Monday, 05 January 2015 08:23

የጠፉት በጐች

Written by  ተስፋዬ ገድሉ (ከመገናኛ)
Rate this item
(14 votes)

     የባለፀጋው ሶስቱ ቅጥር እረኞች፣ በቀዝቃዛው ማለዳ ጠዋት ከእንቅልፋቸው የነቁት በጐቹ ግድግዳውን ሲታከኩ በፈጠሩት መጓጓት ነበር፡፡
መፅሃፉን ሲያነቡና ሲከራከሩ አምሽተው ስለተኙ እንቅልፋቸውን ባይጨርሱም ባለቤቱ ከተነሳ የሚደርስባቸውን ቁጣ በማሰብ እየተነጫነጩ ከፍራሻቸው ተነሱ፡፡ ልብሳቸውን ከደራረቡ በኋላ ትንሽ ራቅ ያለው ሜዳ ላይ በጐቹን አሰማርተው፣ እነሱ እልፍ ብለው ከፍ ያለ ድንጋይ ላይ በዝምታ ሳይነጋገሩ ተቀምጠው የፀሃይዋን መውጣት መጠበቅ ጀመሩ፡፡
ቀኑ ረፈድፈድ ሲል ፀሃይዋን በደንብ ከሞቁ በኋላ የቋጠሩትን ምግብ ተመግበው አረፍ ሲሉ እንቅልፍ ስለተጫጫናቸው፣ በጐቹን ለአንዱ እረኛ አደራ ሰጥተውት ሁለቱ ዋና ሊዋኙ ወደ ወንዝ ወረዱ፡፡ ብቻውን የቀረው እረኛ የተቀመጠበትን ዋርካ እንደተደገፈ አሸለበው፡፡ከሰአታት በኋላ ከእንቅልፉ በርግጐ የተነሳው ሁለቱ ጓደኞቹ ተመልሰው መጥተው በጩኸት ሲቀሰቅሱት ነበር፡፡ እረኞቹ ከበጐቹ መሃል ሶስቱ እንደጐደሉ አውቀው በጣም ተረበሹ፡፡ ከእነሱ በፊት የነበሩት የባለፀጋው ቅጥር እረኞች፣ ሁለት በግ ስለጠፋባቸው ባለፀጋው አርባ አርባ ጅራፍ አስገርፏቸው የአራት ወር ደሞዛቸውን ሳይሰጣቸው እንዳባረራቸው ያውቃሉና በፍርሃት እንደተደነባበሩ በጐቹን ፍለጋ ጀመሩ፡፡ቀበሮ በልቷቸው ይሆናል በማለት አካባቢውን ቢፈትሹም ለምልክት የሚሆን ደም፣ ፀጉር ወይም የተቆራረጠ አካል አልነበረም፡፡
 ጀንበር እስክትጠልቅ ለሰአታት ሲንከራተቱ ቆይተው ምንም ስላላገኙ፣ ተስፋ በመቁረጥ በሃዘን አንገታቸውን ደፍተው የቀሩትን በጐች እየነዱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ቤታቸው ደርሰው በጐቹን ከበረቱ ሲያስገቡ በተመለከቱት ነገር ሶስቱም በድንጋጤ በር ላይ ደርቀው ቀሩ፡፡ እዚያ በረት ውስጥ በብርሃን የተከበቡ፣ አንድ የሚያንቀላፋ ህፃን የታቀፈች ሴትና አንድ ወንድ ሰውዬ ወደ አንዱ ጥግ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡እረኞቹ ይህን ሲያዩ ትላንት ማታ ቅዱስ መፅሃፍ ላይ ሲያነቡት ያመሹት የነበረው ፅሁፍ ትዝ አላቸው፡፡“ዛሬ በዳዊት ከተማ መድሃኒት እርሱም ክርስቶስ የሆነ ተወልዶላችኋልና ይህም ምልክት ይሆናችኋል፡፡
ህፃኑን ተጠቅሎ በግርግም ታገኙታላችሁ፡፡” ወዲያውኑም ሶስቱም እረኞች በጉልበታቸው ወድቀው በግንባራቸው መሬቱን እየሳሙ ለህፃኑ ሰገዱለት፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲሆን የህፃኑን እናትና አብሯት ያለውን ሰው እየመሩ ወደዚህ ቦታ ያመጧቸው ሶስቱ የጠፉት በጐች ወደ በረቱ መመለሳቸውን እረኞቹ ልብ አላሉም ነበር፡፡

Read 3091 times