Saturday, 17 January 2015 10:31

ለሰኔው አለማቀፍ ጉባኤ 10ሺ ተሳታፊዎች ይመጣሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመቶ ከሚቆጠሩ አገራት ከአስር ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በማስተናገድ በአዲስ አበባ ከተካሄዱ አለማቀፍ ጉባኤዎች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው 3ኛው “ፋይናንስ ለልማት” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሰኔ ወር ለማካሄድ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዋና አማካሪዎች እየተዘጋጁ ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ሚኒስትሮች፤ እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎችን ጨምሮ 10 ሺ ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ኮንፍረንሱ የእዳ ቅነሳና ስረዛ ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል፡፡ ከፍተኛ እዳ የተከማቸባቸው የአፍሪካና የሌሎች ድሃ አገሮች መንግስታት ባለፉት አስር አመታት የእዳ ስረዛ እንደተረገላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደገና እዳ ውስጥ እየገቡ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ በእዳ ብዛት ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት በርካታ ቢሆኑም፤ በኢትዮጵያ መንግስት ስር የሚገኙ ድርጅቶች በብድር የተከማቸባቸው እዳ በጥቂት አመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡
ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ (ወደ 300 ቢሊዮን ብር ገደማ) የውጭ እዳ፣ እንዲሁም የዚያን ያህል 300 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ የባንክ እዳ እንዳለባቸው ከመንግስት ተቋማት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሰኔ ወር የሚካሄደው አለማቀፍ ጉባኤ ለድሃ አገራት የእዳ ቅነሳና ስረዛ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የሚወያይ ቢሆን፤ ከዚሁ ጐን ለጐን የድሃ አገር መንግስታት ራሳቸውን የሚችሉበት ጉዳይም ይነሳል ተብሏል፡፡ ጉባኤው የአገር ውስጥና ፋይናንስ መፍጠሪያ ዘዴዎችን በማስፋፋት ላይ ትኩረትን ያደርጋል ብለዋል፡፡ የሀገር ውስጥ አለማቀፍ ፋይናንስን እንዴት ማንቀሳቀስ ይቻላል በሚለው ጥያቄ ላይም  ይመከራል ተብሏል፡፡  
ሚኒስትሩ ሐሙስ ጥር 7 ቀን ከአሜሪካ ከመጡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ከፍተኛ አማካሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ የሰኔው ጉባኤ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋቸውን ለመስጠት መምጣታቸውን ከኦባማ ዋና አማካሪዎች መካከል ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ጆን ፓዴስታ ተናግረዋል፡፡
 ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም በበኩላቸው፤ የኦባማ ዋና አማካሪዎች እዚህ መምጣታቸው ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፍያ አህመድ የሚመራ የበላይ ኮሚቴ የጉባኤውን ዝግጅት እያከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው አለማቀፍ የፋይናንስ ለልማት በ2002 ዓ.ም በሞንትሪያል ሁለተኛው አለማቀፍ “ፋይናንስ ለልማት” ደግሞ በ2008 ዓ.ም በዶሀ መካሄዱን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

Read 1334 times