Saturday, 10 January 2015 09:39

የኒዮርክ ሲቲ ፖሊሶች ‘አድማቸውን’ ቀጥለዋል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ለከንቲባው ጀርባቸውን ሰጥተዋል

   ባለፈው ወር መጨረሻ፡፡ አንድ ተሲያት ላይ ከብሮክሊን ሰማይ ስር ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡ የተኩሱን ድምጽ የሰሙት የከተማዋ ፖሊሶች በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ሲያመሩ፣ አስደንጋጭ ትእይንት ገጠማቸው፡፡ ራፋኤል ራሞስ እና ዌንጂን ሊዩ የተባሉ ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በጥይት ተመትተው ደማቸውን እያፈሰሱ ጎዳና ዳር ወድቀዋል፡፡ ተኳሹ ኢስማኤል ብሪንስሊ የተባለ ግለሰብ ነበር፡፡ ሰበቡ ደግሞ ንዴት፡፡ብሪንስሊ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በፈርጉሰን እና በኒውዮርክ ሲቲ በነጭ ፖሊሶች በተገደሉት ሁለት ጥቁሮች ጉዳይ በንዴት ሲብከነከን ሰንብቷል፡፡ ንዴቱንና ቂሙን መርሳት ያልሆነለት ይሄው ግለሰብ ታዲያ፣ በገና ዋዜማ ጠመንጃውን አንስቶ ወደ ብሮክሊን ለበቀል ተንደረደረ፡፡ በሁለት ፖሊሶች ላይ አነጣጠረ፡፡ ጥይት ቆጠረ፡፡ በስተመጨረሻም በገዛ ጠበንጃው ራሱን አጠፋ፡፡
በግለሰቡ ድርጊትና መንግስት ተገቢውን ፍትህ ለመስጠት አልቻለም በሚል ክፉኛ የተበሳጩት በርካታ የኒውዮርክ ሲቲ ፖሊሶችም ታዲያ፣ ነግ በእኔ ብለው ተቃውሟቸውን በግልጽ አሰምተዋል፡፡ ላለፉት ሁለት ሳምንታት መደበኛ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን መተዋቸውንም ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡ፖሊሶቹ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ማቆማቸውን ተከትሎ በከተማዋ ያለው የወንጀል ቁጥር መላላቱ ተነግሯል፡፡ ወንጀለኞችን በአግባቡ በቁጥጥር ስር በማዋል ከህገወጦች በቅጣት መልክ ሊሰበሰብ የሚገባው ገንዘብ እየተሰበሰበ አይደለም፡፡ ዘ ታይምስ እንዳለው፤ የከተማዋ ፖሊሶች ወንጀለኞችን በአግባቡ በቁጥጥር ውስጥ ለማዋል ተግተው ባለመስራታቸው የወንጀል ክሶች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል፡፡ በቁጥጥር ውስጥ የሚውሉ ወንጀለኞች ቁጥር 66 በመቶ ያህል ቀንሷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ፖሊስ የተያዙ የወንጀል ክሶች 347 ብቻ መሆኑንና፣ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ይህ ቁጥር ከ4 ሺህ በላይ እንደነበር ዘ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ቀረጥና ፓርኪንግን ከመሳሰሉ ነገሮች የሚገኘው የመንግስት ገቢም፣ ስራ በፈቱ ፖሊሶች ሳቢያ በአግባቡ ሊሰበሰብ ባለመቻሉ ከ90 በመቶ በላይ ቀንሷል፡፡ ይህም በከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡የፖሊስ አባላት ስራ መፍታታቸው ምንም እንኳን በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በማበራከት ረገድ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ ባይፈጥርም፣ በአንድ አካባቢ የዝርፊያ ድርጊቶች ከወትሮው በተለየ ከፍ ማለታቸውን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያሳያል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከበረው የፈረንጆች የገና በዓል ዋዜማ ላይ በተከናወነው የሟቹ የስራ ባልደረባቸውን ዌንጃን ሊዩን የቀብር ስነስርዓት ላይ የተገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች የከተማዋ ከንቲባ ቢል ዲ ባላሲዮ ወደ መድረክ ወጥተው የሃዘን መግለጫቸውን ሲያስተላልፉ ጀርባቸውን ሰጥተዋቸው ነበር - ተገቢውን ምላሽ አልሰጡንም በሚል፡፡
የከተማዋ የፖሊስ ኮሚሽነር ቢል ብራተን ባልደረቦቻቸው በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ተቃውሞ እንዳያሰሙ አበክረው ቢያስጠነቅቁም፣ ፖሊሶቹ ግን ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው ተቃውሟቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡የፖሊስ አባላቱን አቋም በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ ለመብታቸው መከበር በጽናት መቆማቸውን ያደነቁ መኖራቸውን ያህል፣ በወጉ ከመንግስት ጋር ተወያይተው መፍትሄ መሻት ሲገባቸው ስራ መፍታታቸውን ክፉኛ የተቹም ብዙዎች ናቸው፡፡
 ይህ ድርጊት ያናደዳቸውና የፖሊሶች እምቢ ባይነት ያበሳጫቸው የከተማዋ ከንቲባም ታዲያ የፖሊስ አባላቱ በዚሁ ድርጊታቸው የሚገፉና የዕለት ተዕለት ስራቸውን በአግባቡ የማያከናውኑ ከሆነ፣ ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ ተቆጥሮ በሌሎች እንደሚተኩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል፡፡


Read 3379 times