Monday, 29 December 2014 07:33

መንግሥት በባህርዳር ተቃውሞ ለተጎዱ ካሳ እንዲከፍል መድረክ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

መንግሥት የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል

    በባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግስት ካሳ እንዲከፍልና ጥቃቱን የፈፀመውን አካል ለፍርድ እንዲያቀርብ መድረክ የጠየቀ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ ጉዳቱ እየተጣራ ነው ብሏል፡፡ “በባህርዳር ከተማ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ባህሪ ነፀብራቅ ነው” ያለው ፓርቲው፤ ማንኛውንም የኃይል እርምጃ በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ በሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ የተወሰደው የኃይል እርምጃ በህገ መንግስታዊ የመቃወም መብት ላይ የተፈፀመ ጥሰት ነው ያለው መድረክ፤ ከዚህ ቀደምም የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ መሰል ተግባር ሲፈፀም መቆየቱን ጠቅሶ፤ “ጥቃቱ ኃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል አውግዟል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የመድረኩ አባላት በማዳበሪያ እዳ ሰበብ እየታሰሩ እንደሆነ የጠቆመው ፓርቲው፤ ድርጊቱ የሚፈጸመው አባላቱን ከግንቦቱ የምርጫ እንቅስቃሴ ለማራቅ በማሰብ ነው ብሏል፡፡ በባህርዳር ከእምነት ቦታ ጥያቄ ጋር በተገናኘ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳት ስለ መድረሱና ስለ እርምጃው ተገቢነት ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ጉዳት ስለመድረሱ መረጃው እንዳላቸው ጠቁመው የጉዳቱ ምክንያት ምንድን ነው የሚለው ተጣርቶ እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ “በፀጥታ ኃይሎች ነው የተከናወነው ወይስ የተለያየ የራሱ መንገድ አለው የሚለው ተጣርቶ የሚታወቅ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩ ተጣርቶ ውጤቱ በሚታወቅ ጊዜ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል፡፡


Read 1424 times