Monday, 05 January 2015 08:20

ህያው ህይወት

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(10 votes)

“ህይወት ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀ እዝራ፡፡
አሰበ አሰበና መልሱን ያገኘው መሰለው፡፡ “ህይወት መስታወት ናት!” አለ፡፡
“ለሚስቅላት የምትስቅ፤ ለሚኮሳተርባት የምትኮሳተር!” የቤቱ በረንዳ ላይ እንደተቀመጠ ሲጋራውን ለኮሰ፡፡ ለኮሰና ይምገው ገባ፡፡
አንዳንዶች ሲሳካላቸው ለሌሎች የማይሳካው ለምንድን ነው? ሲል ጠየቀ፡፡
እኩል አቅም እንደውም የተሻለ አቅም እያላቸው የማይሳካላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ምስጢሩ ምንድን ነው? አንዳንዶች ህይወትን አይመሯትም፡፡ የምትመራቸው ህይወት ናት፡፡ የምትመራን ህይወት ከሆነች መውደቂያችን የት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ህይወት የሆነ ጢሻ ውስጥ ወትፋን ዞር ልትል ትችላለች፡፡ ስለዚህ ዋናው ቁም ነገር በህይወት አለመመራት ነው፡፡ አለመመራትና በተቃራኒው ህይወትን መምራት መቻል ነው ወደ ስኬት የሚወስደው ፍኖት፡፡
ህይወት ግን ምንድን ናት?!
የማትታይ የማትዳሰስ ህቡዕ ገብታ በግልጥ የምትነዳ፡፡ ህይወት ህቡዕ ብትገባም እኛን ይዛን አትገባም፡፡ እኛን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ መሰወርን ትመርጣለች፡፡ ህይወት ህቡዕ ትግባ እንጂ እኛ ከእሷ ጋር ህቡዕ እንድንገባ አትፈቅድም፡፡
እንደፍጥርጥራችን እንድንሆን ለራሳችን ትተወናለች፡፡ ዘመኑ የፉክክር ነው፡፡ ተፎካክሮ አሸናፊ ሆኖ መገኘት ደግሞ መታደል ነው፡፡ ህይወታችን እስከአለ ድረስ በህይወት መድረክ ላይ መተወናችን አይቀርም፡፡ አተዋወኑ እንዴት ነው? ነው ጥያቄው፡፡ ህይወትን በጥሩ ሁኔታ ተወነናታል ወይስ አልቻልንም? ተውኔቱን በአግባቡ የተጫወተና የትወና ብቃቱን ያሳየ አሸናፊ ሆኖ ይወጣል፡፡
Survival of the fittest ነው ነገሩ፡፡
ብቁ የሆነው ግለሰብ በአሸናፊነት ይወጣዋል፡፡
ብቁ ያልሆነው ደግሞ እዛው ባለበት እያከከ ይኖራል፡፡
አመሻሽ ነው፡፡
አየሩ እየቀዘቀዘ ሄደ፡፡ እዝራ ወደ ቤት ገብቶ ጋቢ ደርቦ ተመለሰ፡፡ ከፊቱ የተለያዩ መፅሐፍት ጠረጴዛው ላይ ተደርድረዋል፡፡ አንዱን ሲያነብ ይቆይና ሲደብረው ሌላኛውን አንስቶ ያነባል፡፡ የንባብ ሱሰኛ ነው፡፡
ሳያነብ ከዋለ ጤና አይሰማውም፡፡
ከስራ ውጭ ያለውን ጊዜውን በንባብ ለማሳለፍ ይሞክራል፡፡ ተግዳሮቶች ግን አሉበት፡፡ ጓደኞቹ ከስራ ሰዓት በኋላ አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ማሳለፍን ይመርጣሉ፡፡ እና እሱንም ይጠሩታል፡፡ አንዳንዴ ይቀላቀላቸዋል፡፡ አንዳንዴ ትቷቸው ወደ ቤቱ ይገባና ያነባል፡፡ ሁሌ ግን በእምቢታው አይፀናም፡፡ የጓደኞቹ ውትወታ ያሸንፈውና ሳያነብ ያመሻል፡፡ ከእነሱ ጋር ሲጫወት አምሽቶ ከሆነ ወደ ቤቱ ገብቶ ሊተኛ ሲል፣ አንድ መፅሐፍ ይዞ አልጋ ላይ በመውጣት እንቅልፉ እስኪመጣ በማንበብ ያሳልፋል፡፡ የስራ ባልደረቦቹ ጠጠርና መጠቅ ያለ ነገር አይመቻቸውም፡፡ አለመመቸት ብቻ ሳይሆን አቅማቸውም ስለማይፈቅድላቸው ከእሱ እኩል መራመድ አይችሉም፡፡ እሱ ደግሞ የሚወደው ከበድ ካለ ነገር ጋር መታገል ነው፡፡ የሼክስፒር እንግሊዝኛ ይፈታተነዋል፡፡ ቢሆንም ግን እጅ አይሰጥም፡፡ መዝገበ ቃላቱን ከአጠገቡ አድርጐ ይታገለዋል፡፡ ዛሬም የሼክስፒርን ቄሳር የተሰኘ ልብወለድ (ተውኔት) እያነበበ ነው፡፡ ልክ ውሃ እንደምትጠጣ ዶሮ አጐንብሶ የተወሰኑ ዐ.ነገሮችን ከለቀመ በኋላ ቀና ብሎ ያብሰለስለዋል፡፡ ጨረቃዋን እያየና ውበትዋን እያደነቀ ስለመፅሐፉ ጭብጥ ያብሰለስላል፡፡
እዝራ በአሜሪካዊትዋ ደራሲና ፈላስፋ አየንራንድ አባባል ያምናል፡፡
ሼክስፒር “መሆን አለመሆን ይኼ ነው ጥያቄው” (To be or not to be this is the question) ይላል፡፡ ራንድ ይህን አባባል ትወስድና ታጐነዋለች:-
“The question to be or not to be is the question to think or not to think!” ትላለች፡፡ (ያ መሆን አለመሆን ጥያቄ የማሰብ ያለማሰብ ጥያቄ ነው፡፡)
ጓደኞቹ ስለ ሀሳብ ያላቸው ሀሳብ ይገርመዋል፡፡ ለምንም ሆነ ለምንም ግድ የላቸውም፡፡ ዝም ብሎ መኖር ብቻ፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ የቢሮ ስራ መስራት፤ መተኛትና መነሳት፤ ይኸው ነው፡፡
“መኖር ብቻ አይበቃም” ይላል እዝራ፡፡
“የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ” ብቻ እያሰቡ ለእዚያ የሚሰሩ ልቦናቸው የታወረባቸው ሰዎች ናቸው - ይላል፡፡
“የሰው ልጅ ትልቅ ተልዕኮ የሸከመ ፍጡር ነው፡፡” ብሎ ያምናል፡፡
ነገሮችን ለማቃናት፤ ያልተሰራን ለመስራት፤ ያልታሰበን ለማሰብ፣ ያልተባለን ለማለት ዝግጁ መሆን ከእያንዳንዱ የሰው ዘር የሚጠበቅ ነው - ይላል፡፡ የመሆን ያለመሆን ጥያቄ የማሰብ ያለማሰብ ጥያቄ ሆኗል - (ነው) ብላለች ራንድ፡፡
ሰው ከእንስሳት የሚለየው፤ ሰውም ከሰው የሚበላለጠው በማሰብ ነው፡፡ ሰው በሀሳቡ ልክ የተቀነበበ ፍጡር ነው፡፡
ምናቡን ሲያሰፉ እሱም ሀሳቡም ይሰፋሉ፡፡ በጥቃቅን ነገሮች ላይ ከተወሰነም በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ይኖራል፡፡ ዓለምን ያገነናት ዋናው ነገር ሀሳብ ነው፡፡ ሀሳብ ምን ጊዜም ከፊት ይቀድማል፡፡ ያሻውን ሰው፤ ወዳሻው ቦታ ይመራል፡፡ ሃሳብ አልባ ሰዎች ግዑዛን ናቸው፡፡ ከሰውነት መመደባቸውም አከራካሪ ነው፡፡
ሀሳብ ነው ዓለምን የሚመራው፡፡
ስለዚህ ሰዎች አሳባዊያን መሆን ይጠበቅባቸዋል፡
ሁሉም ቀን አንድ አይደለም፡፡ ዛሬ ከትላንት ይሻላል፡፡ ነገ ደግሞ ከዛሬ!...
ዓለም በሂደት ላይ ነች፡፡ ሃሳብ ያለው ሂደቱን ይመራል፡፡ ሃሳብ የሌለው ደግሞ ከዓለም ጋር በአሳቢው ይመራል፡፡ ብዙዎች ዕጣ ፈንታቸው፣ ከቀዳሚዊያኑ አሳቢ መሪዎች ጋር ሳይሆን ከሚመራው ዓለም ጋር ያለሃሳብ መመራት ነው፡፡
አንዱ መሪ፣ ዘጠኙ ተመሪ ወይም ተከታይ ነው፡፡ ብዙው ጥሩ ተመሪ መሆን እንኳን አይችልም፡፡  ጥሩ ተመሪ መሆን በራሱ አንድ እራሱን የቻለ ተሰጥኦ ወይም ስጦታ ሳይፈልግ አይቀርም፡፡
እዝራ “ዓለምን የለወጠው ሃሳብ ነው!” ብሎ ያምናል፡፡ ከአውሮፕላን መስራት በፊት ሀሳብ ነበር፡፡ ሁለቱ የራሮት ወንድማማቾች አእዋፋትን አይተው አውሮፕላን መስራት እንደሚቻል አስቡ፡፡ አስበውም አልቀሩ፤ አውሮፕላኑን ሰሩ፡፡
ቢል ጌት፤ ኮምፒውተር የሚባል ነገር በመስራት የሰውን አድካሚና አሰልቺ ህይወት ማቅለል እንደሚችል አሰበ፡፡ እና ኮምፒውተርን ፈጠረ፡፡
ፎርድ፤ የሰው በእግርና በአጋሰስ (በጋማ ከብቶች) መጓጓዝ አድካሚ መሆኑን አይቶ መኪና ለመስራት አስቦ፡፡ አስቦም አልቀረ፤ መኪናን ለዓለም አበረከተ፡፡ ማርክ ዙከርበርግ የዓለም ህዝብ በኑሮ አስገዳጅነት ማህበራዊነቱ እየተዳከመ መምጣቱን አይቶ፤ ማህበራዊ ኑሮን የሚያበረታታ ነገር ለመፍጠር አስቦ ፌስቡክን ፈጠረ፡፡
እውነት ነው፤ ዓለም የምትመራው በሀሳብ ነው፡፡ ሀሳብ ከሁሉ ቀዳሚ የሆነ ነገር ነው፡፡
የፈጠራ ሥራ መሪው ሃሳብ ነው፡፡ ምድር ላይ ያለውን ሰው ሰራሽ የሆነ ነገር ሁሉ ብንመለከት ወደ አሁን ማንነቱ ከመምጣቱ በፊት ሃሳብ ነበር፡፡ ሀሳብ ፊታውራሪ ነው፡፡ ሌላው ነገር ሁሉ ከሀሳብ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡
እዝራ ውጪው ሲጨልም መፅሐፎቹን ሰብስቦ ወደ ቤት ገባ፡፡ ሲያነብ ከቆየ በኋላ የእንቅልፍ ሰዓቱ በመድረሱ አልጋው ላይ ወጥቶ ጥቅልል ብሎ ተኛ፡፡

Read 8005 times