Saturday, 27 December 2014 16:09

ጭውውት 12፤ማርጀት፣ መሞት፣ ወዘተ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

     ሂሳብ፣ የዛሬው የመጨረሻው ጭውውታችን ነው፣ ማርጀትና መሞትን የሚመለከት፡፡ ጥናቱን የሚያቀርብልን ጓድ አስተዳደር ነው፡፡ መድረኩ ይኸውልህ!
ኬሚስትሪ፣ ጓድ ሰብሳቢ፣ ይህ አርእስት ስጋት ላይ ጥሎኛል፣ ማለቴ ጡረተኛ ስለሞት ማውራት አለበት እንዴ? እንደኔ ከዚህ አርእስት መራቅ ይሻላል!
ምህንድስና፣ አቤት ፍርሃት! አይዞህ ጭውውቱን እስክንጨርስ አትሞትም፣ ለማናቸውም ብትሞትም አንዴ ነው፣ ደግመህ ትሞትም፡፡ ስለዚህ ፍርሃትህን ወደ ጎን አድርገው፡፡
አስተዳደር፣ ጓዶች፣ አርእስቱን እንተወው ለማለት ትንሽ የዘገየ ይመስለኛል፡፡ እኔም እኮ የማይናቅ ጊዜ መሰናዶው ላይ አጥፍቻለሁ፡፡
ሂሳብ፣ መልካም፣ በል ጥናትህን አቅርብልን፡፡
አስተዳደር፣ በመጀመሪያ ሦስታችሁንም ለማመስገን እፈልጋለሁ፣ የሚነበቡ ፅሁፎች ባትሰጡኝ ኖሮ በፍፁም ልወጣው ባልቻልኩ ነበር፡፡
በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፣ ስለ ፕሮቶን፣ ኤሌክትሮን ባላወራሁም ነበር፡፡ እስቲ ከመሰረቱ ልጀምር፡፡ ሳይንስ ሲያስተምረን ሁሉ ነገር፣ ማለትም ከድንጋይ እስከ ሰው ያለው ሁሉ የተገነባው ከአቶሞች እንደሆነ ነው፡፡
አቶሞች በተራቸው ከፕሮቶኖችና ኤሌክትሮኖች የተነቡ ሲሆን፣ ፕሮቶኖች ከኳርክ ዝርያዎች ተቀነባብረው የተሰሩ ናቸው፣ ኤሌክትሮን ግን እራሷን የቻለች ናት፡፡ ጓዶች፣ ከወር በፊት “ኳርክ” ምንድነው ብትሉኝ ኖሮ፣ እንቁራሪት የሚያሰማው ድምፅ    ነዋ! እል ነበር፡፡ እንደምታዩት እኔም መጠነኛ ትምህርት ቀስሜያለሁ!
የሚነሳው ጥያቄ የአቶሞች ዕድሜ ስንት ነው? ያረጃሉ ወይ? የሚል ነው፡፡ የፊዚክስ ባለሙያዎች ሲያስረዱ፣ የፕሮቶን እድሜ 1031 ዓመታት (ማለትም 10 ሚሊዮን፣ ሚሊዮን፣ ሚሊዮን፣ ሚሊዮን፣ ሚሊዮን) ሲሆን ኤሌክትሮን ግን ጨርሶ የማትለወጥ ናት፡፡
ታዲያ ይኸ እንዲህ ከሆነ በአቶሞች የተገነቡት ሀዋሳ፣ ብሎም ተክሎችና እንስሳት እንዴትና ለምን ማርጀት ቻሉ? አንዳንዶች ሲያስረዱ፣ ህዋስ ከአቶም የበለጠ ውስብስብ፣ እንቁራሪት (የህዋሳት ስብስብ) ከአንድ ህዋስ የበለጠ ውስብስብ ናቸው፡፡ እነኚህ ምሁራን እንደሚሉት ውስብስብነት (ኮምፕሌክሲቲ) ወደ ህይወት ያመራል፣ አይቀሬ ነው፡፡ ህይወት ወደ ሞት! ይህ አባባል ወደ ፍልስፍናው የሚያደላ ስለሚመስል ባንገፋበት ይሻላል፡፡
ባለአንድ ህዋስ ባክቲሪያም እኮ ታረጃለች፣ ማለትም ውስብስብነት በይፋ የማይታይበት፣ ለምን? እርጅናን የሚቆጣጠሩ ጂኖች አሉ? አንዳንድ ሰዎች እስከ 130 ዓመት እንደሚኖሩ የታወቀ ነው፣ ባካባቢያቸው ምክንያት ይሆን? ብዙ ጊዜ እነኚህ ሰዎች ዳገትማ ስፍራ፣ ንፁህ አየርና ውሃ በሚገኝበት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ለምግባቸውም ከስጋ ይልቅስ ተክሎችን ያዘወትራሉ ይባላል፡፡ ተክሎችን ስንመለከት፣ በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ “ሴኮያ” የተባለ ዛፍ እስከ 3,800 ዓመት እንዲኖር በተደረገ ምርምር በ C-14 እና ከግንዱ ቀለበቶች ቁጥር ተረጋግጧል፡፡
የዚህ ዓይነት ዛፍ፣ ትልቅና ረጅም ዕድሜ ያለው የግንዱ ግማሽ - ወገብ ስፋት (ሬዲየስ) 4,85 ሜትር፣ ዙሪያ ርቀት (ሰርከምፈረንስ) 30 ሜትር፣ የቅርፊት ውፍረት 61 ሴንቲሜትር መሆኑ ታውቋል፡፡ እርግጥ፣ ሴኮያ በንግዱ መወፈርና በቅርፊቱ ደንዳና መሆን ምስጥ፣ ዝናብ፣ በረዶ ሊያጠቁት የቻሉ አይመስልም፡፡ ሌላው የዛፉ ከፍታ ቦታ በማደግ ከእንስሳት መራቁ ነው፡፡ ከሴኮያ ህዋሳት የምንማረው ይኖራል?
[“ከዚህም ከዚያም” (የ4 ጡረተኞች ጭውውት) ከተሰኘው የፕሮፌሰር ግርማ ሙልኢሳ መፅሃፍ የተቀነጨበ]

Read 6494 times