Saturday, 03 January 2015 10:36

የመንግሥት የግዢ ሥርዓት ለግሉ ዘርፍ አመቺ አይደለም ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

      መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች መጠናከርና አቅም መፈጠር ድጋፍ አደርጋለሁ ቢልም በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የመንግሥት የግዢ ሥርዓት አመቺ አልሆነልንም አሉ፡፡በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በዚህ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባደረጉት ውይይት የመንግሥት ግዢ አሰራር ሂደት ለአሰራራቸው አመቺ እንዳልሆነና ዕድገታቸውን እያቀጨጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ፅ/ቤት በብረታ ብረትና በጨርቃጨርቅ፣ በአይቲና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያደረገውን ጥናት አቅርቦ ተወያይተውባቸዋል፡፡በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የዘርፉን እድገትና ልዩ ባህርይ ያገናዘበ የግዢ ሥርዓት እንደሌለና ያለውም በትክክል እንደማይፈፀም የጠቆመው ጥናቱ፤ የአገር ውስጥ ተጫራቾች በአግባቡ ቅድሚያ እንደማያገኙና በተለያየ መንገድ መገለል እንደሚፈፀምባቸውም፣ ለኬብል ግዢ 400 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ሽያጭ እንደሚጠየቁ ጠቅሰዋል፡፡ከምርቶች ስታንዳርድ ስፔስፊኬሽን ዋጋ በተጨማሪ ለተጫራቾች ግልፅ ያልሆነ ሌላ ሀሳባዊ መስፈርት ይጠቀማሉ፤ ለፋይናንስና ለቴክኒክ መስፈርቶች የተያዘውን ነጥብ ተወዳዳሪው አስቀድሞ ስለማያውቅና ወጥ አሰራር ስለሌለ የፈለገውን ለማሳለፍ እንዲችል ያደርገዋል ብሏል ጥናቱ፡፡ጥናቱ በመፍትሄነት ካቀረባቸው ነጥቦች መካከልም፡- ለአገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ አፈፃፀም ወጥ መመሪያ ማዘጋጀት፣ የሚፈለገው ምርት አገር ውስጥ አለመኖሩ ሳይረጋገጥ የውጭ አገር ግዢ ያለመፈፀም፣ ከግዢ በፊት አስፈላጊ ስታንዳርድ በማውጣት ያንን ስፔሲፊኬሽን ከሚያሟሉት መካከል አሸናፊውን በዋጋ መምረጥ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ውጤትን መደመር ማቆም ለቴክኒክና ለፋይናንስ የተያዘውን ነጥብ ለተወዳዳሪዎች ማሳወቅ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በመንግሥት ግዢ ሂደት የዘርፉን ልዩ ባህርይ ያገናዘበ ስርዓት እንደሌለና ያለውም ሕግ በትክክል እንደማይፈፀም ጥናቱ አመልክቷል፡፡ አምራቹ ያለበት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ሳይገናዘብ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ምርት እንዲያቀርብ ጫና ይፈጠርበታል ያለው ጥናቱ፤ በእነዚህ ምክንያቶች ለሚደርስ የምርት አቅርቦት መዘግየት የሚወሰደው የውሉን 20 በመቶና የውል ማስፈፀሚያ ተቀማጭን የመውረስ ቅጣት ተመጣጣኝ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ የውል ማስፈፀሚያ ጊዜው ከአቅም በላይ በመሆኑ

ምክንያት በውሉ መሰረት ካላቀረበ አምራቹ በቀጣይ በማንኛውም ጨረታ እንዳይሳተፍ ማገድ ሚዛናዊ አይደለም ብሏል፡፡ጥናቱ መስተካከል አለባቸው ያላቸውን የአሰራር ችግሮችንም ዘርዝሯል፡፡ ለሚፈለገው ማንኛውም ምርት ስታንዳርድ (ደረጃ) የማውጣት ችግር፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ አምራቾች ብቻ ክፍት የሆኑ ጨረታዎች ያለመኖራቸው፣ በጨረታ ወቅት በውል መፈፀሚያ ጊዜ መካከል ለሚከሰት የዋጋ ያለመረጋጋት ማስተካከያ ከ18 ወራት በታች እድሜ ላላቸው ፕሮጀክቶች ከ12 ወር በኋላ ካልሆነ በስተቀር ምንም ማካካሻ አለመፈፀም፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርት ለመባል 35 በመቶ እሴት በአገር ውስጥ መጨመር ከባድ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት ጥናቱ አሳስቧል፡፡ለኮንትራት ማስፈፀሚያ የሚያዘው ከገንዘብ በተጨማሪ በኢንሹራንስ ቦንድ ቢተካ እንዲሁም የውል ቅድሚያ ክፍያ መያዣ በኢንሹራንስ ቦንድ ቢፈፀም፣ በገበያ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሚደርሰውን ኪሳራ ለመካስ የተቀመጡት የ18 እና የ12 ወራት ቅድመ ሁኔታዎችን በመተው ተጨባጭ በሆነ የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ ማድረግ፣ አቅራቢው በውሉ መሰረት ማቅረብ ባይችል የሚጣልበት ቅጣት ያልተፈፀመውን የውል ግዴታ ክብደት ከግምት ያስገባና ተመጣጣኝ ማድረግ፣ በዚህ ረገድ የሚፈጠሩ ያለመግባባቶች ፍ/ቤት ከመሄድ በግልግል ዳኝነት መፍታት፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ብቻ ክፍት የሆኑ ግዢዎች እንዲኖሩ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ ምርት ለመባል 35 በመቶ እሴት የመጨመር ግዴታን ማሳነስ የሚሉትን ጥናቱ በመፍትሄነት አቅርቧል፡፡በኮንትራክሽን ዘርፍ በገበያ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሚደርሰውን ኪሳራ ለመካስ የተቀመጡትን የ12 እና የ18 ወራት ቅድመ ሁኔታዎች በመተው ተጨባጭ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ ማድረግ፣ የዋጋ ማስተካከያ ሲደረግም ለዕቃ ብቻ ሳይሆን የሠራተኛ ደሞዝና የማሽነሪ ዋጋ ኪራይም (ከጨመረ) በዋጋ ማስተካከያው እንዲሸፈን ማድረግና ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ የሚሉትንም በመፍትሄነት ይጠቅሳል ጥናቱ፡፡በአገር ውስጥ አይቲ ዘርፍ፣ አገልግሎት አቅራቢዎች መገለልና፣ በአገልግሎታቸው አለመተማመን እንዲሁም ለዘርፉ ቅድሚያ እንዳልተሰጠ መቁጠርና ከመንግሥት እንደችግር የጠቆመው ጥናቱ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮግራም ምርት መሳተፋቸው በዘርፉ  ኢ-ፍትሃዊ ውድድር መፍጠሩን ይገልፃል፡፡በመንግስት ፖሊሲ ዘርፉ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ውስጥ እንዲታቀፍ የተደረገ በመሆኑ በግዢ ሂደትም በዚሁ መንገድ እንዲስተናገድ ማድረግ፣ በአይቲ ዘርፍ ለትንንሽ ግዢዎች በአገር ውስጥ አቅራቢዎች እስካሉ ድረስ የውጭ አቅራቢዎች ግዢን ማቆም፣ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማርና ምርምር ሥራቸው አልፈው በገበያው ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በግዢ ሕጉና በገበያ መርህ መሰረት እንዲሆን ሲልም የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቧል፡፡በቀረቡት ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበና የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ሃሳብ ሰጥተው ጉባኤተኞችም ጥያቄና ሃሳብ አቅርበው በመወያየት ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡
 

Read 2075 times