Saturday, 20 December 2014 12:47

ይድረስ ለህፃናት መምህራን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ህፃናትን በፍቅር እናስተምራቸው”

     ልጆቼ የአምስትና የሶስት አመት ህፃናት ናቸው፡፡ የሚማሩት አንድ ትምህርት ቤት ሲሆን ትልቋ መካከለኛ የመዋዕለ ህፃናት፣ ትንሿ ደግሞ ጀማሪ የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከአንደበታቸው የማይጠፉ ሁለት አባሎች አሉ - “loser” እና “ shame on you” የሚሉ ናቸው፡፡ አንድ ቀን እኒህን አሉታዊ አባባሎች ከየት እንዳመጧቸው ስጠይቃቸው፣ ከትምህርት ቤት መሆኑን ነገሩኝ - ያውም ከመምህራኖቻቸው፡፡
ልጆቼ በሚማሩበት ት/ቤት መምህራን የህጻናቱን የዕለት ውሎ ለወላጆች ሪፖርት የሚያደርጉበትና ወላጆችም መመልከታቸውን ከአስተያየት ጋር (ካላቸው ማለት ነው) አክለው ፈርመው የሚልኩበት “ኮሙኒኬሽን ቡክ የሚሉት ትልቅ ጥራዝ አለ፡፡ በሌሎቹም የግል ት/ቤቶች ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ በመጀመሪያዋ ልጄ የ “ኮሙኒኬሽን ቡክ” ላይ ዲሲፕሊን በሚለው ስር “ጥሩ” የሚል አስተያየት ሰፍሮ በማየቴ (ከወትሮው ዝቅ ያለ ነው) ምክንያቱን ጠየቅኋት፡፡
እሷም “ግድግዳ ላይ ስለፃፍኩ ነው…” አለችኝ
“ይቅርታ ጠየቅሽ?”
“አዎ፤ መጀመርያ የቅጣት ወንበር ላይ ተቀመጥኩና የክፍል ልጆች ጮክ ብለው “loser እና  shame on you” እንዲሉኝ ሚስ አዘዘቻቸው፡፡ ከዚያም ሚስን ይቅርታ ጠይቄ ወደ መቀመጫዬ ተመለስኩ” በማለት ሂደቱን አስረዳችኝ፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ነገር ሰምቼ ስለማላውቅ ደነገጥኩ፡፡ ሃሳብም ገባኝ፡፡ “አንቺም ሌሎችን እንደዛ ብለሽ ታውቂያለሽ?” ጠየቅኋት፤ ልጄን፡፡ “አዎ ብዙ ቀን እከሌ እና እከሌን ብለናቸዋል”፡፡ የልጄ መልስ ነበር፡፡ በከተማችን በሚገኙ አምስት የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪ የሆኑ ህፃናትን ጠይቄ ድርጊቱ በእነሱም ት/ቤቶች እንደሚፈፀም ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ልጆች በስነስርአት ታንፀው እንዲያድጉ ከተፈለገ፣ ያጠፉት ጥፋት ምን እንደሆነ በትክክል ተረድተው፣ ከጥፋታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅጣት ያልተገባ ባህርይን ወይም ድርጊትን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ እንደሚያግዝ አያከራክርም፡፡ ሆኖም በተለይ በህፃንነት ዕድሜ ባሉ ተማሪዎች ላይ የሚፈፀመው ቅጣት ጥንቃቄ የተሞላበትና ያልተፈለገ ውጤት የማያመጣ መሆን ይገባዋል፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በልጆች ስነልቦና ላይ የሰሩትና በሙያቸው መምህር የሆኑት አቶ ማናዬ አደላ፤ ህፃናትን እንዴት ከጥፋት እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ፤ “የመጀመሪያው አማራጭ የህፃናትን መልካም ስነምግባር ማበረታታት፣ ህፃናቱ ጥሩ ባህርይ እንዲላበሱ ያደርጋል፤ እግረመንገዱንም መጥፎውን እንዳይቀጥሉበት ይከለከላል፡፡ ነገር ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከስነ ምግባር ውጭ የሆኑ ነገሮችን መልመዳቸው ስለማይቀር ተገቢ ማረሚያ መንገዶችን መጠቀም ይገባል፡፡ ከማረሚያ መንገዶቹ አንዱ ቅጣት የምንለው ነው፡፡” የሚሉት አቶ ማናዬ፤ በስነልቦና ሙያ ቅጣት ሁለት አይነት ነው፡- አዎንታዊና አሉታዊ ቅጣት” በማለት ያብራራሉ፡፡
“አሉታዊ ቅጣት በድርጊት (አካላዊ ቅጣት ማለት ነው) ወይም በቃላት የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ ቅጣት አካላዊ ጉዳትና ስነልቦናዊ ተፅዕኖ ስላለው በፍፁም አይመከርም፡፡ አዎንታዊ ቅጣት የሚባለው ምንም አይነት ስነልቦናዊና አካላዊ ጉዳት በህፃናቱ ላይ ሳያደርሱ፣ ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ውጪ የሆኑ ነገሮችን እንደ መቀጣጫ በማስቀረት ስህተታቸውን  ደግመው እንዳይፈፅሙ ማስተማር አይነት ዘዴዎችን ያካተተ ነው፡፡” ይላሉ - ባለሙያው፡፡   
በህፃናት ላይ የሚሰነዘር ስድብና ማላገጥ የህፃናቱን በራስ የመተማመን መንፈስ ይጎዳል፣ ከሌሎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባ መቀራረብን ያሳጣል፣ ለትምህርት ያላቸውን ተነሳሽነት ይገድለዋል፣ ፍርሀት በውስጣቸው  እንዲፈጠር በማድረግ የፈጠ አቅማቸውን ያዳክማል ያጠፋል ፣ ሌሎች ነገሮችን እንዳይሞክሩ ያደርጋል፣ የበታችነት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከዚያም አልፎ ትምህርት ቤትን እንዲጠሉና አንሄድም እንዲሉ ያደርጋል፣ የቀጣውን አስተማሪ ከእነሚያስተምረው ትምህርት ጭምር እንዲጠሉ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ህፃናት መቀጣት ያለባቸው በመምህራቸው ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው፤ ተማሪን እያስጨበጨቡ  በቅጣት ላይ ማሳተፍ በተለይ በአቻ እድሜ ላይ ሲሆን የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነው ባይ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች  በመምህራቸው ትዕዛዝ የክፍላቸውን ተማሪ  “loser” እና  “shame on you” የመሳሰሉ አባባሎችን በመጠቀም እንዲያሾፉበት ሲደረግ ተማሪው ላይ የበታችነት ስሜት ይፈጠራል፤ ይህ ደግሞ በህፃናት ላይ መፈፀም ከሌለባቸው ድርጊቶች አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም የበታችነት ስሜት የሚሰማው ህፃን ተወዳዳሪነቱ ይቀንሳል፣ በራስ የመተማመን ስሜት ያጣል፣ በአጠቃላይም እጅግ አፍራሽ ውጤት የሚያስከትል ድርጊት ነው ይላሉ፤ አቶ ማናዬ፡፡ከሁለት አመት እስከ ሰባት አመትና ከሰባት እስከ አስራ አንድ አመት ያሉት ጊዜያት እጅግ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው፣ በህፃናት እድገት ላይ ወሳኝ ጊዜያት ናቸው ያሉት ባለሙያው፤ በዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ እጅግ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚባሉ የእድሜ ደረጃዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ ይህ እድሜ የልጆችን ሁለንተናዊ እድገት ማበረታቻ እንጂ ማጨናገፊያ መሆን የለበትም፡፡ አስተማሪዎች እጅግ ብልጠት የታከለበት ቅጣትን በመጠቀም ተገቢ ያልሆኑ ባህርያትን ማረም እንዳለባቸውም ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
 የልጆቼ ትምህርት ቤት ሄጄ ዳይሬክተሯን አነጋግሬ ነበር፡፡ “ልጆች እንዴት ከትምህርት ቤት ስድብ ተምረው ይመጣሉ፤ ስድቦቹ ለመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለአዋቂም እንኳን እጅግ የሚያሸማቅቁ ናቸው፣ እንዲህ አይነት አባባሎች በትምህርት ቤቱ እንዳይበረታቱ ሊደረግ ይገባል” በሚል ያቀረብኩትን ሃሳብ በቀናነት ተቀብለውኛል፡፡ ለመምህራኑ ተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ዳይሬክተሯ ጠቁመውኛል፡፡ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንዲህ ያለ የህፃናትን በራስ የመተማመን ስሜት የሚጐዳ ስድብና ድርጊት ከመፈፀም በመታቀብ፣ ያጠፉ ህፃናትን አስተማሪ በሆነና ሰብዕናቸውን በማይጐዳ መልኩ መቅጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ህፃናትን መስደብና ማሾፊያ ማድረግ በትምህርታቸውና በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል መገንዘብ ይገባል፡፡  ህፃናትን በፍቅር እናስተምራቸው!!

Read 3964 times