Monday, 29 December 2014 08:25

ጆርጅ ቡሽ ገናን በሆስፒታል አሳለፉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የትንፋሽ ማጠር ገጥሟቸው ባለፈው ማክሰኞ ሂዩስተን ሜቶዲስት ሆስፒታል የገቡት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት  ጆርጅ  ኤች ደብሊው ቡሽ፤ ከትላንት በስቲያ የተከበረውን የፈረንጆች የገና በዓል በሆስፒታል አሳለፉ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ጂም ማክግራዝ፤ ቡሽ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና የገና በዓልን በሆስፒታል ያሳለፉት በሽታው ከፍቶባቸው ሳይሆን ለጥንቃቄ ሲባል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ብሮንካይትና በሃይለኛ ሳል ይዟቸው ሆስፒታል ከገቡ በኋላ የገና በዓልን ጨምሮ ለሁለት ወራት እዚያው መቆየታቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ የአሁኑ ግን ከቀድሞው በጣም ይለያል ብለዋል - የፕሬዚዳንቱን ጤናማነት ሲገልፁ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ሆስፒታል መግባት ላሳሰባቸው በርካታ ወዳጆችና አድናቂዎቻቸው የቡሽ ዋና ኃላፊ በሰጡት መግለጫ፤ “የቡሽ ቤተሰብ፤ ለጭንቀታችሁ፣ ለፍቅራችሁና፣ ለፀሎታችሁ በእጅጉ ያመሰግናል፡፡ ይሄ የዛሬ ሁለት ዓመት እንደሆነው ዓይነት አይደለም፡፡ የትንፋሽ ማጠር ነው፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ” ብለዋል፡፡ ቡሽ ሆስፒታል መግባታቸውን የሰሙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸውም ለቀድሞው ፕሬዚዳንትና ለመላው የቡሽ ቤተሰብ የመልካም ጤንነት ምኞታቸውን ልከዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ የ90 ዓመቱ ቡሽ፤ 41ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን የ43ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽም አባት ናቸው፡፡ የዊልቸር እስረኛ ባደረጋቸው ከፍተኛ የነርቭ ህመም ሲሰቃዩ የቆዩት ቡሽ፤ በቅርቡ ግን ነቃ ነቃ ማለት ጀምረው ነበር ተብሏል፡፡ ባለፈው ሰኔ ለ90ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ከሄሊኮፕተር ላይ በፓራሹት የዘለሉ ሲሆን የዛሬ ወር “41፡ A Portrait of My Father” የተሰኘ አዲስ መፅሃፋቸው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከልጃቸው ጋር ተገኝተው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡበትን 25ኛ ዓመት በዓል በቅርቡ ያከበሩት ጆርጅ ቡሽ፤ በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በባህር ኃይል አብራሪነት የተሳተፉ ሲሆን ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት በቴክሳስ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደሰሩ የህይወት ታሪካቸው ያወሳል፡፡

Read 2848 times