Print this page
Saturday, 20 December 2014 12:06

የ“የኛ ፕሬስ” አሳታሚ የ187 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወሰነበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ታስሯል
በአይናለም የመፅሐፍት መደብር የስም ማጥፋት ክስ የቀረበበት የ“የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ አሳታሚ ዮርዳኖስ ስዩም ሚዲያ ኃ/የተ/የግ.ማህበር፣ ከ187 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት የተወሰነበት ሲሆን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ካሳሁን ወ/ዮሐንስ በቀጠሮ አልተገኘህም በሚል እስከ ቀጣይ ቀጠሮ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ፍ/ቤት አዟል፡፡ የአይናለም መፅሃፍት መሸጫ መደብር ባለቤት አቶ አይናለም መዋ፤ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ፤ ዮርዳኖስ ስዩም ሚዲያ በሚያሳትመው “የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ ላይ “መልካም ስሜን አጥፍቷል” የሚል ነው፡፡ ነሐሴ 21 ቀን 2006 በወጣው “የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ እትም ላይ አቶ አይናለም “ተዋናይ” የተሰኘ በድብቅ የታተመ መፅሃፍ ለገጣሚ ኤፍሬም ስዩም እንደሸጡና ፎርጂድ መፅሃፍ እንደሰጡት፣ ነሐሴ 28 በወጣው የጋዜጣው እትም ደግሞ አቶ አይናለም በሚሊዮን ብር የተገመተ የአቶ ያሬድ ግርማን መፅሃፍ ከፍቃድ ውጪ በማሳተም ጉዳት እንዳደረሱ የሚያትት ዘገባ እንደወጣ ያመለከተው የክስ መዝገቡ፤ ተከሳሽ እነዚህን ዘገባዎች እንዲያስተካክል ከሳሽ ማሳሰቢያ እንደሰጡም ይጠቁማል፡፡ ሆኖም ማስተካከያው ሳይደረግ ጳጉሜ 5 ቀን 2006 በወጣው ጋዜጣ “አቶ አይናለም መዋ ቀርበው ምላሽ ያልሰጡባቸው የየኛ ፕሬስ ጥያቄዎች” በሚል “አቶ አይናለም መፅሃፍትን በመጋዘን በማከማቸት ደራሲያንን ያሰቃያል፣ የመፅሃፍቱን የጀርባ ዋጋ በመፋቅ የዝርፍያ መንገድ ፈጥሯል፣ ለመፅሃፍት ተገቢውን ክብር አይሰጥም” በማለት ባወጣው ዘገባ “መልካም ስሜን አጥፍቷል” ሲሉ አቶ አይናለም መክሰሳቸውን መዝገቡ ያመለክታል፡፡ተከሣሽ የጋዜጣው አሳታሚ ፍ/ቤት ቀርበው ለተከሰሱበት ጉዳይ ምላሽ እንዲሠጡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጭምር ጥሪ ተደርጐላቸው አለመቅረባቸውን ያረጋገጠው ፍ/ቤቱ፤ ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ከተከሣሽ በኩል የቀረቡለትን ማስረጃዎች መነሻ በማድረግ፣ ተከሣሽ በሌሉበት በመልካም ስም ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል ወስኗል፡፡
ፍ/ቤቱም ታህሣስ 1 በዋለው ችሎትም፤ ተከሳሽ በሌሉበት በብር 187,462.50 (አንድ መቶ ሰማኒያ ሰባት ሺህ አራት መቶ ስልሣ ሁለት ብር ከሃምሣ ሣንቲም) እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ተከሣሽ የተወሰነባቸውን የገንዘብ መቀጮ ፖሊስ አስገድዶ ቦሌ ምድብ ችሎት በማቅረብ እንዲያስፈፅም፣ ንግድ ሚኒስቴር በንግድ ፍቃድ በእድሣት ወቅት ገንዘቡ ገቢ ስለመደረጉ እንዲያረጋግጥ፣ የቅጣቱ ውሣኔ በጋዜጣ ላይ ታትሞ እንዲወጣ፣ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔው ለብሮድካስት ባለስልጣን እንዲተላለፍ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሠጥቷል፡፡ የተከሣሽ የይግባኝ መብት የተጠበቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆኑ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት ጋዜጠኛ ካሳሁን ወ/ዮሐንስ፤ ህዳር 29 የተሰጠውን ቀጠሮ አክብሮ ባለመገኘቱና የቀረበትን ምክንያት በማስረጃ አስደግፎ ባለማስረዳቱ ትናንት በፖሊስ ተይዞ ፍ/ቤት ከቀረበ በኋላ ቀደም ሲል ያስያዘው የ2ሺህ ብር ዋስትና ለመንግስት ገቢ ተደርጎ፣  ፍርድ እስከሚሰጥበት ቀጣይ ቀጠሮ ድረስ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተወስኗል፡፡ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ለመስጠትም መዝገቡን ለጥር 5 ቀጥሯል፡፡በአሳታሚው ላይ የተወሰነውን ቅጣት በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የ“የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ስዩም፤ “ውሳኔው አልደረሰንም፤ የምንሰጠው አስተያየት የለም” ብለዋል፡፡
 በሻማ ቡክስ አሳታሚ የታተመው የደራሲ ኤፍሬም ስዩም ‹ተዋናይ› መፅሃፍ በድብቅ አሳትመው አሰራጭተዋል የሚል ክስ በደራሲ ኤፍሬም ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት አቶ አይናለም መዋ ወንጀሉን አለመፈፀማቸውን 4 ምስክሮች አቅርበው በማስረዳታቸው ከ9 ቀናት እስር በኋላ ተለቀው አቃቢ ህግም የቀረበባቸውን ክስ መዝጋቱን አቶ አይናለም ተናግረዋል፡፡ በየኛ ፕሬስ አሳታሚ ላይ ክስ የመሰረቱበት ምክንያትም ጋዜጣው ላይ በተከታታይ በወጡ ዘገባዎች ስሜ ጠፍቷል በሚል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3607 times