Saturday, 27 December 2014 16:27

ባለ ቆዳ ካልሲው

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(9 votes)

ድሮ ሰፈሩ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ድሮ፤ ከአስር አመት በፊት ሊሆን ይችላል፡፡ እልም ያልን አራዶች ነን የሚሉ ሁሉ የሚያዘወትሩት ስፍራ ነበር፡፡ አሁን አራዳ በሙሉ ተስፋ ቆርጧል፡፡ የአራዳ ልጅ ጊዜ አልፎበታል፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ መሆንም የሚያሳፍር የድሮ ዘመን ሰውነት ነፀብራቅ ተደርጐ ተወስዷል፡፡
አራዳ ነን የሚሉ ብዙዎች ተሰደዋል፡፡ ያልተሰደዱት በከፍተኛ ሱስ ተጠምደዋል፡፡ አራዳ  ለመስራትም ሆነ ለመስረቅ አቅም የለውም፡፡ አራድነት በምላስ ይታወቅ ነበር መጀመሪያ ላይ፡፡ ምላስም ግን በመጤዎቹ ተበለጠ፡፡
ድሮ ሰፈሩ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ድሮ፤ ከአስር አመት በፊት ሊሆን ይችላል፡፡ እዚሁ ሰፈር ውስጥ ተቀምጠው ሲቅሙ በሚውሉበት አንድ ትንሽ ጫት ቤት ውስጥ አንድ እንግዳ ሰውዬ በሩን ከፍቶ ከእለታት አንድ ቀን ገባ፡፡
የሰፈሩ ነባር የሆኑት መጤን አይወዱም፡፡ አያምኑም፡፡ መጤ ሁሉ ወራሽ ነው የሚመስላቸው፡፡ የሚወረስ ነገር ባይኖራቸውም እንኳን መጤን ይፈራሉ፡፡ መጤ በሙሉ ገጠሬ ነው፡፡ ይሄንንም ጐልማሳ ገና ከመግባቱ ፊት ነሱት፡፡ ጠጋ ብለው ሊያስቀምጡትም አልፈቀዱም፡፡ ጫት ሻጩ ራሱ ከሚያውቀው ሰው በስተቀር ማስተናገድ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ጐልማሳው ቢጫው ጄሪካን ላይ ተቀመጠ፡፡
“ምን አይነት?”      
“እነሱ የያዙትን አይነት”
“የምትፈልገውን ሳታውቅ ነው እንዴ ልትቅም የመጣኸው!?”
“ቅሜ አላውቅም…ቅሜ አለማወቄ ወንጀል ነው”
ጫት ቤቱ ውስጥ የተኮለከሉት አድፍጠው እያጠኑት ነው፡፡ ገጠሬ አለማወቁን ማሳወቅ አይፈልግም፡፡ ከድቁናው ቀድሞ ቄስ መምሰል ይፈልጋል፡፡ አጉል አራዳ በመሆን ነው ፋርነቱን በራሱ እጅ የሚያጋልጠው፡፡ ይሄኛው ለምን ራሱን በማጋለጥ እንደጀመረ አልገባቸውም፡፡
“ወንጀል አይደለም…የሚጣፍጠውን ስጠው…የተቀቀለውን ይስጥህ ወይንስ የታጠበውን?” ተስፋ ከቆረጡት አራዶች አንዱ ጠየቀው፡፡
“የትኛው ይሻለኛል?” እያገዙት በመሆኑ ተደስቷል፡፡ አዲስ የቆዳ ጫማ ነው ያደረገው ግን ጫማው ጠቦታል፡፡ የገበሬ እግሩ ጫማውን አፈንድቶ ራሱን ነፃ ለማውጣት እየታገለ ይመስላል፡፡ ካልሲ አላደረገም፡፡ በሱሪው ያልሸፈነው የእግሩ ቆዳ እንደ አውራሪስ ቆዳ ወፍራም እና ግራጫ ነው፡፡
አራዳው ሊያማርጠው ተነሳ፡፡ ከጀንቡ ውስጥ ጫት እያወጣ ገለፃ መስጠት ጀመረ፡፡
“ይኼኛው የሚያዘፍን ነው…ይኼኛው የሚያሳስብ…ይኸውልህ ይሄ ደግሞ ፍቅር የሚያስይዝ ጫት ነው…ፎቅ እና መኪና የምትፈልግ ከሆነ ደግሞ እቺኛዋን ቃም…”
“የሚያዘፍነውን ስጠኝ - ዘፈን እወዳለሁ”
“ዝህ!” ትልቁን እስር ሰጠው፡፡
የተሰጠውን ይዞ ቀረ፡፡ አራዳው ተመልሶ ተቀመጠ፡፡ በአራድነት የሚበልጠውን በማግኘቱ ደስ ብሎታል፡፡ ግን የተበለጠ መስሎ ለመብለጥ እንደመጣ አውቋል፡፡ ባላወቀ ሙድ መሀላቸው ሊገባ ነው፡፡
የተሰጠውን እስር እንደያዘ ቀረ፡፡ ወደ አራዶቹ ተመለከተ፡፡ እነሱ እንደሚያደርጉት ጫቱን ከፊት ለፊቱ አስቀመጠ፡፡ የጫት እግር መዘው ሲያወጡ አወጣ፡፡ ቀንበጥ ቀንበጡን ሲቀነጥሱ እሱም በጠሰ፡፡ ሲጐርሱ ጐረሰ፡፡በፊቱ ላይ በሚያሳየው ገፅታ ጫቱ በጣም እንደመረረው ያስታውቃል፡፡ ኮካ ይምጣልህ? ተባለ፡፡
አዎ እንደማለት ተወዛወዘ፡፡ ኮካው ሲመጣ በአንድ ትንፋሽ ግጥም አድርጐ ጨረሰወ፡፡ “ጨምርልኝ” አለው ባለ ጫቱን፡፡ የትንሿ ጫት ቤት ብዙ ጭንቅላቶች በጐልማሳው ላይ ተነጣጥረዋል፡፡ ሁለተኛ ኮካ ተከፈተለት፡፡
ቅድም ጫት ያማረጠው አራዳ “ማንም አይጠጣብህም እኮ ቀስ ብለህ ተጐንጭ” አለው፡፡ ጐልማሳው እሺ አለ፡፡
ትንሽ ሲያመነዥግ ከቆየ በኋላ፤
“ልዋጠው ወይንስ ልትፋው?” አለው ለመካሪው አራዳ
“ከዋጥከው የሆድ ቁርጠት ይይዘሃል…ከተፋኸው ደግሞ የሉሉ ትከፍላለህ” አለው ያኛው ቀልጠፍ ብሎ፡፡
ጐልማሳው ማመንዠጉን ቀጠለ፡፡ ኮካውን ቀስ ብሎ ጠጣ፡፡ የጐረሰውን ጫት ሳይተፋም ሳይውጥም ማኘኩን ገፋበት፡፡
ሬዲዮው ከፍ ተደረገ፡፡ የአራዶቹ ሳቅ እና ቀልድ እሱ ላይ መሆኑ አልተሰማውም ወይንም አልገባውም፡፡ አንድ ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተሰጠውን ጫት ግጦ ጨረሰው፡፡ ሲውጥም ሆነ ሲተፋ አልታየም፡፡ አይኑ ፈጠጠ፡፡ የት እንዳለ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እጁን አሻሸ፡፡
“አሁን በጣም ደስ አለኝ” አለ፡፡ አራዶቹ “እንኳን ደስ ያለህ” አሉት፡፡ “ይድፋህ” ከማለት በተስተካከለ ቅላፄ፡፡
“እስክስታ ልውረድ?” ብሎ አስፈቀዳቸው፡፡ ውረድ አሉት፡፡ ተነስቶ በጠባቧ ጫት ቤት ውስጥ እየተሽከረከረ እስክስታ መታ፡፡ ጉንጩ ውስጥ የያዘው ተክዚና ፊቱ በየትኛው ጐን እንዳለ ያምታታል፡፡ እስክስታ ሲወርድ አጨበጨቡለት፡፡ ሲጨርስ ሌላ ዘፈን ጀመረ፡፡ ልቀጥል? ብሎ አስፈቀዳቸው፡፡ ቀጥል አሉት፡፡ ላቡ ጠብ እስኪል ትከሻውን ሰበቀ፡፡
ጫት ሻጩ ተቆጣ፡፡ “ይሄ ጭፈራ ቤት…ናይት ክለብ አይደለም! አርፈህ ቁጭ በል ወይ ውጣ!” አለው፡፡ እሺ ብሎ ተቀመጠ፡፡
አራዶቹ ለሻጩ አስረዱት “ጫት ቅሞ ስለማያውቅ ምርቃና እንደ ስካር መስሎት ነው…ተጠጥቶ እንደሚደነሰው ተቅሞ የሚደነስ መስሎት ነው” አሉት፡፡ እነሱን እንዳሳቃቸው እሱን አላሳቀውም፡፡     
ተቀመጠ፤ ላቡን እየጠረገ፡፡ ዘፈኑ ተቀነሰ፡፡ “ሌላ ጫት ይጨመርልኝ” አለ፡፡
“ቅድም ያደቀቅሕውን መጀመሪያ ክፈል” ተባለ፡፡ የሱሪ ኪሱ ውስጥ ሲገባ ብዙ መቶ ብሮች ይዞ ወጣ፡፡ ለራሱም ለሌሎችም አዘዘ፡፡ አንድ ዙርባ ጫትን እንደ አንድ ጠርሙስ ቢራ ነው የቆጠረው፡፡ ሩብ ጫት የጠረረበት የሰፈር አውደልዳይ፤ አንድ ሙሉ ጫት ሲሰጠው እየተቀበለ ጥጉን ያዘ፡፡
“በጣም ደስብሎኛል” አላቸው ጐልማሳው
“ለምን?” አሉት፡፡
“ሎተሪ ስለደረሰኝ” አላቸው፡፡
“ስንት ደረሰህ?” ሎተሪውን አውጥቶ አሳያቸው፡፡ ሎተሪ የደረሰው ሰው በዝቅተኛ ገንዘብ (በሁለት ሺ ብር) የአንድ ማሊዮን ብሩን ሎተሪ እጣ እንደሸጠለት ነገራቸው፡፡
“እንኳን ደስ አለህ” ብለው ጨበጡት…የደስ ደስ ሁሉንም ሊጋብዝ እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ አብሽር አሉት፡፡
በቃመ ቁጥር ደስታው እየናረ በመምጣቱ፣ ምን ማድረግ እንዳለበት ጨነቀው፡፡
“ጨመቅ አድርገህ ቃም፤ ውሀም አብዝተህ ጠጣ” አሉት፡፡
“አብዝቼ ካልጠጣሁስ?”
“አልወጣ ይልህና…በኋላ በቪኖ መክፈቻ ካልሆነ ሰገራህ አይወጣም”
ሳቁበት፡፡ ሳቀላቸው፡፡
ካልሲ ከሚያዞር ሱቅ በደረቴ በጫት ቤቱ መስኮት ነጭ ካልሲ ገዛ፡፡ “ካልሲ ምን ያደርግልሃል… አንተ እኮ ምርጡን ካልሲ ነው የለበስከው”
“እውነታችሁን ነው…አዲስ ጫማ በአዲስ ካልሲ ካልተደረገ ይሸታል ብለውኝ እኮ ነው”
“የሚናገሩትን አያውቁም ይቅር በላቸው…የአንተ ካልሲ በአለም ዙሪያ ተፈልጐ አይገኝም፡፡ አንተ እኮ የማያረጅ፣ የማይሰፋ፣ የማይቆሽሽ ካልሲ ነው ያደረግኸው…የጨርቅ ካልሲ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ አንተ የሌዘር ካልሲ ነው ያደረከው” ጐንበስ ብሎ እግሩን አይቶ፣ በተፈጥሮ ካልሲው ተኩራራ፡፡
“ይልቅስ በነፃነት መደነስ ከፈለክ፣ በባንድ የሚቃምበት ቤት ስላለ እዛ ይዘንህ እንሂድ
…በብራስ ኦርኬስትራ ሌሊቱን ሙሉ እየተቃመ የሚጨፈርበት ቤት ነው”
“አሁኑኑ እንሂድ” ብሎ ተፈናጥሮ ተነሳ፡፡
“ቆይ ተረጋጋ እንጂ በባንድ የሚቃምበት ቤት ሌሊት ነው የሚከፈተው… በዚያ ላይ ሴቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ሴቶቹ እንዲወዱህ ፍቅር የሚያሲዘውን ጫት እየቃምክ ቆይ፡፡ ፍቅር የሚያሲዘውን ጫት ስትጨርስ ፎቅና መኪና የሚያስገዛውንም ብትሞክር አይጐዳህም…”
“ልክ ነው…መኪና መግዛት አለብኝ፡፡ የሎተሪውን ብር ተቀብዬ ስመለስ ሚስትም ገዝቼ ወደ ሀገሬ ብገባ ማለፊያ ነው”
“ሴቶች ደግሞ መኪና ይወዳሉ ታውቃለህ አይደል…የእኛ የወንዶች አይን የተሰራው ከሴቶች ዳሌ እንደሆነው ሁሉ…የሴቶች አይን ደግሞ የተሰራው ከመኪና እቃ ነው…ለዚህ ነው መኪና ሲያልፍ አይናቸውን መንቀል የማይችሉት…እኛም ወንዶች ሴቶች ሲያልፉ አይናችንን ከዳሌያቸው ላይ መንቀል አንችልም አይደል?”
“ልክ ነህ…በደንብ ነው ነገሮችን የገለፅክልኝ…ስለዚህ መኪና መግዛት ይቀድማል ማለት ነው?”
“እንደ ምርጫህ ነው…በባንድ የሚቃምበት ቤት መዝናናት…ወይንስ ሴቶችን ማዝናናት ወይንስ መኪና?”
“መኪና ስንት ነው ዋጋው? አንድ ሚሊዮን ብር ነው የደረሰኝ”
“አንድ ሚሊዮን ብር … አንድ ሚሊዮን መኪና መግዛት ይችል ነበር…ችግሩ ጐማው ነው፡፡ መኪና ያለ ጐማ አይሽከረከርም… ጐማ በጣም ውድ ነው፡፡ ጐማው ለምን መሰለህ ውድ የሆነው? ባዝሊን ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ባዝሊን ሀገር ውስጥ አይመረትም፤ የማመጣው ከአውስትራሊያ ብቻ ነው፡፡ ባዝሊን ካልተቀባ ጐማ አይሽከረከርም፤ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ መኪና ሳይሆን ባዝሊን ነው…” አለው አራዳው፡፡
“ስለዚህ ምን እንዳደርግ ትመክረኛለህ?” አለ ባለ ሌዘር ካልሲው፡፡
“እኔ እንዳጋጣሚ ባዝሊን በርካሽ ዋጋ የሚሸጥ ሰው አውቃለሁ፡፡ ሰውየው ሀገር ጥሎ ሊሄድ ስለሆነ የባዝሊን በርሜሎቹን የሚገዛው ሰው ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ በደንብ አስብበትና ባዝሊን ንግዱን ተረክቤ ልስራ የምትል ከሆነም ትችላለህ…አይ ተዝናንቼ ወደ ሀገሬ የሎተሪ ሽልማቴን ይዤ ልግባ ካልክም ያንተ ምርጫ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን በደንብ አስቦ ለመወሰን እንዲረዳህ…ከዚህ ቤት ከመውጣትህ በፊት የማሰላሰያ ጫቱን አንተም እኔም ብንቅም ጥሩ ነው…ከዛ ማታ ተያይዘን በባንድ ወደሚቃምበት ቤት እንሄዳለን”
“በጣም ነው ደስ ያለኝ ዛሬ…ስለተዋወቅኋችሁ ደስ ብሎኛል…ሁላችሁንም፡፡ በተለይ አንተ ስምህ ማነው?”
“ስሜን አስይዘህ ትበደርበታለህ አልነግርህም” ሌሎቹ ሳቁ፡፡
“ስምህ ራሱ የገንዘብ እውቀት ባለው ሰው የወጣ እንደሆነ ያስታውቃል…አቶ አስይዘህ ትበደርበታለህ…የአያትህ ስምስ?”
“ፊት አውራሪ አልነግርህም…የአንተስ?”
“የእኔ ኮንስታብል ዘረ ያዕቆብ ነው…በባንድ ስለሚጨፈርበት ጫት ቤት እዚያው ፖሊስ ጣቢያ ትነግሩኛላችሁ…መኪና ይምጣና አንድ ላይ እንሄዳለን…” መታወቂያውን አውጥቶ አሳያቸው፡፡ እውነትም ፖሊስ ነው፡፡
 ፖሊስ ሲሆን ታዲያ ድንገት ቁጡ ሆነ፡፡ ፊቱ ጠበብ፣ ጫማው ሰፋ ያለ መሰለ፡፡
 

Read 4233 times