Saturday, 27 December 2014 16:11

በሲጋራ ላይ የወጣው ህግ በቅርቡ ይተገበራል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ታዳጊዎች ለማጨስ እንዳይበረታቱ ከፍተኛ ቀረጥ ሊጣል ነው
በፓኬት እንጂ በነጠላ መሸጥ ሊከለከል ነው

    የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ላይ በአገሪቱ የሲጋራ አጫሹ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሲጋራ ምርት ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እንደሚመጣል ተጠቆመ፡፡
በ2003 ዓ.ም የተደረገውን የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት (DHS) ዋቢ በማድረግ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች እንደተመለከተው፤ የአጫሾች ቁጥር ወደ ስድስት ሚሊዮን ገደማ ይሆናል፡፡ ከአጫሾቹ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወንዶች ቢሆኑም የሴት አጫሾች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ የሲጋራ ፍላጐትም ወደ 5 ቢሊዮን ፍሬ ደርሷል ተብሏል፡፡
ከአገሪቱ አጠቃላይ የሲጋራ ፍላጐት 53 በመቶ ያህሉ የሚሸፈነው በብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ሲሆን 4.6 በመቶ ከውጪ በማስገባት፣ 38 በመቶ ደግሞ በኮንትሮባንድ (ህገወጥ) ንግድ ነው፡፡ ትምባሆ፤ ሱስ አስያዥ የሆነውን ኒኮቲን የተባለ ንጥረ ነገር ጨምሮ ከአራት ሺህ በላይ ኬሚካሎችን በውስጡ ይይዛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 250 ያህሉ እጅግ አደገኛ ኬሚካሎች ሲሆኑ 50 የሚደርሱት ደግሞ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት ተወካዩ አቶ ዋሲሁን መላኩ ተናግረዋል፡፡
አዕምሮአችን የተስተካከለ ጤና እንዳይኖረው ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ሱሰኝነት ነው ያሉት ዶክተር ሙሴ ገብረሚካኤል፤ በትምባሆ ውስጥ የሚገኘውና ኒኮቲን የተባለው ንጥረ ነገር አንጐላችን ውስጥ የተለያዩ ለውጦችን በመፍጠር አንጐላችንን የኒኮቲን ጥገኛ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ትንባሆ ውስጥ የሚገኘው ሱስ አስያዥ ኒኮቲን መጠኑ እየጨመረ በመጣ ቁጥር  ለአዕምሮ ህመም እንዲሁም ለሞት የመጋለጥ እድል እንደሚጨምር ገልፀዋል፡፡
መከላከል እየተቻለ ለሞት መንስኤ ከሚሆኑ የአለማችን የጤና ጠንቆች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ትምባሆ፤ ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ ህመም፣ ለተለያዩ ካንሰር ህመሞች፣ ለአይን ሞራ ግርዶሽ፣ ለጥርስ መበስበስ፣ ለጨጓራ ቁስለት፣ ለአንጐል በሽታ፣ ለጋንግሪንና ለስንፈተ ወሲብ እንደሚያጋልጥም የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡
በ2013 የተደረገና በአለም ጤና ድርጅት ይፋ የሆነ የጥናት ውጤት እንደሚጠቁመውም፤ በአለማችን በትምባሆ ሣቢያ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በኤድስ፣ በትራፊክ አደጋ፣ በአደንዛዥ እፅ፣ በግድያ ወንጀልና ራስን በማጥፋት ከሚሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ድምር ይበልጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 1.3 ቢሊዮን የትምባሆ ተጠቃሚዎች የሚገኙ ሲሆን በየዓመቱም 5 ሚሊዮን የሚሆኑት በትምባሆ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ የሟቾቹ ቁጥር ካደጉት አገራት ይልቅ ገና በማደግ ላይ ባሉት አገራት ይጨምራል፡፡
በአገራችን ትምባሆ በተለያዩ መንገዶች በጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ማጨስ፣ ማኘክ፣ መታጠንና ማሽተት ዋንኞቹ የትምባሆ ተጠቃሚዎች የሚያዘወትሯቸው መንገዶች ናቸው፡፡ በተለይ ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች በማኘክና በማሽተት የትምባሆ ተጠቃሚ መሆን የተለመደ ነው፡፡
በከተሞች አካባቢ በፋብሪካ የሚዘጋጁ የትምባሆ ምርቶች የሚዘወተሩ ሲሆን በብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል የሚመረቱት ግስላ፣ ኒያላ፣ ኢሌኒና ዲላይት የተባሉት የሲጋራ አይነቶች ገበያውን በከፍተኛ ደረጃ ተቆጣጥረውታል፡፡  
ማልቦሮ፣ ዊንስተን፣ ሮዝማን፣ ኤል ኤንድ ኤም እና ኬንት የተባሉት የሲጋራ አይነቶች ደግሞ በህጋዊ መንገድና በኮንትሮባንድ ከውጪ አገር እየገቡ ለአገራችን ገበያ የሚቀርቡ የሲጋራ አይነቶች ናቸው፡፡
የትምባሆ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የታክስ ገቢ በማስገኘት ለአገሪቱ የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም የሚያስከትለው ችግርና የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ፣ በትምባሆ ሣቢያ የሚሞቱ ዜጐችን መታደግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ፣ ህግ አውጥቶ፣ አሠራሩን መቆጣጠር እንዳስፈለገ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አማካሪ አቶ መንግስተአብ ወልደአረጋይ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ማጨስ በሚጀመርበት የወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ዜጐች ሲጋራ በቀላሉ ለማግኘት እንዳይችሉ በትምባሆ ላይ የሚጣለውን ታክስ ከፍ በማድረግ፣ የሲጋራ መሸጫ ዋጋን ለመጨመር የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎና ረቂቅ ህግ ወጥቶ በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ አማካሪው ጠቁመዋል፡፡ ህጉ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅ ለማስፈፀም ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ ህዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ በማውጣት አፅድቋል፡፡ በቅርቡም ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጀመር ሲሆን በትምባሆ ምርቶች ሽያጭ፣ ዝውውርና አጠቃቀም ላይ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
በአዲሱ አዋጅና መመሪያ መሰረትም፣ ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ ኒኮቲን መስጫ መሳሪያ ማምረት ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ ወይም በማንኛውም መንገድ ገበያ ውስጥ ማስገባት የተከለከለ ነው፡፡
የትምባሆ ምርቱ ለጤና አደገኛ መሆኑን የሚገልፅ የማስጠንቀቂያ ፅሁፍ የሲጋራ ባኮውን 30 በመቶው ያላነሰ ቦታ በሚሸፍን መልኩ መገለፅ ይኖርበታል፡፡ የትምባሆ ምርትን በችርቻሮ የመሸጥ ፍቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ምርቱን ለአይን በሚታይ መልኩ መደርደርና ገዥን መሳብ አይችሉም፡፡ የትምባሆ ምርት የሚሸጠው ባልተከፈተ ፓኬት ወይም ማሸጊያ ሲሆን ሲጋራን በነጠላ መሸጥ የተከለከለ መሆኑን አዲሱ አዋጅና መመሪያ ያዛል፡፡
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በትምባሆ ምርት ግዥም ሆነ ሽያጭ ላይ ተሳታፊ መሆን እንደማይችሉ የደነገገው አዲሱ መመሪያ፤ የትምባሆ ምርት በችርቻሮ በሚሸጥበት ወቅት ሻጩ የገዥውን ዕድሜ ከተጠራጠረ ህጋዊ ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ ወይም የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ አይቶ ማረጋገጥ አለበት ይላል፡፡ አዲሱ መመሪያ ሲጋራ ማጨስ የማይፈቅድባቸውን ቦታዎች በዝርዝር የገለጸ ሲሆን፤ ሆቴሎች፣ የመጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ክለቦች፣ መዝናኛ ክበቦች፣ ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች፣ ሊፍቶች፣ መታጠቢያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎችና የንግድ መደብሮች፣ ሲኒማ፣ ቲያትርና ቪዲዮ ቤቶች፣ ሙዚቃ ማሣያ አዳራሾች፣ የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ የህዝብ ትራንስፖርቶች፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ማጨስ የተከለከለ ነው፡፡
አዲሱ ህግና መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ደንብና መመሪያውን በማይተገብሩ አካላት ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል፡፡ ከሶስት ወራት በኋላ በሚወጡ ፊልሞች ላይ ሲጋራ እንዳይጨስና የሚጨስባቸው አጋጣሚዎች ካሉም በፊልሙ ላይ የሲጋራን ጎጂነት የሚገልፁ ፅሁፎች በስክሪኑ ላይ እንዲጻፉ የሚያስገድድ አሰራርም እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

Read 6296 times