Saturday, 20 December 2014 12:11

የህንዱ የአይን ህክምና ማዕከል አሰራር እንዲፈተሽ ታዘዘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

ለፍተሻው የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራ ጀምሯል
የጤና ጥበቃ ሚ/ሩ በማዕከሉ ተገኝተው ከህንዳዊያኑ ጋር ተነጋግረዋል

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የላቀ የአይን ህክምና ይሰጣል ተብሎ በኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት በዘውዲቱ ሆቴል ሆስፒታል የተቋቋመው OIA የህንድ የዓይን ህክምና ማእከል ፈፅሟል በተባለው የህክምና ስህተቶች፣ በአስተዳደራዊና በገንዘብ ምዝበራ ጉዳዮች ላይ ፍተሻ እንዲካሄድ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በታዘዘው መሰረት የተቋቋመው ኮሚቴ ሰሞኑን እንደጀመረ ምንጮች ገለፁ፡፡
ለዓይን ህክምና ወደ ማዕከሉ በሄዱ ታማሚዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ መዘገቡን ተከትሎ ባለፈው ቅዳሜ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ በማዕከሉ ተገኝተው ከህንዳውያኑ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ ከኃላፊዎቹ ጋር ምን እንደተባባሉና ምን ውሳኔ ላይ እንደደረሱ አልታወቀም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምንጮቻችን እንደገለፁልን፤ ብቃት በሌላቸው ሃኪሞች በዜጎች ላይ እየደረሰ ነው በተባለው የህክምና ችግርና በአጠቃላይ በማዕከሉ ብልሹ አሰራር ዙሪያ የማጣራት ስራ እንዲካሄድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባዘዘው መሰረት ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲም ሁለት ባለሙያዎችን መድቦ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሆነ የገለፁልን የማዕከሉ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች፤ የኮሚቴው አባላት ባለፈው ሐሙስ ከማዕከሉ ሰራተኞች መረጃ ማሰባሰባቸውን ጠቁመዋል፡፡
በማዕከሉ ይከናወናሉ የተባሉ አግባብ ያልሆኑ ተግባራትን ለማጣራት ለመጣው ኮሚቴ ሁሉን ነገር በዝርዝር አስረድቻለሁ” ያሉት አንድ ኢትዮጵያዊ የህክምና ባለሙያ፤ ሙሉ ሃኪም ሳይሆኑ በባለሙያነት ተመድበው በሚሰሩ የህንድ ባለሙያዎች ብዙ ጥፋቶች እየደረሱ እንደሆነ፣ ሰዎች ለህክምና ገብተው ማደንዘዣ ከተወጉ በኋላ ሃኪሞች ዋጋ እንደሚደራደሩ፣ ማዕከሉ የካርድ ክፍልና የመረጃ ዴስክ እንደሌለ እና ሌሎች ችግሮችን ለአጣሪው ቡድን መግለፃቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ታካሚዎች ከገንዘባቸውም ከአይናቸውም ሳይሆኑ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግሬአለሁ ያሉት ሃኪሙ፤ ማዕከሉ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአቅም ግንባታ ስራ እየሰራ እንደሆነ ተደርጐ ቢተዋወቅም በዚህ ረገድ አንድም ስራ አለመስራቱን ለኮሚቴው እንደገለፁ ጠቁመዋል፡፡
“ማዕከከሉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ያሉት ሌላ የማዕከሉ ኢትዮጵያዊ ሰራተኛ፤ መንግስት የኮሚቴውን የጥናት ውጤት ከመረመረ በኋላ አንድ እርምጃ ይወስዳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በማዕከሉ ላይ ከተሰራው ጥናት በተጨማሪ አዲስ ጥናት እንዲካሄድ የተፈለገው በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ለመስጠት እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ የህንዱ የአይን ህክምና ማዕከል (OIA) በዓይን ታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የሚገልፅ ዘገባ ከተጐጂዎች በተገኘ መረጃ ተደግፎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

Read 3479 times