Saturday, 10 January 2015 09:34

የምርጫ ሂደቱ በኢህአዴግ ዓይን

Written by 
Rate this item
(72 votes)

•    ኢህአዴግ ዲሞክራሲን የሚያየው በእውነተኛ ገፅታው ነው
•    ምርጫ በውጤት አይመዘንም፤ ዋናው ሂደቱ ነው
የግንቦቱን ምርጫ እየተቃረበ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ የተለያዩ ቅሬዎችንና ተቃውሞዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግስ ምን ይላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋውን በምርጫው ዝግጅትና ሂደት ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡
እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት ምን ይመስላል?
በኛ በኩል የምርጫው ሂደት በተቀመጠለት አቅጣጫ መሠረት እየሄደ ነው፡፡ ቀድመን ስትራቴጂና እቅድ አዘጋጅተናል፡፡ ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ለመንቀሳቀስ ዝግጅት አድርገን ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ሃገሪቱን እንደሚመራ ገዢ ፓርቲና ተወዳዳሪ ፓርቲ ሁለት ሚናዎች ነው ያሉት፡፡ በመንግስት በኩል (ሀገሪቱን የሚመራ ፓርቲ እንደመሆኑ) ምርጫውን ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሠላማዊ በማድረግ ረገድ እየተሠራ ነው፡፡ እንደ ተወዳዳሪ ፓርቲ ደግሞ አሸናፊ ሆነን የምንወጣበትን አጠቃላይ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ እንደ ድርጅት፣ በስነምግባር ደንቡና በአጠቃላይ በምርጫ ህጐቹ ሂደት ላይ የአሠልጣኞች ስልጠና በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ሰሞኑን ተሰጥቷል፡፡
በየደረጃው ለሌሎችም ስልጠናው ይሰጣል፡፡ ካለፉት ምርጫ ልምዶች ተነስተን 5ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ ወሳኙ ህዝብ ስለሆነ የህዝቡን ወሳኝነት ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ከህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ጋር ተያይዞ ተቃዋሚዎች፤ “ኢህአዴግ የ1ለ5 አደረጃጀቱን ተጠቅሞ አባላቱን አስመርጧል” ሲሉ ይወቅሣሉ፤ በዚህ ላይ የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው?
የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫን በተመለከተ አንዳንድ ፓርቲዎች መሠል አስተያየቶችን ሲያቀርቡ ሰምተናል፡፡ አንደኛው ወቀሳቸው፣ የታዛቢዎች ምርጫ የተካሄደው ለኛ ሣይነገረን ኢህአዴግ ብቻ ተነግሮት ነው የሚል ነው፤ ይሄ በጣም መሠረታዊ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም ኢህአዴግም እነዚህ ፓርቲዎችም ባሉበት የምርጫ ጊዜ ሠሌዳው ቀርቦ ውይይት አድርገንበታል፡፡ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሠሌዳ ኢህአዴግን ጨምሮ ለእያንዳንዱ ፓርቲ አቅርቧል፡፡ ስለዚህ ታህሣሥ 12  የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች በሚዲያም ቀርበው ታህሣሥ 12 የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ በሚስጥር የተደረገ ነው፤ የሚለው የተሣሣተ ነው፤ በይፋ በደብዳቤም በሚዲያም ተገልጿል፡፡
በእለቱም ኢህአዴግ አባሎቹ እንዳይመረጡ ጥንቃቄ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ቦታ እንኳ አባሎቻችን ሲጠቆሙ “እኔ አባል ነኝ፤ አልችልም” ብለው ከምርጫው የወጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ የተቃዋሚዎች ውንጀላ የተለመደ ሂደቱን ከጅምሩ ጥላሸት የመቀባት አካል ነው፡፡ የተመረጡት የህዝብ ታዛቢዎች ገለልተኛ አይደሉም ለማስባል የሚረዳ ተራ የስም ማጥፋት ሂደት ነው፡፡
1ለ5 የሚባለው ለመንግስት የልማት ስራ የተደራጀ ነው እንጂ የፓርቲው አደረጃጀት አይደለም፡፡ የተቃዋሚም የኢህአዴግም አባል የሆነ ሊኖር ይችላል፤ ስለዚህ የ1ለ5 አደረጃጀትን ሂዱና የህዝብ ታዛቢ ምረጡ ቢል ችግር የለውም ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግን ምረጡ ወይም ደጋፊ የሆነን ሰው ምረጡ የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ በ1ለ5 አደረጃጀት ላይ ብዥታ ሊኖር አይገባም፤ አደረጃጀቱ የልማት አደረጃጀት ነው፡፡ ይህን አደረጃጀት ሂዳችሁ ታዛቢ ምረጡ ወይም በምርጫው ተሳተፉ ቢል ነውር አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ህዝቡ ገለልተኛ ናቸው ያላቸውን ታዛቢዎቹን መርጧል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ውንጀላዎች ተቀባይነት የሌላቸው፣ ሂደቱን ጥላሸት ለመቀባት ሆነ ተብሎ የሚደረጉ ናቸው፡፡ የኢህአዴግ አባል ተመርጧል የሚሉ ከሆነና የተመረጠበትን ቦታ ከጠቆሙ እኛም ለማጣራት  ዝግጁ ነን፡፡ ድንገት ሾልኮ የገባ ካለም እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ እስካሁን ግን እንዲህ ያለ ነገር ስለመኖሩ ምንም መረጃ የለንም፡፡ ህዝቡ  ምርጫውን ማካሄዱ መብቱን ማረጋገጫ መንገድ ነው፡፡
የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር ኢህአዴግ ለመወያየት የማይችልበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ደንቡን መፈረምን እንደ ግዴታ ማስቀመጥ የውይይት በርን መዝጋት አይሆንም?  
ደንቡ ሲዘጋጅ ብዙ ሂደት አልፏል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ፓርቲዎች በእርጋታ እየተወያዩ ያለፉበት ሂደት ነበር፤ በዚህ ሂደት መድረክ ሶስት ጊዜ ረግጦ ወጥቷል፡፡ መጀመሪያ ሂደቱ ሲጀመር ወደ ውይይቱ ተጋብዞ መጣ፤ ያኔ ከኢህአዴግ ጋር እንጂ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር መወያየት የለብኝም አለ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ብዙ ፓርቲዎች ባሉበት ሃገር፣ የተናጥል ውይይት ከእያንዳንዱ ጋር ማድረግ አይችልም፡፡ መድረክ፤ ሌሎች ፓርቲዎች ተቃዋሚዎች አይደሉም የሚል አመለካከት ስለለው ወጣ፡፡ በሌላ ጊዜም ተጋበዘ፤ ሂደቱን ትቶ ወጣ፡፡ ለ3ኛ ጊዜ 65 ፓርቲዎች ሲወያዩ ገብቶ ሂደቱን ለመበተን ነው ጥረት ያደረገው፤ ግን መጨረሻ ላይ 65 ፓርቲዎቹ ተስማምተው ህግ ሆኖ ወጣ፡፡ ህግ ሆኖ ሲወጣ በህጉ ውስጥ የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ አለ፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ አባል ሆኖ ለመቀጠል የፈለገ ፓርቲ ህጉን መፈረም አለበት፡፡ ይሄ ማለት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ የስነ ምግባር ደንቡ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ፓርቲዎቹ በራሳቸው ሊገፉት ይገባል ማለት ነው፡፡ የፊርማ ቅድመ ሁኔታን ኢህአዴግ አላስቀመጠም፤ ራሱ ህጉ ያስቀመጠው ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ በስነምግባር መመራቱን, የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን ቀድሞ ማረጋገጥ አለበት ነው የሚለው ህጉ፡፡ ይህን ያረጋገጡ የጋራ ምክር ቤት ውስጥ እየሠሩ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ጋር እነዚህ ፓርቲዎች በፕሮግራም የተለዩ ናቸው፡፡ በምርጫ ሂደቱ ላይ ግን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው የበሠለ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስነ ምግባሩ ያስረናል ብለው ስለሚያስቡና አመፅና ብጥብጥ ለማስነሳት ያግደናል ብለው ስለሚያስቡ ቁርጠኝነት ስላነሣቸው ነው እንጂ ኢህአዴግ በተናጥል አልደራደርም ስላለ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ተስማምተን ህግ ሆኖ በወጣ ጉዳይ ላይ lምንድን ነው ተመልሰን ወደ ድርድር የምንገባው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፤ ስለዚህ ተመልሰን ወደ ድርድር የምንገባበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሁንም ምርጫ ቦርድ በሚጠራቸው ስብሰባዎች ላይ አብረን እንሣተፋለን፤ የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ለመግባት ግን ድርድር አያስፈልገውም፤ በስነምግባር ለመገዛት መስማማት ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ያለፈባቸውን ሂደቶች ስናይ ሁልጊዜም በድርድር የሚያምን መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ለምንድን ነው የአለማቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ስነምግባር ተገዥ ሆናችሁ፣ ለፍትሃዊና ሠላማዊ ምርጫ ውድድር ዝግጁ ያልሆናችሁት የሚለውን ጥያቄ ተቃዋሚዎች መመለስ አለባቸው፡፡ በስነምግባር እንመራ የሚል ውይይት ማካሄድ እንዴት ይቻላል፡፡
ደንቡን ያልፈረሙ መድረክን የመሣሠሉ ድርጅቶች ከኢህአዴግ ጋር መወያየት ቢፈልጉ እንዴት ነው የሚስተናገዱት?
በተቀመጡ ማዕቀፎች መሠረት ይስተናገዳሉ፡፡ ገለልተኛ የሆነው የምርጫ ቦርድ አለ፡፡ ያልተሟሉ ነገሮች ካሉ ለምርጫ ቦርድ እያቀረቡ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በተቋማዊ አሠራር የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ የስነምግባር ደንቡ በሌለበትና የጋራ ምክር ቤቶች ባልተቋቋሙበት ሁኔታ ጥያቄው ቢቀርብ ትክክል ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ፓርቲ ጋር ኢህአዴግ እየተወያየ ሊሄድ ይችላል፡፡ አሁን ግን የጋራ ማዕቀፍ  በተዘረጋበት ኢህአዴግ እንዴት ብሎ ነው ከ70 ፓርቲዎች ጋር በተናጠል መወያየት የሚችለው? አሁን ተቋዋሚ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ለመወያየት የፈለገ የጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ምክር ቤቱ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ያጣራል፤ መፍትሔ እንዲያገኙም ያደርጋል፡፡ ከዚህ ውጪ በተናጠል መወያየት አይቻልም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በራሳቸው የሚፈጠረውን ችግር እንኳ ሣይቀር ኢህአዴግ ፈጠረው ነው የሚሉት፡፡ በአመራር እንኳ የተፈጠረባቸውን ችግር በኢህአዴግ የተፈጠረ ጥፋት አድርገው ይወስዱታል፡፡ ስለዚህ ይሄን መፍረድ ያለበት ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ሁሉንም ነገር ያያል፡፡ ማን ነው ጥፋተኛ? ኢህአዴግ ነው ለዲሞክራሲያዊ ስርአትና ፍትሃዊ ምርጫ ዝግጅ ያልሆነው ወይስ ሌላው? የሚለውን መፍረድ ያለበት ህዝቡ ነው፡፡
ኢህአዴግ የገዢነቱን ኃይል ተጠቅሞ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማፈን ይጥራል የሚሉ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደፓርቲ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
ፓርቲያችን ሰላማዊ ሰልፍ ለዜጎች የተሰጠ ህገ መንግስታዊ መብት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይሄ መብት ተግባራዊ የሚሆንባቸው አሰራሮች እንደሚዘረጉ ህገ መንግስቱም አስቀምጧል፡፡ በህገ መንግስቱ ዜጎች በጋራ ሆነው ቅሬታ የማቅረብ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ የማድረግ መብት አላቸው ይላል፡፡ ይሄን መብት ተግባራዊ ለማድረግ አሰራሮች ሊዘረጉ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች የህዝቡን ሰላም፣ ክብርና የመሳሰሉ መብቶችን መጣስ እንደሌለባቸው ህገ መንግስቱ አስቀምጧል፡፡
አንድ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንደሚጠበቅበትም ተቀምጧል፡፡ የእውቅናውን ጥያቄ የሚያየው አካል የተጠየቀበትን ቦታና ጊዜ ይመለከትና በእውቅና ጥያቄው ላይ ምላሽ ይሰጥበታል፡፡ ቦታ ቀይር ወይም ቀን ቀይር የሚል ምላሽ ይሰጥበታል ማለት ነው፡፡ ዘጠኙ ፓርቲዎች የጠየቁት ቦታ መስቀል አደባባይ ነው፡፡ መስቀል አደባባይ ደግሞ ትልቅ የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገበት ያለ ቦታ ነው፡፡ ለ24 ሰዓት ቆመ ማለት ብዙ ነገር ያስተጓጉላል፡፡ ስለዚህ ቦታው ተገቢ አልነበረም ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የተጠየቀው አካል አልተቀበለውም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ዕቅዳቸው ልማትን ማደናቀፍ፣ ህዝብን ወደ አመፅ መንዳት እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ግን ሰላማዊ ሰልፍ የዜጎች መብት ነው የሚል አቋም አለው፡፡
ኢህአዴግ ለምርጫው ያስቀመጠው ግብ ምንድን ነው? አንዳንድ ወገኖች ሙሉ ለሙሉ አሸናፊ እንዳይሆን ተጠንቅቆ እስከ 15 በመቶ ወንበሮችን ለተቃዋሚዎች ሊለቅ ይችላል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ?
ኢህአዴግ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ወንበር ማግኘት ነው ግቡ፡፡ ይሄ ሲባል ድምፁ እንደ እጩ ቁጥራችንም ይወሰናል በአገሪቱ ባሉ የምርጫ ክልሎች ሁሉ እንወዳደራለን፡፡ በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ለማሸነፍ እንሰራለን ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራሲን የሚያየው በእውነተኛ ገፅታው ነው፡፡ ዲሞክራሲ በአርቴፊሻል ገፅታ መታየት የለበትም፡፡ ዲሞክራሲ የህዝብ ወሳኝነትን ማረጋገጫ መሳሪያ ነው፡፡ በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ተወዳድረን ህዝቡ የሚመርጠን ከሆነ እሰየው ብለን እንወስዳለን፤ ባይመርጠንም እንቀበላለን፡፡ ከዚህ ውጭ አርቴፊሻል በሆነ መንገድ፣ የህዝብን ውሳኔ ባላከበረ መንገድ የተወሰነ ወንበር እንለቃለን የሚል ሃሳብ የለም፡፡ ወሳኙ ህዝብ ነው፡፡ ምርጫ በውጤት አይመዘንም፤ ዋናው ሂደቱ ነው፡፡ ሂደቱ ማማር አለበት፡፡
በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የአለማቀፍ ታዛቢዎች ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ ዘንድሮ የአውሮፓ ህብረትም ቀርቷል፡፡ አለማቀፍ ታዛቢዎች ከምርጫው ለምን ተገለሉ?
 የኛ ምርጫ ማንም ሊታዘበው የሚችል ምርጫ ነው፡፡ በድብቅ የሚካሄድ ምርጫ ሳይሆን ማንም ሊያየው የሚችል ምርጫ ነው፤ ነገር ግን ምርጫን የአውሮፓ ህብረት ካልታዘበው ችግር ይኖርበታል ብሎ ማሰብ በራሱ የምርጫው ወሳኝ ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ ህብረቱ ምርጫውን ለመታዘብ የበጀት እጥረት አለብኝ የመሳሰሉ ምክንያቶችን ነው ያቀረበው፡፡ ስለዚህ ምርጫውን የአፍሪካ ህብረት ይታዘበዋል፣ ከሃገር ውስጥም የተለያዩ የሲቪል ማህበራት ይታዘቡታል፡፡ ዋናው ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ነው ውሳኔ የሚሰጠውም የሚታዘበውም፡፡
አለማቀፍ ታዛቢዎች የምርጫውን ገለልተኛነት ከማረጋገጥ አንጻር ምንም ዓይነት ሚና አይኖራቸውም እያሉን ነው?
 ሊታዘቡ ይችላሉ ግን ዋናው ሚና የህዝብ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሂደት ከህዝብ ጋር የተገናኘ ነው አለማቀፍ ታዛቢ ተጨማሪ ነው፤ ወሳኝነት የለውም፡፡
ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ ሊወዳደረኝ የሚችል ፓርቲ አለ ብሎ ያምናል?
ይሄን ህዝቡ ነው የሚመዝነው፡፡ ቀድመን ባንመዝነው እመርጣለሁ፡፡ ፓርቲዎች ምን እንደሚመስሉ የራሳችን ግምት አለን፡፡ የህዝብን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል ሌላ ይህች አገር የጀመረችውን ልማት፣ ዲሞክራሲ በቁርጠኝነት ይዞ ሊሄድ የሚችል ፓርቲ አለ ብለን አናምንም፡፡ በተለያዩ መንገዶች መመዘን እንችላለን፡፡ ከራሳቸው ባህሪ ተነስተን ማለት ነው፡፡ ፓርቲ ማለት የህዝብን ህይወትና ኑሮ ለመቀየር የሚሰራ ፓርቲ ነው፡፡ የትኛው ፓርቲ ነው ህዝቡ ለልማት ሲንቀሳቀስ ከጎኑ ተሰልፎ የሚሳተፈው? የትኛው ፓርቲ ነው ህዝቡ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙት አብሮ እየተንቀሳቀሰ ያለው? የትኛው ፓርቲ ነው ግልፅ የሆነ ሃገር የሚቀይር አማራጭ ፕሮግራም ያለው? የሚለው ስንጠይቅ፣ ሃገርን በዚህ መንገድ ወደፊት የሚያሻግር ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ ይሄን ግን ህዝቡ ነው ገምግሞ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ያለበት፡፡ አሁን ቅስቀሳ ባልተጀመረበት ሁኔታ በዚህ ጉዳይ ብዙ አስተያየት መስጠት አይቻልም፤ ግን ህዝብ ይታዘባል፡፡ እናሸንፋለን አናሸንፍም የሚለውም ቅስቀሳ ስለሚሆን የምረጡን ቅስቀሳ ሲካሄድ ብናየው የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡
ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ ወይም በምርጫ ሂደቱ ላይ ቅሬታ አለው?
ምርጫ ቦርድ ጋ ቅሬታ የለንም፡፡ ቦርዱ በገለልተኝነት እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡ ስብሰባ ሲጠራን አስተያየት እንሰጣለን፤ እስካሁን ግን ምንም ቅሬታ የለንም፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች የሚያቀርቡትም አብዛኛው ቅሬታ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ ፓርቲዎቹ ራሳቸው መጨረስ ያለባቸውን የቤት ስራ ሳይሰሩ፣ በቦርዱ ላይ የሚያቀርቡትን አብዛኞቹን ቅሬታዎች ስንገመግም፣ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን እንገነዘባለን ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ለኛ የሚያደላልን ነገር የለም፡፡

Read 7351 times