Saturday, 10 January 2015 09:53

ምርጫ ቦርድና ሁለቱ ፓርቲዎች ተፋጥጠዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

•    ለአንድነትና መኢአድ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ሰኞ ይጠናቀቃል
•    ፓርቲዎቹ ምንም የፈፀምነው የህግ ጥሰት የለም ብለዋል
•    “አንድነት” ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ልወስደው እችላለሁ አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ አንድነትና መኢአድ ፈፅመዋል ያለውን የህግ ጥሰት እንዲያስተካክሉ የሰጠው የመጨረሻ እድል ከነገ ወዲያ ሰኞ የሚጠናቀቅ ሲሆን ፓርቲዎቹ የፈፀምነው የህግ ጥሰት ስለሌለ የምናስተካክለው ጉዳይ የለም ብለዋል፡፡
ቦርዱ ማክሰኞ እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች ከአመራር ለውጥ ጋር በተያያዘ የራሣቸውን የውስጠ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ መጣሳቸውን ጠቅሶ፣ የፈፀሙትን የህግ ጥሠት አስተካክለው ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ እንዲገቡም ያሳሰበ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ቦርዱ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና ገልፀዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ በበኩላቸው፤ ምርጫ ቦርድ እየፈፀመብን ነው ያሉትን ጉዳዮች ለጠቅላላ ጉባኤ አባሎቻቸው ለማስረዳት ለነገ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ እነ አቶ ማሙሸት አማረን መርጧል የተባለው መኢአድ ፈጽሟል ያሉትን የህግ ጥሰት በዝርዝር ያቀረቡት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ የፓርቲው ደንብ ፕሬዚዳንቱ በማዕከላዊ ም/ቤት አቅራቢነት በጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመረጥ ቢጠቁምም አሁን ያሉት አመራሮች ደንቡን በጣሰ ሁኔታ መመረጣቸውን ቦርዱ አረጋግጧል ብለዋል፡፡
ሌላው በቦርዱ የተጠቀሰው የህግ ጥሰት፣ የአባልነት መዋጮ ከ3 አመት በላይ አቋርጠው ከፓርቲው የተሰረዙ ግለሰቦች ወደ አመራር መጥተዋል የሚል ሲሆን በፓርቲው ደንብ መሠረት አባልነቱን ያቋረጠ መልሶ አባል በመሆን ወደ አመራር ለመምጣት 6 ወር መጠበቅ እንደሚገባው ቦርዱ ጠቁሟል፡፡ የእነ አቶ ማሙሸት አመራር ሲመረጥ የቦርዱ ታዛቢዎች እንዳይገኙ ተደርጓል ያሉት ፕ/ር መርጋ፤ ጠቅላላ ጉባኤው ይካሄድበታል የተባለውን ቀን በመቀየር ቦርዱ በማያውቀው ቀን መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ በጊዜው ተካሄደ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ህግን ያላከበረ መሆኑን በመግለጽ እንዲስተካከል ቦርዱ ማዘዙን፣ ነገር ግን የተስተካከለ ነገር አለመኖሩን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ የተጠራው ጠቅላላ ጉባኤም በሚመለከተው አካል የተጠራ አለመሆኑን ቦርዱ አጣርቻለሁ ብሏል - መጠራት የነበረበት በማዕከላዊ ም/ቤቱ እንደነበር በማስረዳት፡፡
በሌላ በኩል በ2003 ዓ.ም በተካሄደ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጫለሁ የሚሉት አቶ አበባው መሃሪ፤ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የህግ ጉዳዮችን አሟላለሁ እያሉ ከቦርዱ ጋር ሲነጋገሩ እንደቆዩ የጠቆሙት ፕ/ር መርጋ፤ ሂደቱ በዚህ እያለ ከደንብ ውጭ አዲስ አመራር መመረጡን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የእነ አቶ ማሙሸት አመራር አመጣጡ ትክክል አለመሆኑ ሳያንስ የደረሠበትን ሪፖርት በህጋዊ ማህተም አረጋግጦ ለቦርዱ ማቅረብ አልቻለም ብለዋል - የቦርዱ ሰብሳቢ፡፡
ምርጫ ቦርድ በፓርቲው ተፈፅመዋል ብሎ የዘረዘራቸውንና በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ያላቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ  ጥያቄ የቀረበላቸው የመኢአድ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፤ ቦርዱ የዘረዘራቸው የደንብ ጥሰቶች  በሙሉ ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ጠቁመው ምንም የሚስተካከል ነገር የለም ብለዋል፡፡ ቦርዱ የጠቀሳቸው ጉዳዮችም እሱን ጨርሶ የሚመለከቱት  አይደሉም ብለዋል - አቶ ማሙሸት፡፡
ቦርዱ የአባልነት መዋጮ ያልከፈሉ በመሆናቸው ከአባልነት ተሰርዘዋል ያለውን በተመለከተም ሲመልሱ፤ መተዳደሪያ ደንባቸው አንድ አባል ያለበቂ ምክንያት ከ3 ጊዜ በላይ መዋጮ ያላዋጣ እንደሆነ ይሠረዛል እንደሚል አቶ ማሙሸት ጠቁመው፣ “እኛ ከ3 አመት በላይ ያልከፈልንበት በቂ ምክንያት አለን፤ በወቅቱ በፓርቲው ጉዳይ በፍ/ቤት ታግደን ክርክር ላይ ነበርን” ብለዋል፡፡ ስለዚህ መዋጮ ላለመክፈላችን በቂ ምክንያት ነበረን ይላሉ፡፡ የመኢአድ  የመጨረሻ ውሳኔ ሠጪ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ማሙሸት፤ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሣኔ ቦርዱም ሆነ የመኢአድ አባላት የመሻር ስልጣን የላቸውም ሲሉ ሞግተዋል፡፡ የቦርዱ ኃላፊነት ስብሰባው በትክክል ኮረም ሞልቶ ተካሂዷል አልተካሄደም የሚለውን ማረጋገጥና ምርጫው ዲሞክራሲያዊ መሆኑን መገምገም እንጂ በጉባኤው ውሣኔ ጣልቃ መግባት አይችልም ብለዋል - አቶ ማሙሸት፡፡
የጠቅላላ ጉባኤውን ቀን በመቀየር የቦርዱ ተወካዮች እንዳይገኙ ተደርጓል ለሚለው የቦርዱ ነጥብ ምላሽ የሠጡት አቶ ማሙሸት፤ “ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም ፓርቲው ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሁለት የቦርዱ ተወካዮች መገኘታቸውንና በእለቱ ጉባኤው ባለመጠናቀቁ በማግስቱ እንደሚገኙ ቃል ገብተው ከሄዱ በኋላ ጠዋት ሲደወልላቸው፣ የፓርቲው ጉባኤ ሂደት ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ናዝሬት ለስልጠና የተላክን ስለሆነ መምጣት አልቻልንም ብለውናል” ይላሉ - አቶ ማሙሸት፡፡ አክለውም የቦርዱ ተወካዮች የጠቅላላ ጉባኤውን ሪፖርት አቅርቡልን ማለታቸውን ጠቅሰው የአመራሩን ምርጫ በሃላፊነት መከታተል የነበረበት ቦርዱ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ማሙሸት ቦርዱ አልቀረበልኝም ያለው የጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ለምን በወቅቱ እንዳልቀረበ ሲያስረዱ፤ ከስልጣን ፉክክሩ ደብዳቤ ፅፈው ራሣቸውን ያገለሉት አቶ አበባው መሃሪ ማህተሙን በመውሰዳቸው ነው ይላሉ፡፡ ፓርቲው የማህተሙን ጉዳይ ለቦርዱ ማመልከቱን ጠቁመው ቦርዱም ለፖሊስ አመልክቱ እንዳላቸውና  ለፖሊስ ማመልከታቸውን፣ ከ40 ቀን በኋላም ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ማህተም አስቀርፀው ለቦርዱ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ ምክንያቱን ሣይገልጽ አልቀበልም ማለቱን አቶ ማሙሸት ተናግረዋል፡፡ በኋላም ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም የቦርዱ አመራሮች በሚዲያ፣ መኢአድ በአስቸኳይ የውስጥ ችግሩን ያስተካክል የሚል መግለጫ ሠጠ ብለዋል - አቶ ማሙሸት፡፡
ቦርዱ የፓርቲው ወሳኝ አካል በሆነው ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠን አመራር አልቀበልም የሚልበት ምንም ህጋዊ መሠረት የለውም ያሉት አቶ ማሙሸት፤ “በኛ በኩል ምንም የህግ ጥሰት እንዳልተፈፀመ ለአባሎቻችን እየገለፅን ቦርዱ ምን እየሠራ እንደሆነ እያሣወቅን ነው፤ የቦርዱ አካሄድም ፖለቲካዊ ውሣኔ ያለበት ነው ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡ አመራሩ በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጠ መሆኑንና የህግ ጥሰት እንደሌለ ለማሳየትም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ለነገ መጠራታቸውን የጠቆሙት አቶ ማሙሸት፤ በእለቱ ምንም አይነት የአመራር ምርጫ እንደማይካሄድ ነገር ግን የቦርዱ ተወካዮች ባሉበት ቦርዱ በፓርቲው ላይ እየፈፀመ ያለው ተግባር ለአባላቱ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ቦርዱ ያሻውን መወሰን ይችላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ቦርዱ የህግ ጥሰት ፈፅሟል ያለው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሲሆን በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አሁን ያሉት ፕሬዚዳንት በጠቅላላ ጉባኤው መመረጥ ሲገባቸው በብሔራዊ ም/ቤት እንዲመረጡ መደረጉ ስህተት ነው ብሏል፡፡ “የፓርቲው ፕሬዚዳንት በሚስጥር ድምፅ ይመረጣል፤ በውድድር ላይም የተመሠረተ ይሆናል” የሚለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መጣሱንም የቦርዱ አመራሮች ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው እነዚህን የህግ ጥሰቶች እስከ ጥር 4 አስተካክሎ ይቅረብ በሚለው የቦርዱ ውሳኔ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሠጡት የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አስራት አብርሃም፤ ፓርቲያቸው “ከፀሐይ በታች” የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን ገልፀው፣ በቀጣይ የኛ ተግባር የሚሆነው የቦርዱን ውሣኔ መጠበቅና ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች ማስኬድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ “ምርጫ ቦርድ አንድነትን የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው” ያሉት አቶ አስራት፤ “በዚህ አጋጣሚ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዳልሆነ አጋልጠናል፤ የኢህአዴግ 5ኛው ግንባር እንደሆነም አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ሃሙስ እለት ተሰብስቦ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ለነገ በአስቸኳይ እንዲሰበሰቡ ጠርቷል፡፡ በትናንትናው እለት ፓርቲው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ቦርዱ በአንድነት ላይ ያልተገባ ውሣኔ የሚወስን ከሆነ ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ሊወስደው እንደሚችል አስታውቋል፡፡
ከሁለቱም ፓርቲዎች አባላት የቀረቡለትን የህግ ጥሰት አቤቱታ መነሻ አድርጐ፣ ህገ ደንባቸውን በመመርመር ተፈጽመዋል ያላቸውን የህግ ጥሰቶች እንዲያስተካክሉ እስከ ተነገ ወዲያ ሰኞ የመጨረሻ እድል መስጠቱን ያመለከተው ቦርዱ በበኩሉ፤ ፓርቲዎቹ የተጠየቁትን በህገደንባቸው መሰረት አስተካክለው ካልቀረቡ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡    

Read 3709 times