Saturday, 10 January 2015 09:48

የዋጋ ንረቱ ባለፈው ወር ጭማሪ አሳይቷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የወጪ ንግዱ ባለፉት አምስት ወራት መሻሻል እንዳሳየ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት በህዳር ወር ከነበረበት 5.9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት፣ በታህሳስ ወር ወደ 7.1 በመቶ ማደጉን ትናንት አስታወቀ፡፡ የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ባለፉት አምስት ወራት በ10.7 በመቶ እድገት ማሳየቱን ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ሮይተርስ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የዋጋ ንረቱ ጭማሪ ሊያሳይ የቻለው በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ ሲሆን ስኳር፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ በህዳር ወር ከነበረበት 4.8 በመቶ፣ በታህሳስ ወር ወደ 6.5 በመቶ ከፍ እንዳለ አስታውቋል፡፡
ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ላይም በተመሳሳይ ወቅት ከ7.1 ወደ 7.8 በመቶ ጭማሪ መታየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአመቱ የአገሪቱ የዋጋ ንረት 9.1 ደርሶ እንደነበር አስታውሶ፣ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲቀንስ እንደቆየ ገልጿል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አማከለ ይማም በበኩላቸው፤ አገሪቱ ባለፉት አምስት ወራት ለወጪ ንግድ ካቀረበቻቸው የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የማዕድን ምርቶች 1.16 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ለአናዶሉ ኤጀንሲ ገልጸዋል፡፡
ለወጪ ንግዱ ገቢ መሻሻል አስተዋጽዖ ካበረከቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል የቡና ምርት በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ የገለጸው ዘገባው፣ አገሪቱ በተጠቀሰው ጊዜ 62 ሺህ 560 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዳ፣ ከእቅዱ በላይ 64 ሺህ 228 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ ማቅረቧን ጠቁሟል፡፡

Read 2226 times