Saturday, 20 December 2014 12:15

መድረክና ኢዴፓ የተሳካ ሰልፍና ስብሰባ አድርገናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(37 votes)

የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር በክልሎች ህዝባዊ ስብሰባ ሊያደርግ እየተዘጋጀ ነው
ኢዴፓ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እያገኘሁ ነው ብሏል

መድረክና ኢዴፓ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ማድረጋቸውን የገለፁ ሲሆን የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር በበኩሉ፤ ያቀደው ተከታታይ ህዝባዊ ስብሰባ ቢታገድም የሃገሪቱን የተቃውሞ ፖለቲካ ማነቃቃቱን ገልጿል፡፡ በክልል ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ እየተዘጋጁ መሆኑንE ትብብሩ ጠቁሟል፡፡
ባለፈው እሁድ በመዲናዋ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ የነበረው መድረክ፤ በሰልፉ ላይ ከ10ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ጠቁሞ የታሰበውን ያህል ባይሆንም የተለያዩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደቻለ አስታውቋል፡፡
የመድረኩ አመራር አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ “ፓርቲው የሰልፉን ቅስቀሳ ማድረግ አልቻለም፣ የጥሪ ወረቀት እንዲበትኑ የተሰማሩ ግብረ ኃይሎች ወረቀቱን እንዳይበትኑ ተደርገዋል፤ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ 10ሺዎች የተሳተፉበት ሰልፍ ማድረጋችን ያቀድነው መሳካቱን ያሳያል” ብለዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ከምርጫ፣ ከፍትህና ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ወደ 37 የሚደርሱ መፈክሮችና ጥያቄዎች መቅረባቸውን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፤ “ጥያቄዎቹ የመንግስትን ምላሽ ካላገኙ በድጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግም ሆነ ሌሎች የሰላማዊ ትግል አማራጮችን በመጠቀም ጥያቄያችንን ማቅረብ እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ የጠየቅነው ከፒያሳ እስከ ድል ሃውልት ባለው መንገድ ላይ ቢሆንም ፍቃድ የተሰጠን በግንፍሌ ድልድይ ወደ የካ በሚወስደው መንገድ ነው ያሉት የመድረክ አመራር፤ ለዚህም ምክንያቱ ገዥው ፓርቲ በመሃል ከተማ ድምፃችን እንዳይሰማ በመፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀን በመቀሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ ያደረገው ኢዴፓ በበኩሉ፤ ለሁለት ቀናት የተሳካ ቅስቀሳ ማድረጉንና ነዋሪውም ከፖሊሶች የሚደርስበትን ተፅዕኖ አሸንፎ በስብሰባው መታደሙን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው እስከ 1 ሺህ ሰው በስብሰባው እንደሚሳተፍ ጠብቆ የነበረ ሲሆን ከ600 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውንና ይህም ከታሰበው ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ አመርቂ ውጤት ነው ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡ ህብረተሰቡ የአፈናና የጭቆና ሰለባ መሆኑንና፣ ከድምፀ ወያኔና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውጭ ነጻ ሚዲያዎችን የመከታተል እድል መነፈጉ በስብሰባው ላይ እንደተነሳ የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ በመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የፓርቲው አመራሮች ትንተና እንደሰጡም ተናግረዋል፡፡በድንበርና በአሰብ ወደብ ጉዳይ ላይ ኢዴፓ ያለው አቋም ምን እንደሆነ ከተሰብሳቢዎች ተጠይቆ በቂ ማብራሪያ መሰጠቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ የአሰብ ወደብን በተመለከተ ኢዴፓ የ3 ሚሊዮን ሰዎችን ፊርማ አሰባስቦ ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ለተባበሩት መንግስታት ጥያቄ እንዳቀረበ ተገልጿል ብለዋል፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ የመስራትና የውህደት ጉዳይ ተነስቶ እንደነበርም አስታውሰው ኢዴፓ በአቋም ደረጃ ለውህደት ዝግጁ እንደሆነ ለተሳታፊው መገለፁን ተናግረዋል፡፡ፓርቲያቸው የህዝባዊ ስብሰባ መድረኮችን በሚገባ እየተጠቀመ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ መድረኮቹ ህብረተሰቡን ወደ ኢዴፓ እየሳቡ ነው ብለዋል፡፡ “ኢዴፓ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ ነው፣ አባላቱም ሆነ ደጋፊዎቹ እየተነቃቁ ነው” ሲሉ ገልፀዋል - ዶ/ር ጫኔ፡፡ህዳር 27 እና 28 የ24 ሰዓት የአደባባይ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ለማከናወን አቅዶ ፈቃድ የተከለከለው የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር በበኩሉ፤ በአዲስ አበባ ያሰበውን ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ ባይችልም የፖለቲካ መነቃቃትና ተፅዕኖ መፍጠር እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ ትብብሩ በክልል ከተሞች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ ዋና መርሁ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ መንግስት ለትብብሩ ህዝባዊ ስብሰባ ከልክሎ ለመድረክ መፍቀዱ የጠቀሱት ኃላፊው፤ አንዱን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማሰጠት፣ ሌላውን ደግሞ ለማሳጣት የተደረገ ጥረት ነው ብለዋል፡፡ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ አሁን የሚደረገው ትግል ሃገርን የማዳንና ወደ ትክክለኛው ህጋዊ ስርአት የማምጣት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በወረቀት ላይ ብቻ ቀርቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ፓርቲዎች በወረቀት ላይ ባለው አዋጅ የተሰጣቸውን መብት በተግባር እየተነፈጉ ነው ብለዋል፡፡ “ህዝባዊ ስብሰባ መጥራት፣ ቅስቀሳ ማድረግ፣ አዳራሽ ማግኘትና መሰብሰብ የፍቃድ ጉዳይ ሆኗል፤ ሂደቱ ካልተስተካከለ በሃገሪቱ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ይችላል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የግንቦቱን ምርጫ አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ ህጋዊና ህገ ወጥነትን እያጣቀሱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን መንግስት ቸል እንደማይል ማሳሰባቸውን በተመለከተ ተቃዋሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ ማስፈራራት ለኢህአዴግ አዲስ ነገር አይደለም ብለዋል፡፡
የመድረክ አመራር አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስፈራሪያ አዘል መልዕክቶችን ከመሰንዘራቸው በፊት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉት ፓርቲዎች ጋር ተደራድረው ችግሮችን መፍታት አለባቸው” ይላሉ፡፡ “እኛ ህጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች ነን” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ “መድረክን ከመሳሰሉ ፓርቲዎች ጋር ባሉ ችግሮችና ቅሬታዎች ዙሪያ ተወያይተው ችግር ሳይፈቱ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ከሆኑት ጋር ብቻ ተደራድረው ምርጫ ለማካሄድ መሞከሩ ተገቢ አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን የሚያመጣም አይሆንም” ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ የተለመደ የኢህአዴግ ባህሪ ነው ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ዲመክራሲያዊና ፍትሃዊ ይሆናል ስላሉ ብቻ ይሆናል ብለን አናምንም፤ ሁሌም በጥርጣሬ ነው የምንመለከተው” ብለዋል፡፡ “ህግ የሚፈቅደውን ማድረግ ነውጠኛ የሚያስብል ከሆነ ትክክል አይደለም” ያሉት የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፤ ህጉ ያስቀመጠውን መብት የመንግስት አካላት ሊሸረሽሩት አይገባም፤ ህጉ እስከፈቀደ ድረስ እንንቀሳቀሳለን፤ ምርጫው ስኬታማ የሚሆነው ህዝባዊ ንቅናቄ ሲፈጠር ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ መንግስት ተቃዋሚዎችን ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላችሁ እያለ መክሰሱ የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ “በቅርቡም በዚህ ጉዳይ ላይ በቴሌቪዥን የሚሰራጭ ዶክመንተሪ እየተዘጋጀ እንደሆነ መረጃው አለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ጠንካራ ፓርቲዎችን ለመኮርኮምና ሰላማዊ ትግሉን ለማደናቀፍ ያለመ ነው ያሉት ኃላፊው፤ “ለለውጥ የተነሳን ፓርቲ ስለሆንን ለማስፈራሪያዎች ዋጋ እየከፈልን ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

Read 6689 times