Saturday, 20 December 2014 12:07

አዲሱ የውጭ ማስታወቂያዎች ደንብና መመሪያ ምን ይላል?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)

ያለተጠቃሚው ፈቃድ ማስታወቂያ በስልክ ማሰራጨት አይቻልም
በበራሪ ወረቀቶች፣ በፖስተር፣ በስቲከር.. ማስታወቂያ ማሰራጨት ተከልክሏል..
      የውጭ ማስታወቂያዎች በህግና በሥርዓት እንዲመሩና አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ በአግባቡ እንድታገኝ የሚያግዝ የውጭ ማስታወቂያ ደንብና መመሪያ ወጣ፡፡ ክልሎችም ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት፣ ደንብና መመሪያ አውጥተው ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በውጭ ማስታወቂያዎች ህጋዊ አሠራር፣ በዘርፉ በሚታዩ ችግሮችና መወሰድ በሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰሞኑን ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት ይፋ የተደረገው የውጭ ማስታወቂያ ረቂቅ ሞዴል ደንብና መመሪያ፤ የውጪ ማስታወቂያ ሥራ በሥርዓት እንዲመራ የሚያደርግ የተሟላ ህግ እንደሌለና በህግ እንደማይመራ የሚጠቁም ሲሆን ሥራውን በቋሚነትና በባለቤትነት የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል አለመኖሩን ይገልፃል፡፡ አዲሱ ደንብና መመሪያ ሥራው በአግባቡና በሥርዓት እንዲካሄድ ከማድረጉም ባሻገር አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ያስችላታል ተብሏል፡፡አዲሱ ደንብና መመሪያ፤ የውጪ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ፣ በማንጠልጠል፣ በመስቀልና በመትከል ማስተዋወቅ የሚቻለው በሚመለከተው አካል በተፈቀደ ቦታ፣ ከፍታ፣ መጠን፣ አቀማመጥ፣ ርቀት፣ ጊዜና ተገቢው የአገልግሎት ክፍያ ሲከፈል ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በውጪ ማስታወቂያ ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በየክፍለ ከተማው ከሚገኙት የኮሙኒኬሽን ህዝብ ግንኙነትና የማስታወቂያ ጽሕፈት ቤቶች ፈቃድ ማግኘትም ይጠበቅበታል፡፡
የማስታወቂያ አዘጋጆችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው የውጪ ማስታወቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም ማስታወቂያ ከመትከሉ፣ ከመለጠፉ፣ በድምፅ ማጉያ ከማስነገሩ ወይም በሌላ በማናቸውም ዘዴዎች ከማሰራጨቱ በፊት ተመዝግቦ የተፈቀደለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መያዝ እንዳለበትም በአዲሱ መመሪያ ተጠቁሟል፡፡
በማስታወቂያ ስራ ላይ የመሰማራት መብት የተሰጠው ለኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆን አዲሱ ደንብና መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠ የውጪ ማስታወቂያ ስራዎችና የሌሎችን የውጪ ማስታወቂያ የማሰራጨት ፍቃድ እንደሚሰረዝና ማስታወቂያው እንደሚነሳም ተገልጿል፡፡
የአደንዛዥነት ባህሪ ያላቸው ማንኛውም ዕፆች፣ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ የማይሰጡ መድኀኒቶች፣ ለአጠቃቀማቸው ልዩ ስልጠና የሚያስፈልጋቸውና ለህክምና ሥራ የሚውሉ ዕቃዎችን፣ የሲጋራ ማስታወቂያዎችና የፖለቲካ ግብ ያላቸው ማስታወቂያዎችን በውጪ ማስታወቂያ አማካኝነት ማሰራጨት በአዲሱ ደንብና መመሪያ ተልክሏል፡፡
የአልኮል መጠናቸው ከ12 በመቶ በላይ የሆኑ መጠጦች በውጪ ማስታወቂያዎች ሊሰራጩ የሚችሉ ሲሆን ማስታወቂያዎቹን ከልጆች መዋያ ማዕከል፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሲኒማና ቴያትር ቤት፣ ከስታዲዬምና ከህክምና ተቋማት በመቶ ሜትር ራዲየስ ላይ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡
በማናቸውም ህንፃዎች ግድግዳዎች፣ አጥሮች፣ የአውቶብስ ፌርማታዎች፣ ምሰሶዎች፣ በቴሌ አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች፣ በአውራ ጎዳናዎች፣ በባቡር ሐዲዶች፣ በህዝብ ማጓጓዣዎች እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች ላይ ማስታወቂያዎችን መትከል፣ መለጠፍና በሌላ መንገድ ማሰራጨትም ተከልክሏል፡፡ አዲሱ ደንብና መመሪያ በተጨማሪ በብሮሸር፣ በፖስተር፣ በስቲከሮችና በበራሪ ወረቀቶች ማስታወቂያ ማሰራጨትንም  ከልክሏል፡፡  
በመንገዶች፣ በህንፃዎችና በቢል ቦርዶች ላይ ፈቃድ አግኝተው የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች በአገር ውስጥ ቋንቋና ፊደል የተፃፉ መሆን እንዳለባቸውና በውጪ ቋንቋዎች መፃፍ ካስፈለገም የአገር ውስጥ ቋንቋው በመጀመርያ ሊፃፍ ይገባዋል ይላል - መመሪያው፡፡ ይህም ማስታወቂያያች በየክልሎቹ በየክልሉ ቋንቋና ፊደል ሊፃፉ እንደሚገባቸው የሚያስገነዝብ ነው ያሉት የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ፤ “በኦሮሚያ ክልል በሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ላይ የኦሮሞኛ ቋንቋ ከላይ ሆኖ በሚገባ በሚታይ ሁኔታ መፃፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ምክትል ዳይሬክተሩ አክለው ሲያብራሩ፤ “ኦሮምኛው አነስ ብሎ ለምን ይጻፋል? ይህ እኮ ህዝቦች ለዘመናት ታግለው ያመጡት መብት ነው፡፡ በኦሮሚያ በሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ላይ ኦሮምኛው ጎልቶ ካልተነገረ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት በምን ይረጋገጣል፡፡ ይህ እኮ በቋንቋ የመናገር መብትን የሚጨፈልቅ ነው፡፡ በስንት መስዋዕትነት የመጣውን ነገር በማይረባ አፃፃፍ አሳልፈን መስጠት የለብንም” ብለዋል፡፡
ከቢሮው የተለየ ፈቃድ ካልተሰጠው በስተቀር የድምፁ መጠን ከ50 ዴሲ ቤል በላይ የሆነ ማስታወቂያ ሊተላለፍ አይችልም፡፡
 ማስታወቂያው ሊተላለፍ የሚችለውም ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ቀኑ 12 ሰዓት ብቻ እንደሆነና የትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎችና ፍርድቤቶች ማስታወቂያ ሊተላለፍባቸው የማይችልባቸው አካባቢዎች መሆናቸው በደንቡ ላይ ተገልጿል፡፡ በስልክ አገልግሎት አማካኝነት ማስታወቂያን ለማሰራጨት የሚቻለው ከቴሌኮሙኒኬሽን በሚሰጥ ፈቃድ ብቻ እንደሆነ የሚገልፀው ደንቡ፤ የህዝብ ማስታወቂያ ወይንም የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪውን የሚመለከት ማስታወቂያ ካልሆነ በስተቀር ተጠቃሚው ሣይፈቅድ ማንኛውንም የንግድ ማስታወቂያ በስልክ ማሰራጨት ክልክል እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በኤግዚቢሽን ማዕከል አጥር ላይ ያሉት የማስታወቂያ መለጠፊያ ቦታዎች ለግለሰቦች አይሰጡም ተብለን ከተከለከልን በኋላ ለሳምሰንግ፣ ለቴክኖና ለሪል እስቴቶች የተሰጡበት አሠራር ህጋዊነትን የተከተለ አይደለም፣ የውጭ ዜጐች ከማስታወቂያ ሥራ ውጪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ አሠራር ተግባራዊ መሆን አለበት” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ በበኩላቸው፤ አሠራሮቹ ተፈትሸው ወደ ህጋዊነት የሚመጡበት ሁኔታ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

Read 4983 times