብ ምስራቃዊና ደቡብ ደቡብ ምዕራባዊ የማስፋፊያ ቦታዎችን ተረክቦ፣ የማስፋፊያ ስራዎቹን በመስራት በስድስት ወራት ውስጥ ለኢትዮ ቴሌኮም ለማስረከብ ተስማምቷል፡፡ ዜድቲኢ ቀሪዎቹን ሁለት የማስፋፊያ ቦታዎች ምዕራባዊና ማዕከላዊ ምዕራብ እንዲሁም በእነዚህ ማስፋፊያዎች ውስጥ የሚገኙ ሶስት ሎቶችን እንደሚሰራ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በስምምነት ስነስርዓቱ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱአለም አድማሴ ባደረጉት ንግግር፤ ኤሪክሰን በኢትዮጵያ የረጅም አመት ታሪክና ትውስታ ያለው እንደመሆኑ ለአገራችን አዲስ እንዳልሆነ ገልፀው፤ ስራውን በአግባቡ ያጠናቅቃል ተብሎ በመታመኑ ስምምነቱ መፈፀሙን አመልክተዋል፡፡ ይህም አገሪቱ በያዘችው የእድገትና ትራስፎርሜሽን መጨረሻ በቴሌኮሙ ዘርፍ የምታስመዘግበውን ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎትና የተጠቃሚውን ቁጥር የማብዛት ትልም እውን እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
የኤሪክሰን ኩባንያ የመካከለኛና የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስ ራፊ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ኤሪክሰን እ.ኤ.አ በ1894 በንጉስ ምኒልክ ዘመን፣ የመጀመሪያውን የድርጅቱን ምርት እንደሸጠና በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዳስተዋወቀ አስታውሰው፤ የአሁኑ ስምምነትም ይህንን ታሪክ የሚያስታውስና የሚያጠናክር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኤሪክሰን በ1950 በኢትዮጵያ የስልጠና ማዕከልና ቢሮ ከፍቶ ሥራ መጀመሩን የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ ኩባንያው በሃገሪቱ ውስጥ ልዩ ቦታና ትስስር ያለው በመሆኑ የአሁኑንም ስራ በብቃት ሰርቶ ያስረክባል ብለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ፤ ኤሪክሰን የሚሰራው ማስፋፊያ ሲጠናቀቅ የተጠቃሚውን ቁጥር ወደ 40 ሚሊዮን እንደሚያደርስና የኔትዎርክ ጥራቱን እንደሚያሻሽልም ገልፀዋል፡፡

Read 1305 times