Monday, 29 December 2014 07:42

ተቃዋሚዎች የታዛቢዎችን የምርጫ ሂደት ተቃወሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ምርጫው ሳይነገረን ነው የተካሄደው ብለዋል
ታዛቢዎቹን ህብረተሰቡ ነው የመረጣቸው - ምርጫ ቦርድ
  በግንቦቱ ምርጫ የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ከህግና ደንብ ውጪ፣ የገዢው ፓርቲ አባላት የተመረጡበት ነው በማለት የተቃወሙ ሲሆን ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ የህዝብ ታዛቢዎችን ህብረተሰቡ ነው የመረጣቸው ብሏል፡፡በዘጠኝ ፓርቲዎች ጥምረት የተመሰረተው የፓርቲዎች ትብብር፤ የታዛቢዎች ምርጫ በተከናወነ ማግስት “የታዛቢዎች ምርጫ የገዥውን ፓርቲና የምርጫ ቦርድን አንድነት ይበልጡን ያረጋገጠ ነው” በሚል ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫው ዋና ዋና ፓርቲዎችን ባገለለ መልኩ የተከናወነ ነው ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ የህዝብ ታዛቢዎች አመራረጥን በሚደነግገው መመሪያ መሠረት፤ የምርጫ ጣቢያ ሃላፊው ለህዝብ ይፋ የስብሰባ ጥሪ ማድረግ እንዳለበት ተቀምጧል ያለው የትብብሩ መግለጫ፤ ታህሣሥ 12 በተካሄደው ምርጫ ግን የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የመረጧቸው የወጣትና የሴት ሊግ አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል ብሏል፡፡ መመሪያው ፓርቲዎች በምርጫው እንዲሳተፉ በደብዳቤ ጥሪ ይደረጋል ቢልም ከኢህአዴግ ተወካዮች ውጪ የትኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ በፅሁፍ አልተጋበዘም ብሏል - ትብብሩ፡፡
“ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሂደቱ ባገለለ መልኩ የምርጫ ታዛቢዎችን መርጦ መሠየሙ ለገዥው ፓርቲ መገልገያ ከመሆኑም ባሻገር ባጠቃላይ ምርጫው የኢህአዴግ የማምታቻ ፖለቲካ እንደሆነ ያረጋገጠ ነው” ይላል - መግለጫው፡፡
በ2002 ምርጫ ተመሳሳይ ነገር መፈፀሙን ያስታወሰው ትብብሩ፤ የህዝብ ታዛቢዎች ያለተወዳዳሪ የኢህአዴግ አመራር በሆኑ አስመራጮች መልካም ፈቃድ ብቻ ታዛቢ እንዲሆኑ ተደርጓል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ የአመራረጥ መመሪያው ለተሣታፊ ፓርቲዎች በቀጥታ ጥሪ ተደርጐላቸው እንዲታደሙ ይደረጋል እንደሚል ጠቅሰው፤ “በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረው ውጭ በምርጫው ላይ እንድንሣተፍ ጥሪ አልቀረበልንም፤ ከዚህ አንፃር አካሄዱ ሚስጥራዊና ስህተት ያለበት ነው” ብለዋል፡፡

Read 2474 times