Monday, 29 December 2014 07:34

በእንግሊዛዊው ላይ የተፈፀመው ግድያ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

     ሠሞኑን በባህር ዳር ከተማ በእንግሊዛዊው የ50 አመት ጐልማሳ ቱሪስት ላይ የተፈፀመው ግድያ ሆን ተብሎ የተፈፀመ አለመሆኑን መንግስት ገለፀ፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ቱሪስቱን በመግደል ተጠርጥሮ የተያዘው ግለሰብ ፍቃድ ያለው መሣሪያ ይዞ እንደነበርና ከአንዱ ትከሻው ወደ አንዱ በሚያቀያይርበት ወቅት በድንገት ጥይት ባርቆበት አደጋው መከሰቱን ለፖሊስ ተናግሯል ብለዋል፡፡ በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ላይ የሚደረገው ተጨማሪ ምርመራ መቀጠሉንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው ባለፈው ረቡዕ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ላይ ባህርዳር ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ መሆኑን ፖሊስ ገልፆ፤ ተጠርጣሪውን ወዲያው በቁጥጥር ስር አውሎ የሟች አስከሬን ባህርዳር ሆስፒታል እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ሃሙስ እለት ወደ አዲስ አበባ እንዲላክ ተደርጓል ተብሏል፡፡ የሟች አስከሬን አዲስ አበባ በደረሰበት ወቅትም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድርና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሣደር ግሬግ ዶሪ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን አስከሬኑ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ወደ ትውልድ ሀገሩ እንደሚሸኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ አበባ በተደረገው አቀባበል ላይ፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር፤ ግድያው በልዩ አላማ ወይም በሽብር የተፈፀመ አለመሆኑን በመጥቀስ የእንግሊዛዊውን መገደል ተከትሎ የሀገሪቱ የጐብኚዎች ፍሰት አይቀንስም፤ ገጽታንም አያበላሽም ብለዋል፡፡

Read 2062 times