Saturday, 20 December 2014 12:08

የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን ፓትርያርክ፤የህዳሴ ግድብ ማንንም አይጎዳም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ዳግማዊ ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የትኛውንም የተፋሰሱን አገር እንደማይ ጎዳ ገለፁ፡፡ ፓትርያርኩ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ግብፅ ከተጓዘው የኢትዮጵያ “የህዝብ ዲፕሎማሲያዊ” ቡድን ጋር በካይሮ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነው ማንኛውም ፕሮጀክት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ለኩዌት ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለምልልስ፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታን እንደሚቃወሙ የገለፁት ፓትርያርኩ፤ ሰሞኑን ለግድቡ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ መግለፃቸው አነጋጋሪ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ድህነትን ለማሸነፍ የሚያደርገውን ጥረት እናበረታታለን፤ በፀሎታችንም ከጎኑ ነን” ያሉት ዳግማዊ ዮሐንስ፤ ሃገራቸው ግብፅም የግድቡን ግንባታ እንደምትደግፍና በፕሮጀክቱ ዙሪያ ማንኛውንም መረጃ ለኢትዮጵያ በመስጠት ተባባሪ እንደምትሆን ተናግረዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ የተመራው የኢትዮጵያ ህዝብ ዲፕሎማቲክ ቡድን፤ ከግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከሌሎች የሃገሪቱ ባለስልጣናት፣ ምሁራንና የሃይማኖት ልሂቃን ጋር ተገናኝቶ የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ጉዳይ ላይ እንደተወያየ ታውቋል፡፡ ከፓትርያርኩ ጋር የተደረገው  ውይይትም የተልዕኮው አካል ነው ተብሏል፡፡
የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር ለ1600 ዓመታት ዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን ከግብፅ የተሾሙ ከ100 በላይ ፓትርያርኮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እየተፈራረቁ እንደመሩ ይታወቃል፡፡
ከግብፅ የተላኩት የመጨረሻው ፓትርያርክ ሊቀጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ሲሆኑ ከ1951 ዓ.ም በኋላ ቤተክርስቲያኒቱ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ ያስፈልጋታል በሚል ኢትዮጵያዊው አቡነ ባስሊዮስ እንደተሾሙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Read 4750 times