Monday, 29 December 2014 07:42

ተቃዋሚዎች የታዛቢዎችን የምርጫ ሂደት ተቃወሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

ምርጫው ሳይነገረን ነው የተካሄደው ብለዋል
ታዛቢዎቹን ህብረተሰቡ ነው የመረጣቸው - ምርጫ ቦርድ

በግንቦቱ ምርጫ የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ከህግና ደንብ ውጪ፣ የገዢው ፓርቲ አባላት የተመረጡበት ነው በማለት የተቃወሙ ሲሆን ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ የህዝብ ታዛቢዎችን ህብረተሰቡ ነው የመረጣቸው ብሏል፡፡
በዘጠኝ ፓርቲዎች ጥምረት የተመሰረተው የፓርቲዎች ትብብር፤ የታዛቢዎች ምርጫ በተከናወነ ማግስት “የታዛቢዎች ምርጫ የገዥውን ፓርቲና የምርጫ ቦርድን አንድነት ይበልጡን ያረጋገጠ ነው” በሚል ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫው ዋና ዋና ፓርቲዎችን ባገለለ መልኩ የተከናወነ ነው ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡
የህዝብ ታዛቢዎች አመራረጥን በሚደነግገው መመሪያ መሠረት፤ የምርጫ ጣቢያ ሃላፊው ለህዝብ ይፋ የስብሰባ ጥሪ ማድረግ እንዳለበት ተቀምጧል ያለው የትብብሩ መግለጫ፤ ታህሣሥ 12 በተካሄደው ምርጫ ግን የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የመረጧቸው የወጣትና የሴት ሊግ አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል ብሏል፡፡ መመሪያው ፓርቲዎች በምርጫው እንዲሳተፉ በደብዳቤ ጥሪ ይደረጋል ቢልም ከኢህአዴግ ተወካዮች ውጪ የትኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ በፅሁፍ አልተጋበዘም ብሏል - ትብብሩ፡፡
“ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሂደቱ ባገለለ መልኩ የምርጫ ታዛቢዎችን መርጦ መሠየሙ ለገዥው ፓርቲ መገልገያ ከመሆኑም ባሻገር ባጠቃላይ ምርጫው የኢህአዴግ የማምታቻ ፖለቲካ እንደሆነ ያረጋገጠ ነው” ይላል - መግለጫው፡፡
በ2002 ምርጫ ተመሳሳይ ነገር መፈፀሙን ያስታወሰው ትብብሩ፤ የህዝብ ታዛቢዎች ያለተወዳዳሪ የኢህአዴግ አመራር በሆኑ አስመራጮች መልካም ፈቃድ ብቻ ታዛቢ እንዲሆኑ ተደርጓል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ የአመራረጥ መመሪያው ለተሣታፊ ፓርቲዎች በቀጥታ ጥሪ ተደርጐላቸው እንዲታደሙ ይደረጋል እንደሚል ጠቅሰው፤ “በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረው ውጭ በምርጫው ላይ እንድንሣተፍ ጥሪ አልቀረበልንም፤ ከዚህ አንፃር አካሄዱ ሚስጥራዊና ስህተት ያለበት ነው” ብለዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ህገወጥ ተግባር ነው የተከናወነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ለምርጫ ሂደቱ ወሣኝ የሆነው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በዚህ መልኩ መከናወኑ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን በቁጥጥሩ ስር ለማስገባት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ “ቦርዱ 250ሺ የህዝብ ታዛቢ አስመርጠናል ያለው የገዢውን ፓርቲ ሰዎች በማስመረጥ ነው” ሲሉም ተችተዋል - ፕ/ር በየነ፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት አቶ መሣፍንት ሽፈራው በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫ ቦርድ በሰሞኑ የታዛቢዎች ምርጫ ላይ ስህተት ሠርቷል ይላሉ፡፡ “ምርጫው እንደሚካሄድ በሚገባ አላስተዋወቁም፤ ለኛም አልነገሩንም” ብለዋል - አቶ መሣፍንት፡፡
ቦርዱ ለፓርቲዎች በደብዳቤ ጥሪ ማቅረብ እንደነበረበት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ጥሪው ባለመቅረቡ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫው አሳታፊ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ በትክክል የህዝብ ታዛቢዎች ናቸው የተመረጡት ብሎ ለመቀበል የፓርቲዎች ውክልና ያስፈልግ ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የፓርቲዎቹ ተወካዮች በሌሉበት ታዛቢዎቹ መመረጣቸው ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡
ከ400 በላይ አባላቱን የታዛቢዎች ምርጫ በተደረጉባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች ማሰማራቱን የጠቆሙት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፤ ምርጫ ሳይከናወን በ2002 ታዛቢ የነበሩ ግለሰቦች በዘንድሮ ምርጫም እንዲቀጥሉ መደረጉን ይናገራሉ፡፡
የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ገና ከጅምሩ እንከን ነበረበት የሚሉት አቶ ማሙሸት፤ ህብረተሰቡ ታዛቢዎቹን እንዲመርጥ በቂ ቅስቀሳ አለመደረጉንና በዚህም የተነሳ በየጣቢያው ከ20 እና 30 የማይበልጡ ሰዎች መገኘታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ባለፈው ምርጫ ታዛቢ የነበሩ ግለሰቦች ድምፀ ውሳኔ ሳይሰጥባቸው በታዛቢነት እንዲቀጥሉ ተደርጓል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከፓርቲው የተወከሉ ግለሰቦች ያሰባሰቡት መረጃ ለህዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ ቅሬታችንን ለምርጫ ቦርድ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ተገኝተው መታዘባቸውን የተናገሩት፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ በአብዛኛው በስብሰባ ቦታው የነበሩት እናቶች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ መድረክ ላይ የነበሩት ግለሰቦች የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንደሚካሄድ አስተዋውቀው የእለቱ ፕሮግራም መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ ከተሰባሳቢው መሃል ግለሰቦች እየተጠቆሙ ይመረጣሉ የሚል ግምት የነበረኝ ቢሆንም የተደረገው ግን ከገመትኩት ውጭ ነው ይላሉ፡፡ “መድረክ ላይ የነበረው ሰብሳቢ በቀጠናው ላሉ ጣቢዎች 60 ሰዎች እንደሚስፈልግ አስተዋውቆ ስም ዝርዝራቸውን መጥራት ጀመረ፤ ከተጠሩት 60 ግለሰቦች ውስጥ በእለቱ የተገኙት 22 ያህል ብቻ ነበሩ” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የቀሩት ሰዎች ምን ይሁኑ ሲባል አንዳንዶች እየተነሱ “በቃ እኛ እናውቃቸዋለን፤ ባይመጡም ተቀበሏቸው” ይሉ እንደነበር መታዘዛቸውን ገልፀዋል፡፡ በኋላ ላይ ተቃውሞ በመቅረቡ “ከቤቱ ይመረጡ” ተብሎ 5 ደቂቃ  ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰዎች ወደ መድረኩ እየሄዱ በሹክሹክታ ከጠቆሙ በኋላ “በቃ 60 ሰው ሞልቷል፤ መልካም የምርጫ ጊዜ ይሁንልን” ተብሎ ስብሰባው ተበተነ ሲሉ አቶ ዳንኤል የታዘቡትን ተናግረዋል፡
“ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች የተደረገው የኢህአዴግ አባላትን በታዛቢነት የማስመረጥ ልምድ በዚህኛው ምርጫ ላይም ተደግሟል” ያሉት ደግሞ የኢዴፓ አመራር አባል አቶ አዳነ ታደሰ ናቸው፡፡
ኢዴፓ የወከላቸው የምርጫ ታዛቢዎች፤ የኢህአዴግ አባላት የሆኑ ግለሰቦች በታዛቢነት መመረጣቸውን እንደተመለከተ ለፓርቲው ሪፖርት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ አዳነ፤ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ሰዎች እንዲመረጡ መደረጋቸው የምርጫውን ተአማኒነት የሚያሳጣና በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
እንዲህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር እጩዎች አስቀድሞ ታውቀውና ተገምግመው ለህዝብ ምርጫ ይቅረቡ የሚል ሃሳብ ለምርጫ ቦርድ አቅርበን ነበር ያሉት የፓርቲው አመራር አባል ግን ቦርዱ ሃሳባችንን ውድቅ አድርጎታል ብለዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በበኩላቸው፤ የህዝብ ታዛቢዎቹን ህብረተሰቡ ራሱ ነው የመረጠው ብለዋል፡፡ ቦርዱ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ስለታዛቢዎች ምርጫ ማስታወቂያ በማስነገሩም በመላ ሃገሪቱ ያሉ ዜጎች ተወካያቸውን በነቂስ ወጥተው እንደመረጡ ም/ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ቀደም ብሎ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለሚመለከታቸው ሁሉ ማሰራጨቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የታዛቢዎች ምርጫን በተመለከተ በሚዲያ በቂ ማስታወቂያ በመነገሩ፣ ፓርቲዎች በደብዳቤ ጥሪ አልደረሰንም ሲሉ የሚያቀርቡት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለዋል - መድረክ ለቦርዱ በደብዳቤ ቅሬታውን ማቅረቡን በመጠቆም፡፡
በአመራርጥ ሂደቱ ተቃዋሚዎች የጠቀሱትን ችግር በተመለከተም፣ የምርጫ ጣቢያ በትክክል ተጠቅሶ ለሚመጣ አቤቱታ ቦርዱ አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ወንድሙ አስታውቀዋል፡፡

Read 4779 times