Saturday, 10 January 2015 09:33

ምን ያደርጋል ስላስገመገመ፤ ፏ ብሎ ካልዘነመ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

(ምር ያሜቴ የንግበከቤ ፏ አሚተኽ ባንዘነቤ)
(የጉራጊኛ ተረት )
      ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ሊቅ አዋቂ የተባሉ ሳይንቲስቶች ስለንጉሣቸው ሲወያዩ አንደኛው፤
“ንጉሦችና መሪዎች ብዙ ስራ ስለሚበዛባቸው ለዕውቀት ብዙ ቦታ አይሰጡምና ግኝቶቻችንን እንድናሳውቃቸው በየጊዜው እየቀረብን ንግግር እናድርግላቸው” ይላል፡፡
ሁለተኛው፤
“ወዳጄ ሞኝ አትሁን! ንጉሦችና መሪዎች የሚበልጣቸውን ሰው አይወዱም፡፡ ስለዚህም ከማዳመጥና ከመለወጥ ይልቅ አንተን ዝም የሚያሰኙበትን መንገድ ነው ሲያሰላስሉ የሚያድሩት፡፡ የሚሻለው አንተ ድምፅህን አጥፍተህ ምርምርህን መቀጠል ነው፡፡”
አንደኛው፤
“ግዴለህም እንሞክር፡፡ እስከዛሬ ያላወቁትን ነገር ስትነግራቸው በዚያ ይማረኩና፣ ንግግርህን በማድነቅ እንዲያውም ሽልማትና ሹመት ሁሉ ሊሰጡህ ይችላሉ፡፡”
ሁለተኛው፤ ትንሽ ከረር ብሎ፤
“ወዳጄ! ሳይንቲስት ሆነህ እንዴት ሽልማትና ሹመት ያምርሃል፡፡ ዓለም ካንተ ሥራ ውጤት በመጋራት የጥበብህ ተጠቃሚ ለመሆን እንዲችል ለማድረግ መጣጣርህን ትተህ ንጉሥ ንግግሬን ያዳምጡ በማለት እንዴት ልብህን ታወልቃለህ? ይልቁንስ ሊዮናርዶ ዳቬንቺ ያለውን አንድ ምሳሌ ልንገርህ፡-
አንደኛው፤ “ምን አለ?”
ሁለተኛው ቀጠለ:-
‹የባህር እንስሳት የሆኑት ኦይስተሮች ጨረቃ ሙሉ በሆነች ሰዓት አፋቸውን በሰፊው ሙሉ ለሙሉ ይከፍታሉ፡፡ የፈረስ ጫማ ቅርፅ ያላቸው የውሃ እንስሳት ክራቦች ደግሞ የተከፈተውን የኦይስተሮች አፍ ሲያዩ ጠጠር ወይም የባህር አረም ይወረውሩና እዚያ አፍ ውስጥ ይከታሉ፡፡ ኦይስተሮቹ አፋቸውን መግጠም ያቅታቸዋል፡፡ እንደዚያው አፋቸውን አንደከፈቱ ክራቦቹ ምግብ ያደርጓቸዋል፡፡ አፉን በብዛት የሚከፍት ሰው ዕጣ - ፈንታም እንደዚያው ነው፡፡ የሰሚው ሰለባ ይሆናል፡፡” አለው፡፡
* *  *
የምንናገረውን እንወቅ፡፡ የምናውቀውን መጥነን እንናገር፡፡ ለምንናገረው ቦታና ጊዜ እንምረጥ፡፡ የሰሚያችንን ስሜትና እንቅስቃሴ እናጢን፡፡ ቢያንስ በወጉ እንገምት፡፡ “ካፍ ከወጣ አፋፍ” የሚለውን ተረት ለደቂቃም ቢሆን አንዘንጋ!
መጥኖ ትንሽ መናገር ኃይልና አቅምን ማግኘት ነው፤ የሚለውን እንደሚባል ብዙ ፀሐፍት ይናገራሉ፡፡ አንዲ ዋርሆል የተባለው አርቲስት “በህይወቴ የተማርኩት ነገር ቢኖር ዝም ባልኩ ቁጥር የበለጠ ኃይል እንዳለኝ ነው፡፡ ለነገሩ ብዙ አለመናገር ጅል ንግግር ከመናገርም ያድናል” ይለናል፡፡
በሩሲያ የታህሣሣውያን አመፅ (Decemberist Uprising) በመባል የሚታወቀው ንቅንቄ መሪ የነበረውን ኮንድራቲ ራይሌዩቭ ንጉሥ ቀዳማዊ ኒኮላስ ሞት ይፈርድበትና አንገቱ ላይ ገመድ ይጠልቃል፡፡ ከስር የቆመበት ወንበር ሲነሳ ይሰቀላል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ገመዱ ተበጠሰና ዳነ፡፡ በዚያን ጊዜ ዕምነት፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲከሰት አምላክ መሞቱን አልፈለገም ስለሚባል፤ በል የመጨረሻ ይቅርታ ጥያቄ አቅርብ ተባለ፡፡ ተሰቃዩ እንዲህ አለ፡- “አይ ራሺያ! ገመድ እንኳ በትክክል የማይገመድብሽ አገር!” ንጉሡ፤ “ምን አለ?” ብለው ጠየቁ፡፡ ያለውን ሲነግሯቸው፤ የይቅርታ ደብዳቤውን ቀደዱና “በሉ ጠንካራ ገመድ ሥሩና አሳዩት!” አሉ ይባላል፡፡ ጊዜና ቦታን ማወቅ ለሁሉ ነገር ቁልፍ ነው፡፡
ሀገራዊ ስሜትና ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ካልተዋሃዱና፤ በዚያም ላይ ብስለት ካልታከለበት ሁነኛ ለውጥና ዕድገት ለማምጣት ብዙ ጊዜ አዳጋች ነው፡፡ ወቅታዊ ትኩሳት፣ ስሜታዊነት ወይም በፖለቲካዊ አጠራሩ አብዮታዊ ወኔ ብዙ ጊዜ፤ ከድርጊቱ ሞቅ ሞቁ፣ ከተግባሩ ፉከራው፣ መሬት ከረገጠ ለውጡ፤ አየር ባየር የሚሄድ የወሬ ንፋሱ፤ ይበረክታል፡፡ በዚህ ምክንያት ዕሙናዊና ተጨባጭ ለውጥ ከማግኘት ይልቅ እንደሳሙና አረፋ የሚኩረፈረፍ ስሜታዊነት ብቻ ይታያል፡፡ “ምን ያደርጋል ስላስገመገመ፣ ፏ ብሎ ካልዘነመ” የሚለው የጉራጊኛ ተረት የሚጠይቀን ይሄንኑ ነው፡፡

Read 4688 times