Monday, 05 January 2015 08:51

ኢንዶኔዢያውያን አዲሱን አመት በሃዘን ተቀብለውታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ162 መንገደኞች እስካሁን የ7ቱ አስከሬን ተገኝቷል

ባለፈው እሁድ 162 ሰዎችን ይዞ በበረራ ቁጥር 8501 ከኢንዶኔዥያዋ ሱራያባ ከተማ ወደ ሲንጋፖር በመጓዝ ላይ እያለ ድንገት የተሰወረው ንብረትነቱ የኤርኤዥያ አየርመንገድ የሆነው ኤርባስ ኤ320-200 አውሮፕላን እጣ ፋንታ አለምን አሳዝኗል፡፡ ኢንዶኔዢያውያንም አዲሱን የፈረንጆች አመት በጥልቅ ሃዘንና በአስከሬን ፍለጋ ተቀብለውታል፡፡
አውሮፕላኑን መሰወሩን ተከትሎ ኢንዶኔዢያና ሌሎች አገራት በመርከብና በአውሮፕላን ታግዘው ለፍለጋ በተሰማሩ በሶስተኛው ቀን የተሰማው ነገር፣ አዲስ አመትን በደስታ ለማክበር ለተዘጋጁ ኢንዶኔዢያውያን ትልቅ መርዶ ሆኗል፡፡
137 አዋቂዎች፣ 17 ህጻናት አንድ ጨቅላ፣ ሁለት አብራሪዎችና አምስት የበረራ ሰራተኞች፣ ሁሉም የጃቫ ባህር ውስጥ ሰምጠው ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት መንገደኞች 155 ኢንዶኔዢያውያን፣ 3 ደቡብ ኮርያውያን፣ አንድ እንግሊዛዊ፣ አንድ ፈረንሳዊ፣ አንድ ማሌዢያዊና አንድ ሲንጋፖራዊ ነበሩ ተብሏል፡፡
ለአውሮፕላኑ መከስከስ በሰበብነት የተጠቀሰው አስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታ ሲሆን፣ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ የማጣራቱ ሂደትና የመንገደኞችን አስከሬን የማውጣቱ ሂደት እንደቀጠለ ነው፡፡ እስካለፈው ረቡዕ ድረስም የአራት ወንድ እና የሶስት ሴት መንገደኞች አስከሬን ከባህር መውጣቱንና በአካባቢው ያለው የአየር ንብረት ሁኔታ ፍለጋውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኢንዶኔዢያው ፕሬዚደንት ጆኮ ዊዶዶ ግን ምንም እንኳን አስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታው ፍለጋውን እጅግ አዳጋች ቢያደርገውም፣ አስከሬንና የአውሮፕላኑን ስብርባሪዎችን የማውጣቱ ስራ በመርከቦችና በሄሊኮፕተሮች በመታገዝ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለፈው ማክሰኞ አስታውቀዋል፡፡
በራዳር መረጃዎች ላይ በተደረገ ማጣራት፣ አውሮፕላኑ ከሚገባው የበረራ ከፍታ በላይ ወጥቶ እንደነበርና ይህም ለመከስከሱ ምክንያት እንደሆነው የሚያመላክቱ መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ጥሩ የሚባል የደህንነት ታሪክ እንደነበረው ያስታወሰው ዘገባው፣ በአውሮፕላኖቹ ላይም ይህ ነው የሚባል አስከፊ አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1555 times