Monday, 29 December 2014 07:49

ጣቢያውን የማይመጥን ፕሮግራም!

Written by  አንዱአለም ናስር andualemnassir@gmail.com
Rate this item
(14 votes)

     የቴሌቪዥን ስርጭቶች የሚተላለፉበት አንዱ መንገድ በጠፈር ላይ የሚገኙ ሳተላይቶችን በመጠቀም ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለኢትዮጵውያን እንደ አማራጭ ሆኖ የቀረበ የቴሌቪዢን ጣቢያ ነው - ኢቢኤስ፡፡ ጣቢያው ከተመሰረተ ጀምሮ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ከአማራጭም በላይ ለመሆን ችሏል፡፡ ለዚህም ምስክሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘቱ ነው፡፡
በቅርቡ በጀመረውና ምንም ኢትዮጵያዊ መልክ በሌለው ከውጭ በተቀዳ ፕሮግራሙ ምክንያት ግን ለትችት ተጋልጧል፡፡ በግል ምልከታዬ፣ ይህ ፕሮግራም ኢቢኤስን የሚመጥን አይደለም፡፡ እስቲ ፕሮግራሙ ለኔ የሰጠኝን ስሜት ላጋራችሁ፡፡ ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2006 ዓ.ም 12፡00 የተጀመረውና 35 ደቂቃ የወሰደው ሙሉ ፕሮግራም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ፕሮግራሙ ሲጀምር አንድ የ17 ዓመት ልጃገረድ (ተረኛ ባለ ልደት ነች) በሚያምር ሰፊ አልጋ ላይ ተኝታ ያሳያል፡፡ ይህች ተረኛ ባለ ልደት ከተኛችበት ምቹ አልጋ እየተንጠራራች ተነስታ፣ በረጅም መስታወት ፊት በመቆም ጸጉራን በጣቶቿ በተን በተን ታደርግና፣ ቻፒስቲኳን ከመደርደርያው አንስታ ከንፈሯን ትቀባለች፡፡ ከዚያም ጓደኞቿ እቤቷ ድረስ በመኪናቸው መጥተው ይወስዷታል፡፡ (የዚህች ባለ ልደት ኑሮ እንኳን ለመኖር ለማሰብም ይከብዳል‘ኮ! በቁጥርም ቢሰላ እንደሷ ባማረ አልጋ ላይ በምቾት የሚተኙ ኢትዮጵውያን ከመቶ አምስት መሙላታቸውን እንጃ፡፡ የቤታችን መስታወት‘ኮ ግማሽ ፊታችንን ብቻ የሚያሳይ ነው፤ አለባበሳችንን እንኳ እድሜ ለከተማችን ባለመስታወት ፎቆች! ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያልን አስተካክለን እንውላለን፡፡ እኛ 95 በመቶ ኢትዮጵያውያኖች እንግዲህ እንዲህ ነው ኑሮአችን!)
ከዚያም በሚያምረው የመኖሪያ አካባቢያቸው ለመዝናኛ ተብሎ በተከለለው ስፍራ ውስጥ ለምለም ሳር ላይ ከጓደኞቿ ጋር ሩጫ  ሲወዳደሩ፣ በጀርባቸው ሲንደባለሉና የቅርጫት ኳስ ሲጫወቱ ይቆዩና፣ ተመልሰው በመጡበት መኪና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ (እኛ 95 በመቶ ኢትዮጵያውያኖችስ? …ሆ! እኛ‘ኮ እንኳን ተከልሎልን ለምለም ሳር ላይ ልንጫወት በራሳችን ተነሳሽነት ሜዳ ብለን በሃሳብ መስመር የከለልነው አቧራማና ድንጋያማ ሜዳ ለልማት ተብሎ የታጠረብን ምስኪኖች ነን!)
ወደ ቤታቸው ከገቡም በኋላ ተጣጥበው፣ ለልደቷ ቁሳቁሶች ለመግዛት ተሰባስበው በመኪናቸው ይወጣሉ፡፡ ከዚያም በመሃል ከተማ ከሚገኙት ስመ ገናና ውድ ሱቆች ውስጥ ይገቡና እንኳን ከኪስ አውጥቶ ለመክፈል፣ ለማሰብ እንኳ በሚከብድ ዋጋ የሚፈልጉትን ገዝተው ይመለሳሉ፡፡ (እኛስ?... እኛ‘ኮ አዲስ ልብስ የምንለብሰው አዲስ አመትን ጠብቀን ነው - እሱም ከሞላልን ነው፡፡ ታዲያ የ5 በመቶ ኢትዮ-አሜሪካኖችን ኑሮ እያየን መሳቀቅ አለብን እንዴ ጎበዝ!)
በመቀጠል ያቺ የታደለች ባለልደት ከጓደኛዋ ጋር ሆና ወደ ውበት ሳሎን በማምራት፣ ይህ ቀረሽ በማይባል ደረጃ ትዋብና መጥቶ የሚወስዳትን መኪና ትጠባበቃለች፡፡ መኪናው ሲያዩት ያምራል፤ ዋጋው ግን ያስፈራል! በሚሊዮን ብር የሚገመት ነው በተባለለት በዚህ መኪና፤ በግራና በቀኝ በጥቋቁር ሞተር ሳይክሎች በመታጀብ፣ ወደተዘጋጀላት የልደት አዳራሽ ትከንፋለች፡፡ ባለሚሊዮን ብሩ መኪና መንገዱን ዚግዛግ እየመታ፣ የጎን መብራቶቹን ብልጭ ድርግም እያደረገ፣ በጥሩምባው ከተማውን እየበጠበጠ ከአዳራሹ ደረሰ፡፡ ለልደቷ የተጋበዙ ጓደኞቿ በራፍ ላይ ተኮልኩለው ጠበቋት፡፡ አላሳፈሯትም፡፡ ገና ያለችበትን መኪና ሲመለከቱ አካባቢውን በጩኸት ደባለቁት፡፡ አጠገባቸው እንደደረሰች የመኪናው በር ተከፍቶላት በቄንጥ ወረደችና ወደ አዳራሹ ዘለቀች፡፡
(እኛስ?... እኛማ እንኳን በሚሊዮን ብር መኪና  ታክሲም በግድ ነው፤ በሰልፍ እየተንገላታን፡፡ ባቡራችን ቢደርስልን እንኳ በገንዘብ መወዳደር ባንችል እንኳን በፍጥነት እንቀራረብ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ መቼም አማራጭ የለም፤ ያው እንደፈረደብን በአንበሳችን እንታጨቃለን እንጂ!)
አዳራሹ በእንግዶቿ ተሞልቷል፤ ወደ አዳራሹ እንደተገባ በስተቀኝ በኩል መጠነኛ መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡
 አጋፋሪም ተመድቦለታል፤ በፈረንጅ ቡዳ የተበላ ይመስል አንድም የአማርኛ ቃል ሳይተነፍስ ነው ፕሮግራሙን የመራው፡፡ ለነገሩ ማን ያውቃል? “አማርኛ ከተናገርክ ወዮልህ!” ተብሎም ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ አንድም የኢትዮጵያ ሙዚቃና ውዝዋዜ ሳይታይ ነው ዝግጅቱ የተጠናቀቀው፡፡
ከዚህ በኋላ “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኬክ” ቀርቦ ባለ ልደቷ ቆረሰች፤ ርችቶች ተለኮሱ፤ ጩኸት በረከተ፤ ኬክ ተወራወሩ፤ ፊታቸውን ተለቀለቁት፡፡ በመጨረሻም ባለ ልደቷ ወደ መድረኩ በመውጣት ጋብዛቸው ሳያሳፍሯት ለመጡ ጓደኞቿ ምስጋና አቅርባ፣ ቀሪው ጊዜ ያማረ እንዲሆን ተመኝታ ወረደች፡፡ የልደት በዓሉ እዚህ ጋ ይጠናቀቅና ከአንድ ጓደኛዋ ጋር በመሆን አረጋውያንን ስትጎበኝ ተመለከትን፡፡ (በኔ ዕይታ ከፕሮግራሙ ውስጥ ብቸኛ መልካም ተግባር ይሄ ነው፡፡)
እንግዲህ ይህ ነው “One‘s in a Life” ማለት፡፡ አንድም ኢትዮጵያዊ መልክ የሌለው (እኛን የማይመስል) ፕሮግራም እንዴት ለኢትዮጵያውያን አማራጭ ተብሎ በተመሰረተ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲቀርብ ይደረጋል? በእኔ አስተያየት ፕሮግራሙ መልካምነቱ ለተመሰከረለት ጣቢያ የማይመጥን፣ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ፣ ባህልና ወግም ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡
ከእኛ ይልቅ ለውጭዎቹ ይበልጥ የሚቀርብም ነው፡፡ (ምናልባት ለዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን?) እንደሚመስለኝ ባህል ወግ ልማዴን ትቼ ካልጠፋሁ እያለ ያስቸገረውን ወጣት፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለስ ባይቻል እንኳ፣ ባለበት ተረጋግቶ እንዲቆም ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ መልካም  ሳምንት!

Read 5662 times