Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Friday, 06 January 2012 11:32

የሀዲስ አለማየሁ ሦስት ተረቶች አንድነትና ርእዮተዓለማዊ አንድምታው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በብርሃኑ ገበየሁ “ልቦለድ እንደ ርዕዮተዓለም መገለጫ” በሚለው ጥናታዊ ስራ የሀዲስን ተረቶች ለምን ይሆን ያልተካተቱት?

ተረት “እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ”

ፈርመያዣ- ከሳምንት በፊት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ግንባታ ሲቋቋም መጠሪያውንና መታሰቢያነቱን ለታላቁ ደራሲያችን ለሀዲስ አለማየሁ ማድረጉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ይፋ ሆኗል፡፡ የሀገራች ስመጥር የባህልና የስነጽሁፍ ባለሟሎች በባህል ማእከሉ ምረቃ ወቅት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ማቅረባቸውም፣ የሚመሰገን ተግባር ነው፡፡ ዝግጅቱ ዳር እንዲደርስ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ለተሳታፊዎች የጥሪ ወረቀት ሲያደርስ የነበረው፣ የዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ መስፍን የአንዳንዶቹን አድራሻ ለማግኘት ብዙ መልፋቱን ተመልክቻለሁና ዝግጅቱን ለማሳካት ባደረገው ትጋት መመስገን ይገባዋል፤ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ሀላፊዎች ለባህል ጥናት መስፋፋት ያደረጉት ትርጉም ያለው ውሳኔና ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል በርከት ያሉ ጥናታዊ ስራዎች በመድረኩ ላይ መቅረባቸውን ስሰማ፣ አንድ ነገር ታሰበኝ፤ ነፍሱን ይማረውና ታዋቂው የስነግጥም መምህርና የባህል አጥኚው ብርሀኑ ገበየሁ (ረዳት ፕሮፌሰር) በህይወት ቢኖር “ልቦለድ እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” በሚል በሀዲስ ስራዎች ላይ ባቀረበው ጥናቱ ፣ ተማሪዎቹ የጠየቁትን ጥያቄ የሚመልስበት መድረክ ይሆን ይሆን? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ እናም ይህን ሂሳዊ መጣጥፍ ለተወዳጁ መምህር ብርሀኑ ገበየሁ መታሰቢያ እንዲሆንልኝ ብዬ አቀረብኩት…

ሦስቱ የሀዲስ ዓለማየሁ ተረቶች ከወጡበት ዘመን አንጻር ሲፈከሩ

የሀዲስን ተረት ተረት የመሰረት የሚለውን መጽሐፍ በርካታ ጥልቅ ሀሳቦች፣ ፍልስፍናዎች፣ ግለሰባዊ፣ ሀገራዊና አለማቀፋዊ መሪር እውነቶች … የተቀነቀኑባቸው ብዙ ተረቶችን የያዘ አንኳር የፈጠራ ሥራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከመነሻው “ተረት ተረት…” የሚለውን (ርዕሱን)  አይተን ብቻ ለ “ተረት” ካለ የተዛባ አመለካከትና እውቀት የተነሳ መጽሐፉ ተገቢውን ትኩረትና አክብሮት ያገኘ አይመስልም፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ማስረጃ፣ ደራሲው በተለያዩ መድረኮች የሚነሱት፣ በረጅም ልቦለድ መጽሐፎቻቸው እና ጠንከር ሲልም በሁለቱ ኢ-ልቦለድ ሥራዎቻቸው መሆኑን ማስታወስ ይበቃል፡፡

ተረት ተረት የመሰረት የሚለውን መጽሐፍ ላገላበጠ ግን፣ ደራሲ ሀዲስ በመግቢያቸው ላይ ያሰፈሩትን ስለ “ተረት” ያላቸውን ጥልቅ አለማቀፋዊ እውቀት ይገነዘባል፤ የዓለምን እውነት (በተለይ መሪሩን ለምሳሌ በሰው ልጆች መካከል ያለን የንዋይና የእውቀት ልዩነት፣ የዘር መድሎ …) በብልሃት ለመግለጥ ሲሉ ይሁነኝ ብለው የፃፉት የልቦለድ ሥራቸው መሆኑን ይረዳል፡፡ እንደውም፣ እነዚህ ምርጥ ፍልስፍናዊ ተረቶች፣ ከሀገረሰባዊ ተረቶች (Folktales) ጋር ይመደባሉ? በእነሱ መለኪያ ሊዳኙ ይችላሉ? የሚሉ ሞጋች ጥያቄዎች በአእምሮዬ አጭሯል፡፡

እነዚህ ተረቶች፣ የቃል ተረኮች (Oral Narratives) ዘር ስለመሆናቸው Abrams (1999) የRober Southyን “The Three Bears” ዋቢ አድርጐ “The folks tale … is often extended to include stories invented by a known author”(ገጽ፣ 101) በማለት ሀገረሰባዊ ተረቶች፣ የታዋቂ ደራሲዎችን የፈጠራ(የልቦለድ) ተረታዊ ትረካዎች እንደሚጨምር ያስረግጥልናል፡፡

የዚህ ጽሁፍ የትኩረት አቅጣጫ ሁለት ዘመናት ላይ አርፏል፡፡ የመጀመሪያው፣ ተረቶች በተጻፉበት ዓመታት የነበሩት ሃገራዊ ወይም ዓለማቀፋዊ ሁነቶች ከደራሲው ርዕዮተ ዓለም አንፃር ተገርተውና ሰልተው ቀርበዋል ብዬ ስላሰብኩ፣ ተረቶች ከወጡበት ወቅት አንጻር መመርመር ተፈልጓል፡፡

በወቅቱ ሀዲስ የዓለማቀፋዊ ሁኔታ አንቅቷቸው፣ የሰው ልጆችን እጣፈንታ የሚያመለክቱ ስነ-ምግባራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም ሳይንሳዊ ፍልስፍናዎች በተረቶቻቸው አስተንትነዋል፡፡ በዚህ ቀድሞ በታተመው ልቦለዳዊ የተረቶች መጽሐፍ፣ ወደ ኋላ ላይ በሌሎች ሥራዎቻቸው ያነሳቸውን አንኳር ሀሳቦች (ርዕዮተ ዓለም) ቀድመው አንስተዋል፡፡

ተረቶቹ፣ ታሪካዊ ሰነዶች ናቸውም ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ትምህርትን (ሥልጣኔን) ዋና ማንፀሪያ አድርጌ ተረቶች ስለዘመናቸው ምን እንደሚገልጡ ለመተንተን ሞክሬአለሁ፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ፣ ብርሃኑ ገበየሁ “ልቦለድ እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” (1992 ዓ.ም) በሚለው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ይሄን የተረቶች መጽሐፍ ለምን እንዳላካተቱት አጠንክሮ መጠየቅ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ጥናታዊ መጣጥፍ፣ በመጀመሪያው ላይ ነቢባዊ (Theoretical) እውቀትን በማስተንተን ላይ ፣ በሁለተኛው ደግሞ፣ ተረቶችን በሚፈለገው አውድ በመገልገል ላይ ትኩረት አድርጓል ፡፡

እስከ አሁን የተገለጸውን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ 3 ተረቶች በጥንቃቄ ተመርጠዋል፡፡ እነሱም “ጥጋብ ስስትን ያገባ እንደሆነ ረሃብን ይወልዳል”፣ “አይጥ ከጠፋ ድመት አይፈለግም”  እና “ዞሮ ዞሮ ዓለም ለዝንጀሮ”  የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ተረቶች የተመረጡት፣ ካላቸው የርዕሰ ጉዳዩና ጭብጥ አንድነት፣ እንዲሁም የተተረቱበት የትኩረት አቅጣጫ ተመሳስሎ አንፃር ሲሆን፣ (ለምሳሌ፡- ሁሉም በሰው ልጆች መካከል ባለ ልዩነት በተለይ የዘር መድሎ ላይ ያጠነጥናሉ፡፡) ለተነሳንበት ዓላማ ተገቢ ማስረጃ ይሆናሉ ተብሎ ታስቦባቸው በጥንቃቄ የተመረጡ መሆኑን መጠቆም ተገቢ ነው፡፡

ክቡር ሀዲስ አለማየሁ፣ በልቦለድ ሥራዎቻቸው ያነሷቸውን ተጠየቂያዊ ፍልስፍናዎች፣ አመራማሪ ሀሳቦች በተረቶቻቸው አማካኝነት አንስተዋል፡፡ ተረቶቹን “እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” ተገልገለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ኋላ ላይ በሌሎች የልቦለድና የኢ-ልቦለድ መጽሐፎቻቸው ያነሷቸውን ሀሳቦች፣ ቀድመው ያረቀቁት በፈጠሯቸው ተረቶች ነው ቢባል ማጣፊያው አያጥርም፡፡

ብርሃኑ ገበየሁ፣ “ልቦለድ እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” በሚለው ጥናቱ፣ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ልቦለዶቻቸውን ለርዕዮተ ዓለም መገለጫነት እንደተጠቀሙባቸው፣ ሁለት ልቦለድ ያልሆኑ ሥራዎቻቸውን (የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም /1948/ እና ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አሰተዳደር ያስፈልጋታል? /1966 ዓ.ም/) በማስረጃነት ማንፀሪያ አድርጎ አስተንትኗል፡፡ በጥናቱም፣ ደራሲው ርዕዮተ ዓለማቸውን በልቦለዶቻቸው ለማስረፅ በዋናነት 3 ማህበራዊ አውዶች (ትምህርት ቤት፣ ጋብቻ እና ሽፍትነት /አመጽ እና ህጋዊነት/) እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡ በ3ቱም አውዶች ውስጥ፣ ለርዕዮተ ዓለም መግለጫነት ይሆናሉ የተባሉ አስረጅዎችንም ተንትኖ አስረድቷል፡፡

ብርሃኑ፣ በየልምዣት (1980) መቅድም ገጽ÷5 ላይ ደራሲው እራሳቸው የገለጹትን ሀሳብ እንደሚከተለው በማስፈር የጥናቱን ትክክለኝነት ለማሳየት ተግቷል፡፡

“ይህንን የልምዣትን ሆነ ፍቅር እስከ መቃብርንና ወንጀለኛው ዳኛን ለመጻፍ ሳስብ አይነተኛ ዓላማ ያደረግሁት አንድ ነገር ነው፡፡ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስራተ ማህበር÷ ማለት ያስተዳደሩ÷ የፍርዱ÷ የማህበራዊ ኑሮና እነዚህን የመሳሰለውን ሁሉ አጠቃሎ የያዘውን ጠቅላላ ስራት÷ በዘመናዊ የትምህርት ድርጅት ውስጥ በትምህርት መልክ ባለመሰጠቱ÷ መልካሙም ሆነ ክፉው እየተረሳ በመናድ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ … በትምህርት ቤት በጥንቃቄ ተጠንቶና ተሙዋልቶ ሊሰጥ የሚችለውን ያክል ባይሆንም÷ በልብወለድ መልክ እንኩዋ÷ በተከታታይ ትውልዶች ጋር በመጠኑ ለማስተዋወቅ መሞከር ነው፡፡”

የብርሃኑ ጥናት ቀደም ሲል በተገለጹት 3 አውዶች መካከል አንጻራዊ በሆነ መልኩ “ትምህርት ቤት” የሚለውን በስፋት ተንትኗል፡፡ በዚህ ጽሁፍም በዋናነት የትምህርት ቤትና የትምህርት ጉዳይ በሀዲስ ተረቶች እንዴት እንደተገለጹ በማስተንተን፣ በብርሃኑ ጥናት ተረቶቹ ቢካተቱ ያለውን አግባብነት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

በብርሃኑ ጥናት፣ የሀዲስ አለማየሁ የልምዣት ከጣሊያን ወረራ በኋላ ስለነበረው ‹‹ማህበረ ታሪካዊ›› ዘመን የሚሉት እና የኢትዮጵያ ትምህርት ምን መምሰል እንዳለበት እንደ ጭበጥ እንዲነሳ (ገጽ÷50)፣ “… ከባህል÷ ከታሪክ÷ ከወግና ከኢትዮጵያዊነት የተገነጠለ የትምህርት ስርዓት ማንነቱን የማያውቅ ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ ከመፈልፈል ያለፈ ማህበራዊ ፋይዳ የሌለው መሆኑ …” (ገጽ÷51)፣ በወቅቱ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዳልነበሩ (ገጽ÷53)፣ ፈረንጅ ሃገር የተማሩት ተማሪዎች ሕይወታቸውንም ሳይቀር በፈረንጆቹ አምሳል እንደሚያስቀርጹ፣ በቅኝ ግዛት በተያዘች ሃገር ላይ የሚሰጠው ትምህርት የባዕዳንን ታሪክና ባህል የሚያቀነቅን ስለመሆኑ … (ገጽ÷52) ተብራርቷል፡፡

በአጭሩ፣ ሀዲስ አለማየሁ በተለይ የ2ኛ የዓለም ጦርነት በፈጠረው ጣጣ፣ ቅኝ ገዢዎች ስለሚያደርሱት ስልታዊ በደል፣ ስላበላሹት የትምህርት ስርዓት፣ ይሄን ለማስተካከል መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ በልቦለዶቻቸው እንደገለጹ ጥናቱ (ከገጽ 46-56) ገልጿል፡፡

ብርሃኑ፣ ይህ ዳጐስ ያለና ደረጃዉን የጠበቀ ጥናታዊ ሥራ ለማስኬድ የተከተሉት መንገድ ምክንያታዊና ተገቢ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የደራሲውን ርዕዮተ ዓለም ጨምቆ ለማውጣት፣ የደራሲውን ሥራዎች በተናጠልና በጥቅል መመርመራቸው፣ እንደዚሁም፣ ከሃዲስ አለማየሁ ሥራዎች ጋር አብረው የወጡ የዘመኑ አሻራ ያረፈባቸውን የሌሎች ደራሲያኖችንም ሥራ ጐን ለጐን መመልከታቸው ሊጠቀስ የሚገባው ትልቁ ጠንካራ ጐን ነው፡፡ ይሄ ዓይነቱ የአጠናን (የአነባበብ) ስልት ደግሞ፣ የአማርኛን ስነ-ጽሁፎች በወጉ ለመረዳትና ጭብጣቸውን ጨምቆ ለማውጣት ተመራጩ መንገድ እንደሆነ ዮናስ አድማሱ “On the state of Amharic Literary scholarship›› (June 2001 Page 38) በሚለው ጥናታቸው አመላክተዋል፡፡  የዶ/ር ዮናስ ጥናት፣ የአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ጭብጥ ለመለየት ከመጥቀሙም ባሻገር፣ እንደ ቶማስ ኬን ደፋር ስህተት ከመስራት እንደሚታደግም መጠቆም መልካም ነው፡፡ በመሆኑም፣ የብርሃኑ ገበየሁ ጥናትን በተመለከተ ከአካሄዱም ሆነ ከግኝቱ ጠብ የለኝም፡፡

በሌላ በኩል፣ የብርሃኑን ጥናታዊ ጽሁፍ ተጠየቂያው በሆነ መንገድ ሥናነበው፣ “ተረት ተረት የመሰረት” መጽሐፍ ለምን እንደልተካተተ ጠንከር ያለ ጥያቄ እንድናነሳ ይገፋፋናል፡፡ ጥናቱ የሀዲስን ሁሉንም ሥራዎች ሲነካካ፣ አንድም ቦታ ላይ “ተረት ተረት የመሰረት” ሊያወሳው አልፈለገም፡፡ መጽሐፉ፣ የደራሲው አንድ የልቦለድ (fiction) ሥራ እንደመሆኑ መጠን ቢያንስ፣ ለምን በጥናቱ እንዳልተካተተ ጥቆማ የሚያስፈልገው ይመስለናል (በርግጥ በብርሃኑ ጥናት ላይ “ልቦለድ” የሚለው (Novel) የሚለውን ተክቶ የገባ ስለሚመስል፣ ጥያቄዎ የአጥኒውን የምርጫ ጉዳይ የተፈታተነ ሊመስል ይችላል)፡፡

በሀዲስ አለማየሁ ሥራዎች ላይ፣ “ልቦለድ እንደ ርዕዮተ ዓለም” የሚል ጥናት የሚያቀርብ አካል፣ ስለ ልቦለዳዊ ተረቶቻቸው ምንም ሳይል ካለፈ፣ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም፣ በጥናታዊ ጽሁፉ ረቀው የወጡት፣ ጭምቅ ሀሳቦች እና ከእነዚህ ጥልቅ ፍልስፍናዎች ተደምሮ (synthesis) የተገነባው የደራሲው ርዕዮተ ዓለም በተረቶቹ ውስጥ በብልሃት ይሁነኝ ተብለው ተፅፈው እናገኛቸዋለንና፡፡ እንደውም፣ በልቦድ ሥራዎቻቸው ገዝፎ የወጣው የቅኝ አገዛዝ ጣጣ፣ ይሁነኝ ብለው የዓለምን ህብረተሰብ ለማስተማር፣ በሰው ልጆች መካከል ያለን የዘር መድሎ ለመዋጋት ወዘተ. ተረት በመተረት (በመጻፍ) ሊወጡት ቀድመው እንደተጉ እ.ኤ.አ በ1949 “በኢንተርናሽናል ሀውስ” መጽሔት በእንግሊዝኛ ያሳተሙት ተረት ዋቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተረቶች በጥናቱ ያልተካተቱ እንደ ሃገርኛው ብሂል “ተረት” ናቸው ተብለው ታልፈው ይሆን? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ? ተብሎ ቢጠየቅ አግባብ ነው፡፡

(ሳምንት  ተረቶቹን እናስተነትናለን፡፡)

 

 

 

Read 6500 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:45

Latest from