Wednesday, 14 January 2015 09:15

ትመጣለች ብዬ

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(40 votes)

ትመጣለች ብዬ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ
የልጅነት ዓይኔ ሟሟ እንደበረዶ፡፡
ትመጣለች ብዬ እየጠበቅሁ ነው፡፡ የሷ መምጣት ግን ከኢየሱስ መምጣትም በላይ ዘገየ፡፡ እሷን የማይበት ቀን እንደ ምፅአት ቀን ራቀኝ፡፡ ስትሄድ ቃል ገብታልኝ ነው፡፡ ፈፅሞ ላትረሳኝ ምላ፡፡ እንደምትወስደኝ ተገዝታ፡፡ ቢያንስ ቶሎ መጥታ እንደምንገናኝ ቃል ገብታልኝ ነው፡፡ ዲቪ ደረሳትና የሚፈለግባትን አጠናቃ ወደ አሜሪካ አቀናች፡፡ መልካም የሚባል ጊዜ አብረን አሳልፈናል፤ እንደ ከርቤ አፍንጫ የሚያውድ፣ እንደ ናና ከረሜላ ለአፍ የሚጣፍጥ፣ እንደ ቤትሆቨን የሙዚቃ ቅንብር ጆሮ የሚያሰምጥ፤ እንደ አደይ አበባ ለዓይን የሚማርክ፤ እንደ መልካም መዝሙር ልብ የሚያስመልክ … ጊዜ!... የእስራኤል ገናንነትን እንደሚመኝ፣ የኢየሩሳሌምን ማክተም እንደሚፈልግና “ብረሳሽ ቀኜ ይርሳኝ!” እንደሚለው አይሁድ፣ እኔም ስምዋን እየጠራሁ እንደዛው እምላለሁ፡፡ ያጋጣሚ ነገር ሆኖ ስምዋ ኢየሩሳሌም ነው፡፡ እና ዘወትር እንዲህ እላለሁ፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ብከዳሽ ቀኜ ትክዳኝ!” በሄደች በስድስተኛ ወርዋ ደብዳቤ ፃፈችልኝ፡፡ እንዲህ የሚል፡- “እዮብዬ እንዴት ነህልኝ? እኔ ካንተ ሀሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣም ደህና ነኝ፡፡

ስራ ጀምሬያለሁ፡፡ ይሄ ሀገር እንደ ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ዶላር ውድ ነው፡፡ ዶላር የምታገኘው ላብህን አንጠባትበህ ነው፡፡ ቢሆንም ለክፉ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ  ለመስራት ብትፈልግ እንኳ የምትሰራው ስራ አታገኝም፡፡ ወይም ገቢህ ትንሽ ይሆናል፡፡ እዚህ ግን ሰርቶ መኖር ይቻላል፡፡  ስራ መምረጥ እኛ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን የሚመጥን አይደለም፡፡ ለዚያ ማዕረግ ለመብቃት ብዙ ይቀረናል፡፡ ስለዚህ ያገኘነውን ስራ ነው የምንሰራው፡፡ የመብራት፣ የውሃ የምን የምን ቢል ስለሚመጣብህ እንደ ኢትዮጵያ ተኝተህ ማደር አትችልም፡፡እንደምንም ተፍ ተፍ ማለት አለብህ፡፡ ያለበለዚያ መኖር አይቻልም፡፡ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው የኛ የኢትዮጵያውያን ኑሮ አብዝቶ ይገርመኛል፡፡ በኢትዮጵያ እንደ ሌላው ላይ እንደ አነባበሮ ተነባብሮ ነው የሚኖረው፡፡ እዚህ አስራ ስምንት ዓመት ከሞላህ ራስህን መቻል ግዴታ ነው፡፡ ከወላጆችህ ቤት ወጥተህ ወደ ራስህ ቤት፤ ከጥገኝነት ተላቀህ ወደ ወንደላጤነት መቀየርህ የሚጠበቅና የሚከወን እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው እስከ ሰላሳና አርባ ደርሶ ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩ አሉ፡፡ እዚህ ይሄ አይታሰብም፡፡ (የሚታሰብ አይደለም)፡፡ በተረፈ አሜሪካ ለትጉሃን የአፖርቹኒቲ - የዕድል አገር ናት፡፡ ከለፋህ ከደከምክ፤ ከጠራክ ከጋርክ ስኬታማ ልትሆን ትችላለህ፡፡
እዚህ ከመጣሁ በኋላ በጣም የከበደኝ ነገር ቢኖር ያንተ ናፍቆት ነው፡፡ በጣም ትናፍቀኛለች፡፡
በጣም ትናፍቀኛለህ፡፡ እጅግ በጣም ትናፍቀኛለህ፡፡ አብረን ያሳለፍነውን ጊዜ ሁሌም ስዘክረው እኖራለሁ፡፡
ያደረግናቸው ነገሮች አንድ በአንድ ትዝ ሲሉኝ ደስታ ውስጤ እንደ ችቦ ይለኮሳል፡፡ የትውስታ ማህደሬ የተሞላው ባንተ ነው፡፡ ቤተሰቦቼን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡ አዲስ አበባን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡
ኢትዮጵያን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡ በሰላም እንድትቆይልኝ የሰርክ ፀሎቴ ነው፡፡ ተመቻችቶልኝ እስክወስድህ ድረስ ስናፍቅ እኖራለሁ፡፡ ያንተው ኢየሩስወይም አንተ እንደምትጠራኝ ያንተው ጄሪ!
እወድሃለሁ!
ቻዎ!”
እኔም መልሼ ፃፍኩላት፡፡ የኔ ደብዳቤ ይህን ይመስል ነበር፡፡ “ጄሪዬ እንዴት ነሽልኝ?!.... እኔ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደህና ነኝ፡፡ አንቺ ከሄድሽ ወዲህ ጭር ብሎብኛል፡፡ ታምኚኛለሽ? … አዲስ አበባ ጭር አለችብኝ፡፡ ለካ ያንቺ መኖር ነበር ሙቀት የሚሰጣት፡፡ ለካ አንቺ ነበርሽ ጨለማዋን የምትገፊ፣ ዕለቱን በብርሃን የምታደምቂ ፀሐይዋ!
አንቺ ከሄድሽ ወዲህ … በኔ በኩል … ሁሉ ጨለማ ነው፡፡ የደስታ ጣዕም እንደትነት እንኳን ተስቶኛል፡፡  ከደስታ ጋር ተረሳስተናል፡፡ ከሳቅ ጋር ተፋተናል፡፡ ሳቅ ከልቤ ፈልቆ ጥርሴ ላይ የሚታየው ያሳለፍነውን ጊዜ ሳስብ ነው፡፡
አቅፌሽ     ወክ ሳደርግ!
አቅፌሽ ስተኛ!
አቅፌሽ ስውል!
አቅፌሽ ሳድር!
ፀሀዬ ነበርሽ ሙቀት የምትሰጪኝ! ጨረቃዬ ነበርሽ የምሽትን ድንግግዝ ጨለማ ገፈሽ ምሽቴን የምታደምቂ! አንቺ ከተለየሽኝ በኋላ ብዙ ነበር ጎድሎብኛል፡፡ ጉድለቱ ስትመጪ ይሞላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተረፈ እንደዚያው እንደ ድሮው ነኝ፤ ኪሎ ወይም ቁመት አልጨመርኩም፡፡ ልቤም ባንቺ ንግስትነት እምነቱ እንደፀና ነው፡፡ ሁሌ እንዲህ እዘምራለሁ፡፡
አንቺ እዛ ማዶ እኔ እዚህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ
እወድሻለሁ!
ቻዎ!
በሄደች በአስር ወርዋ ደግሞ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፈችልኝ፡፡ “ውዴ እንዴት ነህልኝ?! … ኑሮ እንዴት ይዞኻል?! እኛ ጋ ኑሮ አድካሚም አስደሳችም ነው፡፡ ኑሮአችን የላብም፣ የላቭም ድቅል (ዲቃላ) እውነት ነው፡፡ ስራ ላይ የምታፈሰው ላብ አለ፡፡ በህይወት ድንገት የሚያጋጥምህ ላቭም አለ፡፡ እንደ አበበ ቢቂላ የዞረበት መልስ አንሰጥም፡፡ ታሪኩን ሰምተሃል?! አበበ ቢቂላ በሮም ውድድር ላይ ብቻውን ወደ ስቴዲየሙ ገባ፡፡ ውድድሩንም አንደኛ በመሆን አሸነፈ፡፡ በጉብዝናው የተደነቀች አንዲት ነጭ ሴት ወደ አቤ ቀረብ ብላ እንዲህ አለች፤
“አይ ላቭ ዩ!”
አበበ መልስ ለመስጠት አላመነታም፡፡ “የላቡን ነገርማ ተይው” አላት ይባላል፡፡ ለማንኛውም እኔ ደህና ነኝ፡፡ በቅርቡ ትምህርት ለመጀመርም እያሰብኩ ነው፡፡ አሜሪካ ከጉልበት ስራ መገላገያ ብቸኛው መንገድ መማር ነው፡፡ ተምሬ የተሻለ ስራ የመስራት ራዕይ አለኝ፡፡ አሁነ ባለው ሁኔታ እየሰራሁ መማር የምችል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ትምህርቴን መጀመሬ አይቀርም፡፡ ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ፡፡
እወድሃለሁ!
ቻዎ!
እኔም እንዲህ የሚል መልስ ፃፍኩላት፡፡ “ጄሪዬ ነፍሴ … እንዴት ነሽልኝ?! … እኔ በጣም ደህና ነኝ፡፡ ፃፍሽልኝን ደብዳቤ አነበብኩ፡፡ ሀሳብሽ ጥሩ ነው፡፡ መማርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ እንዳልሽው ጠንከር ብለሽ በፅናት መማር አለብሽ፡፡ ትምህርት የዕውቀት መሰላል ነው፡፡ እዛ መሰላል ላይ የሚወጡት የታደሉት ናቸው፡
የተማረ ሰው ከመሰላሉ ጫፍ ላይ ሆኖ ቁልቁል ያያል፡፡ የሰው ልጅ አጥቶ የሚቸገረው ቁልቁል

ማየትን ነው፡፡
ሁሉም የሚያየው ሽቅብ ነው፤ ወደ ላይ! …
ወደ ላይ በማየት ግን የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ለረጅም ጊዜ ለማጎንበስና አጎንብሶ ለመቆፈር የደፈሩት ናቸው ቀና ብለው መሄድ የሚችሉት፡፡ የቆሸሹ እጆች ባለቤት መሆን በስኬት አሳንሰር ላይ ለመሳፈር ወሳኝ ነው፡፡
እና አንቺም በትጋትሽ     ቀጥይ! … በርቺ….ጄሪዬ ብታውቂው ደስ የሚለኝ፣ ብደብቅሽ መደበቁ አግባብ የማይመስለኝ አንድ እውነት አለ፡፡ እሱም ከምንም ከምንም በላይ አንቺን ለማየትና ለማግኘት መጓጓቴ ነው፡፡ በጣም ናፍቀሽኛል፡፡ ሁሌም በህልሜ አይሻለሁ፡፡ ከአጠገቤ ብትሆኚ፣ ከጎኔ ብትቆሚ እደሰታለሁ፡፡ እውነታውን እያወቅሁ እውነታውን ለመካድ ይዳዳኛል አንዳንዴ!
መሀላችን አትላንቲክ ውቅያኖስ ተዘርግቷል፡፡ ስለዚህ መገናኘታችን በዋዛ የሚሆን አይደለም፡፡ አንቺን ወደኔ ለማምጣት፤ ወይም እኔን ወዳንቺ ለመውሰድ እግዜር ቢተባበረን ምን አለ? እላለሁ ብዙ ጊዜ፡፡
ለማንናውም አብዝቼ እንደምወድሽ አትርሺ!
ቻዎ!
… ጄሪ ከዚያ ደብዳቤ በኋላ ሌላ ደብዳቤ አልፃፈችልኝም፡፡ ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ስራ በዝቶባት ይሆን? ወይስ ትምህርት አጨናንቋት?! እርግጡን እንኳን እኔ አዋቂ የሚባሉት ጠንቋይ እንኳን አያውቁም፡፡ አሜሪካ ከሄደች ዓመታት አለፏት፡፡ ደብዳቤ ከፃፈችልኝም አራተኛ ወርዋ ሆነ፡፡ ምን ነካት? ስል አሰብኩ፡፡
ጊዜው በረዘመ ቁጥር ደህንነትዋ ሁሉ ያሳስበኝ ጀመረ፡፡ አንዱ ጥቁር  ወንበዴ ሽጉግጥ ተኩሶባት አቁስሏት ወይም ገድሏት ይሆን? ስል ተጨነቅኩ፡፡ ጠብቄ ጠብቄ ሌላ ደብዳቤ አልመጣ ሲል እኔ ፃፍኩላት፡፡ እንነዲህ ብዬ፡- “ ጄሪዬ፤ በጤና አለሽን?
… በጤናሽ ከሆንሽ ለእኔ ይሄ ብቻ በቂዬ ነው፡፡ ደብዳቤሽ መጥፋቱ (መቆሙ) ግን ብዙ ነገር አሳስቦኝ… በጤናሽ አይሆንም ብዬ ገመትኩ፡፡ የታመምሽ ወይም የሞትሽ መሰለኝ፡፡ ይሄ ጥርጣሬዬ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ፈጣሪዬን ለመንኩት፡፡ ግን ምን ሆነሽ ነው?!... ይሄ ደብዳቤ ከደረሰሽ፤ እንደደረሰሽ በአስቸኳይ መልስ ጻፊልኝ፡፡
የሚያርፍብሽ ዝንብ ራሱ እሽሽ እንዲባል አልፈልግም፡፡ እንድትጎጂ፤ እንድትታመሚ ወይም እንድትሞቺ አልፈልግም፡፡ እነዚህን ሁሉ ለጠላቶችሽ እመኛለሁ፡፡ አንቺ የኔ ቀዘባ ግን ሙሉ ጤንነትና ሰላም እንዲኖርሽ እመኛለሁ፡፡ (እወድሻለሁ) …
ለማንኛውም እንደምወድሽ ለሰከንድ እንኳን እንዳትረሺ!
ያንቺው አፍቃሪ ነኝ … ከአዲስ አበባ!”
የኔና የኢየሩስ ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ ብዙዎች በመገረም ያወሩታል፡፡ ጥቂቶች ግራ በመጋባት ያሙታል፡፡
የሚቀናብን ነበርን፡፡ ጥምረታችን እንደ እውነት የሰመረ፤ ተግባቦታችን እንደ ከዋክብት ያማረ፣ ፍቅራችን እንደ ጅማት የከረረ ነበር፡፡ ምና ያደርጋል በመጨረሻ ስደት መሀላችን ሰርጎ ገባ፡፡ ፍቅራችንን መገላለፅና ፍቅራችንን መኖር የምንችለው በደብዳቤ ልውውጥ ብቻ ሆነ፡፡ በያን ደብዳቤ ከፃፍኩላትም በኋላ ኢየሩስ መልስ ሳትፅፍልኝ ቀረች፡፡ ከብዙ ወራት በኋላ ግን አንድ ኢንቨሎፕ እጄ ገባ፡፡ ከፍቼ አነበብኩት፡፡ ፀሀፊዋእየሩሳሌሜ ናት፡፡ ደብዳቤ አፃፃፍዋና ቃላት አጠቃቀምዋ ከወትሮው ለየት አለብኝ፡፡     የፃፈችው እንዲህ ለማለት ነበር፤
“ኢዮብ እንዴት ነህ?” (ይህን አረፍተ ነገር ሳነብ ተራው ነገር እንደትልቅ ነገር ሆዴን አሳመመኝ፡፡ “ዬ” ጠፍታለች፡፡ እና ተከፋሁ፤ የ“ዬ” ከኢዮብ ቀጥሎ አለመግባት አንዳች ነገር ነገረኝ፡፡ ነገሩን በሆዴ ይዤ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡)“…. እኔ ደህና ነኝ፡፡ ያልፃፍኩልህ ስላልተመቸኝ ነው፡፡
እንደውም ቀደም አድርጌ ላሳውቅህ ይገባ የነበረ ነገር ሳልነግርህ ዘገየ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ደብዳቤ የመጨረሻዬ ነው፡፡ አንተም ባለፈው የፃፍከውን ደብዳቤ የመጨረሻህ አድርገው፡፡ ኢዮብ ህይወት አጋጣሚ ናት፡፡ ድንገት በገጠመህ ነገር ተወስነህ ትኖራለህ፡፡ ስለዚህ እኔም አንድ አጋጣሚ ገጥሞኛል፡፡ አንድ የምቀራረበው ሰው ነበረ፡፡ ተግባባን፡፡ እና ቸኩሎ ካልተጋባን (ወይም  ካላገባሁሽ) አለኝ፡፡ ጓደኛ
እንዳለኝ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ ሊረዳኝ ግን አልቻለም፡፡ ስለወደደኝ ብቻ ሊያገባኝ ፈለገ፡፡ አንተ በፍቅርህ ፀንተህ በመታመን እንደምትጠብቀኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ፣ እንጋባ ስልህ የምትሰጠኝ መልስም ቀዝቀዛ ስለነበር እሺ አልኩት፡፡ እና ተጋባን፡፡ ከተጋባን አሁን እነሆ ስድስተኛ ወራችን! … አንድ ነገር እመክርሃለሁ፡፡ በተስፋ እየጠበከኝ ከነበረ በሆነው ነገር አትፀፀት፡፡ ኢዮብ እኔ የምመክርህ ቶሎ ብለህ የራስህን ህይወት መኖር እንድትጀምር ነው፡፡ ቢጤህን ፈልገህ አግባ፡፡ ስለኔ ግን ፈፅሞ እንዳታስብ፤ ይህ በመካከላችን እየተካሄደ ያለው የደብዳቤ ልውውጥ የመጨረሻ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ለትዳሬ ጥሩ አይደለም፡፡ በተረፈ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥምህ እመኛለሁ፡፡
ቻዎ!
ገረመኝ፡፡ ደነቀኝ፡፡
(ተደመምኩ፡፡)…
ፍቅርና ተረት አንድ ሆኑ ማለት ነው?!
ተረት ሲሰሙት ደስ ይላል፡፡
ፍቅርም ሲኖሩት ደስ ይላል፡፡
ተረት ከረሱት ይረሳል፤ ፍቅርም ከተዉት ይተዋል ማለት ነው?!
ነው ወይስ መራራቅ ለመለያየት ምክንያት ይሆናል?! …
ይሆናል እንግዲህ፤ ይሆን ይሆናል፡፡
ጄሪ ትክደኛለች ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ አንዳች ነገር ልቤን እንደ ድመት ሲቧጭረው ይሰማኛል፡፡
ነፍሴ የእሾህ አክሊል ደፍታለች፡፡ የሀዘን ማቅ ለብሳለች፡፡ የማይላክ ደብዳቤ ለጄሪ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ‹ደብዳቤዬን የምጀምረው አለማመኑን በመግለፅ ነው፡፡ የማላምነው በእግዜር አይደለም፡፡
የማላምነው ወይም ያላመንኩት ያነበብኩትን ነገር ነው፡፡
እውነቱን ልናገርና  ከዓይኔ ይሆን ብዬ ተጠራጥሬያለሁ፡፡
የደብዳቤው ማዕከላዊ መልዕክት ግን ግልፅ ነበር፡፡ ቁም ነገሩ ካንቺ ከፍቅረኛዬ ጋር መለያየቴን የሚያረዳ ነው፡፡ ማመን አቃተኝ፡፡ ጄሪ ፍቅራችን ይህን ያህል በቀላሉ የሚፈርስ፤ ማገሩ በማይረባ ልጥ የታሰረ ነገር ነበር ማለት ነው?! ገርሞኝ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ በሄድሽ በሁለተኛ ዓመትሽ ሌላ ሰው ማግባትሽን ነገርሽኝ! … ከዛ በፊት በፍቅር ያሳለፍናቸው ሶስት ዓመታት ሚዛን ሊደፉ አልቻሉም ማለት ነው?!ቢገርመኝ ነው ይህን መጠየቄ፡፡ ለማንኛውም አንቺ የራስሽን ህይወት መኖር ጀምረሻል፡፡ እኔም የራሴን ህይወት መጀመር እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ትመጫለሽ ብዬ ለብዙ ጊዜ በጉጉትና በናፍቆት ጠብቄ ነበር፡፡ መምጣትሽ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ መጥተሽ ወይም ወስደሽኝ አብረን እንኖራለን የሚል ምኞት ነበረኝ፡፡ አልሆነም፡፡ ምኞቴ ለፀሐይ
እንደተሰጣ ገብስ አደባባይ ላይ ተበተነ፡፡ ከኔ መለየትሽ እውነት መሆኑን ሳረጋግጥ ፍቅርሽ ከልቤ
ይወጣ እንደሁ ብዬ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ፤ ላንቺ ያለኝ ስሜት ከቁብ እንደማይገባ ሁሉ፤

እንዲህ ስል በስነ ቃል ተሳደብኩ፡-
“ድዳም የድዳም ልጅ መሰረተ ድዳም
 ብትመጪ አልጠቀም ብትሄጂ አልጎዳም!”

Read 18546 times