Saturday, 03 January 2015 10:43

ግልገል ጊቤ 3 በሰኔ ሃይል ማመንጨት ይጀምራል ተባለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

         በ1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የግልገል ጊቤ 3 የውሃ ሃይል ማመንጫ
ግድብ ግንባታ 88 በመቶ መጠናቀቁንና በመጪው ሰኔ ወር በከፊል ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ሮይተርስ ዘገበ፡፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ ከትናንት በስቲያ ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ግድቡ ከሚኖሩት አስር ሃይል ማመንጫ ክፍሎች ሁለቱ በመጪው ሰኔ ወር ሃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ሲሆን፣ በቀጣይም በየወሩ አንዳንድ ማመንጫዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ከአንድ አመት በኋላ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የግድብ ፕሮጀክቱ 1ሺህ 870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የገለጹት ወ/ሮ አዜብ፣ ግንባታው ተጠናቅቆ በሙሉ ሃይሉ ማመንጨት ሲጀምር አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በማምረት ላይ የምትገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል በእጥፍ ያህል ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ግንባታው እ.ኤ.አ በ2008 የተጀመረው የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት፣ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ግድቡ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል በሚል ያካሄዱትን አለማቀፍ የተቃውሞ ዘመቻ ተከትሎ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአውሮፓ የኢንቨስትመንት ባንክ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ብድር በመከልከላቸው ግንባታው እንደተጓተተ ይታወቃል፡፡

Read 6034 times