Saturday, 17 January 2015 10:37

መኢአድና አንድነት የምርጫ ቦርድን የመጨረሻ ውሳኔ እንጠብቃለን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

•    ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አንችልም ብለዋል

ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈተው እንዲቀርቡ የመጨረሻ እድል የተሰጣቸው መኢአድና አንድነት፤ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያካሂዱና የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደሚጠብቁ ተናገሩ፡፡
የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቢሮን የያዙት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፤ ፓርቲያቸው ባለፈው እሁድ የምርጫ ቦርድን ፍላጐት ለማሟላት ሲል በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄዱን ጠቁመው፣ ቦርዱ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንድናካሂድ መጠየቁ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ ትክክለኛውን ውሳኔ መስጠት ይችላል ያሉት አቶ ማሙሸት፤ ይህ ካልሆነ ግን ቦርዱ መኢአድን ከምርጫ የማስወጣት ተልእኮ እንዳለው ልንገምት እንችላለን ብለዋል፡፡
ፓርቲያቸው በእሁዱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካዮች እንዲገኙለት ጥሪ ማስተላለፉን የጠቆሙት አቶ ማሙሸት፤ ቦርዱ ግን ተወካዮቹን ልኮ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ በራሱ ምክንያት ሳይታዘብ ቀርቷል ብለዋል፡፡ “በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የማይታሰብ ነው፤ ከዚህ በኋላ የቦርዱን የመጨረሻ ውሳኔ ነው የምንጠብቀው” ብለዋል፤ አቶ ማሙሸት፡፡
በቦርዱና በፓርቲው መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ መኢአድ እጩዎቹን ማስመዝገብና ደጋፊዎቹ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ መቀስቀስ አለመቻሉን፣ ይሄም በፓርቲው አጠቃላይ የምርጫ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ ማሳረፉን አቶ ማሙሸት ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፅ/ቤትን ይዘው የሚገኙትና ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት በተመረጡት በአቶ በላይ ፈቃዱ ካቢኔ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ባለፈው እሁድ ምርጫ ቦርድ በፈለገው መልኩ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለተኛ ጊዜ ማካሄዱን ጠቅሰው፣ ለሦስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠሩ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ ምርጫ ቦርድ፣ አንድነት የአመራር ምርጫውን ያደረገው የፓርቲውን ደንብና የምርጫ አዋጆችን መሰረት አድርጎ መሆኑን ከቀረበለት ሰነድ መርምሮ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደሚጠብቅ አስታውቋል፡፡ “እነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ አንድነትን የመወከል ህጋዊ መብት ስለሌላቸው ከነሱ ጋር ለድርድር መቀመጥ የማይታሰብ ነው” ብለዋል - አቶ ግርማ፡፡
ባለፈው እሁድ በዲአፍሪክ ሆቴል ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው፤ ምርጫ ቦርድ በሰጠው የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከእነ አቶ በላይ ቡድን ጋር ተነጋግሮ ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ የሚጠራበት ሁኔታ እንዲመቻች ለድርድር ለመቀመጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “በኛ በኩል በችግሮቹ ላይ ተወያይቶ ፓርቲውን ለማዳን ዝግጁ ነን” ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የእነ አቶ በላይ ቡድን የሚስማማ ከሆነ ጠቅላላ ጉባኤ በጋራ ተካሂዶ አዲስ ፕሬዚዳንት ይመረጣል ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም ያስቀመጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፤ በመኢአድም ሆነ በአንድነት በኩል አልተፈቱም ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሮ በማስረዳት፣ ችግራቸውን ፈተው እንዲቀርቡ ለሶስተኛ ጊዜ ዕድል መስጠቱን ያስታወቀ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት የተሰጠው ቀነ ገደብ ያበቃል፡፡

Read 1246 times