Monday, 05 January 2015 08:15

ለነፍሰ ጡር… ‘አልወለድም’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንኳን ለነቢዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁማ!
እንኳን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁማ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሷዬዋ ሀያኛ ነው የምትለው የልደት በዓሏን እያከበረች ነበር፡፡ እናላችሁ…በሆዱ “ድንቄም!” የሚል ጓደኛ ዘመድ ተሰባስቧል፡፡ ታዲያላችሁ…እሷዬዋ ምን ትላለች መሰላችሁ…
“እዚህ ክፍል በጣም ይበርዳል፡፡ ሙቀት ያስፈልጋል፡፡”
ይሄኔ  ከተጋባዦች አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“የእውነተኛ ዕድሜሽን ያህል ቁጥር ሻማዎች ቢበሩ ሙቀቱ አይደለም ለዚህ ክፍል ለጎረቤትም ይተርፋል…” እየጋበዙም ‘መሰደብ’ አለ እንዴ!
ስሙኝማ… የስጦታ መሰጣጫ ሰሞን አይደል…ዘንድሮ ለሰው ስጦታ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡
እናላችሁ…ለምሳሌ ለነፍሰ ጡር ሴት ስጦታ ‘በእርግዝና ወቅት ሊደረጉ የሚገባቸው ነገሮች…’  ምናምን የሚል ስጦታ መስጠት ይቻላል፤ ግን የእኔ ቢጤው ነገሮችን አዙሮ ማየት የማይችል… አለ አይደል…የአቤ ጎበኛን ‘አልወለድም’ ቢሰጥ ይታያችሁ! አሀ…ዛሬ መጣ፣ ነገ መጣ እየተባለ ገንፎው ምድጃ ላይ ሆኖ… የምን ሟርት ነው!
ልክ ነዋ…ሁሉም ነገር ‘አማራጭ’ ትርጉም ነገር አለዋ! ለምሳሌ የዘፈን ሲዲ መስጠት…አለ አይደል…አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሀ…“የአገሬን ዘፈን ሲዲ ትታ የሌላ የሰጠችኝ በአሽሙር ዲቃላ ነሽ ማለቷ ነው እንዴ!”…የሚል ነገር ሊኖር ይችላላ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የአገሬ ልጅ ነው የሚለው ‘መለኪያ’ እየጠበበ፣ እየጠበበ ወደ መንደር መውረዱ እንዳልተመቸን “ብለው ነበር… በሚል ይያዝልን፡፡
እናላችሁ…ሌላ ደግሞ ወይ አልበሙን ስለወደደው፣ ወይ ፖስተሩ ስለሳበው አንድ አዲስ የዘፈን ሲዲ የአበባ፣ የልብ ምናምን አይነት ስዕሎች ካሉበት ካርድ ጋር ለእንትናዬው ይሰጣታል፡፡ አንደኛው ዘፈን ውስጥ…“ሴት በሴት ይተካል እናቴ አይደለሽም…” ምናምን የሚል ነገር ሊኖርበት ይችላል፡፡ አያችሁ አይደል! በኋላ “ዜማው ደስ ስላለኝ ነው…” “የዘፋኙ ድምጽ ልዩ ከለር ስላለው ነው…” ምናምን ብሎ ማስተባበያ አይሠራም፡፡ እሷዬዋ… “ካላጣው አልበም ‘ሴት በሴት ይተካል’ የሚል ግጥም ያለበት ሲዲ የመረጠው ሊነግረኝ የፈለገው ነገር ነው ቢኖር ነው…” ልትል ትችላለቻ!
ለነፍሰ ጡር… ‘አልወለድም’ን የመስጠት አይነት ነገር ነው፡፡
ሀሳብ አለን…ቦሶቻችን ለበዓላቱ ስጦታ የማይሰጡንሳ! ለምሳሌ… “ጥር ወር ሙሉ ሻሽ የመሰለ ኩንታል ነጭ ጤፍ አርባ ዘጠኝ ብር ከዘጠና ዘጠኝ ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል…” ቢሉን…አለ አይደል…አንዳንድ ነገር ላይ ‘ለመወሰን’ ያግዘን ነበር፡፡ ቂ…ቂ...ቂ…
ሰውየው ለሚስቱ አሪፍ የሆነ የአልማዝ ቀለበት የገና ስጦታ ገዝቶ ይሰጣታል፡፡ እሷም በጣም ተደስታ በመንደሩ ትነሰነስበት ገባች፡፡ ታዲያላችሁ…አቶ ባል ይህን ውድ ስጦታ ለሚስቱ መስጠቱን የሰማው ጓደኛው ምን አለ መሰላችሁ…“ ያወጣኸው ገንዘብ እኮ ብዙ ነው…ያን ያህል ካወጣህ ለምን መኪና አትገዛላትም ነበር?” ይለዋል፡፡  
ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…“በእርግጥ መኪና ብገዛላት ጥሩ ነበር…ግን ፎርጅድ መኪና ከየት ነው የማገኘው!” አሪፍ አይደል! አጅሪት በ‘ዳይመንድ’ ሸልያለሁ ብላ…ጉዷን አላወቀች!
‘ውድ ስጦታ’ የተሰጣችሁ እንትናዬዎች…‘ፎርጅድ’ ሊሆን ስለሚችል አጣሩማ!
ኦርጂናል እያለ ‘ፎርጅድ’ ስጦታ መስጠት…አለ አይደል…ለነፍሰ ጡር ‘አልወለድም’ን የመስጠት አይነት ነገር ይሆናል፡፡
ለምሳሌ እንትና ለእንትናዬው ሊጠብ በሚችልበት ቦታ ሁሉ የጠበበ ‘ሞደርን’ ሱሪ ይሰጣታል፡፡ እሷ ደግሞ አንዳንዴ… “ኩዊን ላቲፋ ዘመድሽ ነች እንዴ!” እየተባለ ‘ሙድ የሚያዝባት’ አይነት ነች፡፡ እሷ ደግሞ “ምን ሥጋ አለኝና ነው!” የምትል ነች፡፡ “ይህንን ጠበብ ያለ ሱሪ የምሰጥሽ ወደፊት ክብደት መቀነስሽ ስለማይቀር ነው…” ቢላት…እንትነኛው የዓለም ጦርነት በሉት፡፡
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው! አሁን ወፍራም ነሽ ለማለት ነው! ይሄኔ ለሌላዋ ውሽማህ ገዝተኸው አልፈልግም ብላህ ይሆናል፣” ብላ ‘ልትለቀቅበት’ ትችላለች፡፡ (እነ እንትና ሱሪ ላይ ወሽመጥ የሚገባበት ዘመን ቀረ አይደል! የሚተራርፋችሁን ጨርቅ ሰብሱማ! አሀ ተጣጥፎ…አሪፍ ‘የአርት ሥራ’ ሊፈጠር ይችላላ!
ስማኝማ…ወዳጄ፣ ያኔ ጣልያን ሠላሳ ምናምነኛውን መንግሥት ያገኘች ጊዜ የሰጠኸኝ ስጦታ እኮ እንዴት ትዝ እንደምትለኝ! አሁን ማን ወዳጅ ነው…አለ አይደል…ያን ያህል ተጨንቆ የመሶብ ክዳን በስጦታ የሚሰጠው! ለቀጣዩ ዓመት ሰፌድ ነገር ትሰጠኛለህ ብዬ ብጠብቅ ኩም አደረግኸኝሳ! ብቻ አንተ ምን ታደርግ…ዘንድሮ እኮ እንኳን እነ ውስኪ ምናምን በስጦታ ሊመጡልኝ (በመለኪያ ቢሆንም!) የማውቃቸው የውስኪ ስጦታ የሚደርሳቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡
እናማ…ዘንድሮ ልትሰጠኝ ያሰብከው ነገር ካለ ሀሳብ ላቅርብ…ወንፊት ላክልኝ፡፡ አሀ… እህሉንና ‘ጠጠሩን’ መለየት ሲያቅተኝስ! ወንፊት ካልቻልክ አደንዛዥ ዕጽ እያነፈነፈ የሚያሳብቅ ውሻ ላክልኝ፡፡ ዘንድሮ ‘አደንዛዥ ዕጽ’ ማለት የሚጠበስ፣ የሚደቆስ ብቻ ሳይሆን ‘በሁለት እግሩ የሚሄድ’ ሊሆን ይችላል! ታዲያ ብቻውን ሳይሆን ማሰሪያ ገመዱንም አብረህ ላክልኝ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን…እሺ የመሶብ ክዳኑን እንኳንም ሰጠኸኝ…እስከ ዛሬ ያልተፈታልኝ ነገር ቢኖር ‘መሶቤ ክፍቱን እንደሚያድር’ ሹክ ያለብኝ ማን እንደሆነ ነው፡፡
እናማ…የሰጠኸኝ ዘንድሮ ቢሆን ኖሮ የመሶቡን ‘ስታተስ’ ሳያውቁ የመሶብ ክዳን መስጠት… አለ አይደል…ለነፍሰ ጡር… ‘አልወለድም’ን እንደ መስጠት ይሆን ነበር፡፡
የምር ግን… አለ አይደል… እስቲ ለራሰ በራ ሰው ሚዶ ሲሰጠው አስቡት! ለነፍሰ ጡር…   ‘አልወለድም’ ማለት ይሄ አይደል! ባይሆን ጄል ነገር ቢሰጥ…አሀ ቅቤ የጠጣ ቅል ይመስለላ! ስሙኝማ…ራስ በራን ጄል መቀባት ማለት እኮ ያው የእንጨት በርን ቫርኒሽ እንደመቀባት አይመስላችሁም!
“ምነው አረፈድክ?”
“ራሴን ቫርኒሽ ስቀባ…”
ቂ…ቂ...ቂ… የውሸቴን ነው የምስቀው፡፡ ‘ቂም ቋጥረው’.. አለ አይደል… “የበላሃትን ተጋሚኖ ሂሳብ ራስህ ቁጭ አድርጋት…” የሚሉ ወዳጆቼን እየቆጠርኩ ነው፡፡
ሀሳብ አለን…እንግዲህ ‘ቦተሊካው’ ሞቅ፣ ሞቅ እያለ አይደል! ለ‘ቦተሊከኞች’ በሙሉ ‘ኮሚኒስት ማኒፌስቶ’ በስጦታ ይታደልልንማ! አሀ… ጥቅስ እንዳያልቅባቸው ብለን ነዋ! አልፎ፣ አልፎ…አለ አይደል… ‘ቅዳሴው ቢያልቅበት ቀረርቶ ጨመረበት’ ነገሮች እንሰማለና! ወይም አሥርቱን ትዕዛዛት ከእነ ትርጉማቸው የሚያስረዳ መጽሐፍ ይሰጥልን፡፡ አሀ…እኛ መዝናናት እንፈልጋለና! እና የሆነ “ለማያቁሽ ታጠኝ…” የምንለው አይነት ‘ቦተሊከኛ’… አለ አይደል… “ታላቁ መጽሐፍ አታመንዝር ይላል…” ሲል…ቤታችን ሆነን በሳቅ እንንፈራፈራለና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኔ የምለው…ለሚስቶቻቸው የጂም ቦርሳ ስጦታ የሚሰጡ ባሎች የእውነትም ብጹአን ናቸው፡፡ ወይ ሚስቶቻቸውን ያምኗቸዋል፣ ወይም ይፈሯቸዋል፡ ልክ ነዋ…ከሦስት ወር በኋላ…ሚስት “አንገበገበኝ!” “አሁንስ መድረሻ አሳጣኝ!” ብሎ መማረር የለም፡፡ ይቀምሳታላ!
በቀደም አንድ ኤፍ ኤም ፕሮግራም ላይ በሚስቶቻቸው የሚደበደቡ ባሎች ማህበር ሊያቋቁሙ ነው የሚል ነገር ሰምቼ እንደተመቸኝ፡፡ እንዲህ እቅጯን ማሳወቅ ነው፡፡
አሀ…‘በግራ ጎኖቻቸው’ ይደበደባሉ ብዬ የምጠረጥራቸው ወዳጆች አሉኛ! (እንትና የበቀደሙ የጉንጭህ ላይ ሰንበር…መቼም ‘ታቱ’ ነው አትለኝም!) ስሙኝማ… አንድ ወዳጅ ነበረን፡፡ እናላችሁ… እንትናዬው የእሱን ‘ሁለት ከግማሽ’ ትሆናለች፡፡ ታዲያ ማታ አብረው ቀማምስው ሲገቡ መጀመሪያ ‘ለካፊው’ እሱ ነው፡፡ ከዛማ ምን አለፋችሁ… ታጣድፋዋለቻ! አድራሻውን ሳውቅ የዚህን ማህበር ነገር ሹክ እለዋለሁ፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በዚህ የጂም ጉዳይ ሀሳብ አለን፡፡ ለሚስቶች ብቻ ጂም ይዘጋጅልንማ! ልጄ የምንሰማው ነገር ሁሉ…“ለካ ከተሜው ሁሉ ጡንቻ በጡንቻ ለመሆን የሚሞክረው ዝም ብሎ አይደለም…” ያሰኛል፡፡ በየወሩ ጂም የሚለዋውጡ እንትናዬዎችም አሉ ይባላል፡፡ ‘ቀለብ’ ፍለጋ ነዋ! ‘ምግብ ለሥራ’ በሉት፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ሌላም ሀሳብ አለን…ለምስኪን ወንዶች የተለየ ጂም ይዘጋጅልን፡፡ አሀ…እንትናዬዎቹ እነ ቫን ዳምን እያዩ ሲሳሳቁብን እኛ ተሳቀን አለቅና!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የግራ ጎን ነገር ካነሳን አይቀር ህጻናት ወንድምና እህት እየተጫወቱ ነው፡፡ እናላችሁ…ወንዱ ይመታትና ታለቅሳለች፡፡ አባትም…
“አንተ ማሙሽ እህትህን ለምን መተሃት?” ሲል ይቆጣዋል፡፡ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አዳምና ሔዋን እየተጫወትን እያለ አፕሉን ቀጥፋ እኔን ማስጎምጀት ሲገባት ራሷ በላችው…” ብሎት አረፈው፡፡ አፕሉን ቀጥፋችሁ ራሳችሁ የምትበሉ እንትናዬዎች የአዳምና የሔዋንን ታሪክ አስታውሱማ!
የ‘ሳንታ ክላውስ’ ነገር ግራ የገባው አንድ ህጻን ልጅ ምን ብሎ ቢጠይቅ ጥሩ ነው… “የገና አባት ሲተኛ ጺሙን ከብርድ ልብሱ ስር ነው ወይስ በላይ የሚያደርገው?” አሪፍ አይደል! ይሄንን ለሚመለስ ስፖንስር የሚያደርግ ከተገኘ ሦስት ጣሳ ሚጥሚጣ እንሰጣለን፡፡ ‘እየሰማን’ ከምንጠበስ ‘እየበላን’ ብንጠበስ ይሻላላ! ቂ…ቂ…ቂ…
እንትና የወንፊቷን ነገር አደራ በሰማይ፣ አደራ በምድር፡፡ ደግሞ ትንሽ ድፍን ምስር ቢጤ ልትጨምርባት ከቻልክ…ቅር አይለኝም፡፡ ደግሞም “ሦስተኛውን አማራጭ ወስጃለሁ…” የምትል ከሆነ… (ቀጥሎ የምታነበው ለሚያስከትልብህ የጤና ችግር ሀላፊነት የለብንም!)… ‘ስማርት ፎን’ ላክልኝማ፡፡ ታዲያ ምን ላድርግ…የማውቃቸው ‘ስማርት’ ሰዎች ቁጥር እያነሰ ስለሄደ ባይሆን ስልኬ እንኳን ‘ስማርት’ ይሁንልኝ!
መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4266 times