Monday, 29 December 2014 07:40

መንግሥት ሔሊኮፕተሯን ለማስመለስ የጀመረው ጥረት የለም ተባለ

Written by  ማህሌት ሰለሞን
Rate this item
(22 votes)

በዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ ተጠልፋ ወደ ኤርትራ የገባችውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሆነች ሩሲያ ሰራሽ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ለማስመለስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተጀመረ ምንም አይነት ጥረት እንደሌለ ተገለፀ፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ምላሽ፤ “የኤርትራ መንግስት ለአካባቢያዊ ህጎችም ሆነ ለዓለም አቀፍ ህጎች ተገዢ የሆነ መንግስት ስላልሆነና ከኤርትራ መንግስት በጎ ምላሽ ይገኛል ተብሎ ስለማይታሰብ፣ ሔሊኮፕተሯን ለማስመለስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምንም አይነት ጥረት እየተደረገ አይደለም” ብለዋል፡፡ መንግስት ወደፊት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥም አክለው ተናግረዋል፡፡ቀደም ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፣ ረዳት አብራሪውና የሔሊኮፕተሩ ቴክኒሻን በዋና አብራሪው ሻምበል ሳሙኤል አስገዳጅነት ኤርትራ መግባታቸውን የጠቆመ ሲሆን የሔሊኮፕተሯ አብራሪ ለምን ድርጊቱን እንደፈፀመ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡አሶሼትድ ፕሬስ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ፤ ብዙ ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች በአገራቸው ባለው አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ጠቁሞ “ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚደረግ ሽሽት ግን ያልተለመደና እንግዳ ጉዳይ ነው” ብሏል፡፡ ባለፈው አርብ ማለዳ 2፡35 ላይ ድሬደዋ ከሚገኘው የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ የዘወትር የልምምድ በረራ ለማድረግ የተነሳችው ተዋጊ ሔሊኮፕተር፤ በዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ እየተመራች ረዳት አብራሪ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝንና ቴክኒሻን ፀጋ ብርሀን ግደይን ይዛ ወደ ኤርትራ መኮብለሏ የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ በ1995 ዓ.ም ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ በተሰኘ የአየር ኃይል ባልደረባ ኤል 39 የተሰኘ የልምምድና ቀላል የውጊያ አውሮፕላንን ለልምምድ ከመቀሌ የማዘዣ ጣቢያ ይዞ በመነሳት ወደ ኤርትራ መኮብለሉ የሚታወስ ነው፡፡ እስካሁን የኤርትራ መንግስት በጉዳዩ ላይ አንዳችም አስተያየት እንዳልሰጠ ታውቋል

Read 6710 times