Saturday, 17 January 2015 11:00

‘ኒው ወርልድ ኦርደር’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ ያው እንግዲህ ‘ዕጣ ፈንታችንን የሚወስኑልን’ እንደመሰላቸው ሲያሽከረክሩን… አለ አይደል… መሽከርከር ነው፡፡ አሁን፣ አሁንማ እንትን ከተማ ሲያነጥሱ እንትን ከተማ የጉንፋን ወረረሽኝ የሚገባባት ዘመን ነው፡፡ ምን የማይደገስልን ነገር አለ፡፡
እናላችሁ…‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ የሚሏትን ነገር በብዙ ነገሮች ውስጥ ብልጭ ያደርጓታል፡፡ ነገርዬው… አለ አይደል… ‘የነበረው እንዳልነበረ’ አይነት ነው፡፡
ለምሳሌ ‘ቦተሊካ’ን ውሰዱት፡፡ (እንግዲህ አየሩ እንደዛ መሽተት ጀምሮ የለ!) እናላችሁ…ለስንትና ስንት ዓመት “ዓይንህ ለአፈር…” ሲባባሉ ይከርማሉ፡፡ እርስ በእርስ መወነጃጀል የ‘ቦተሊካ’ ‘ፍሬሽማን ኮርስ’ ነገር የሆነ ይመስል ….አሁንማ የእርግማን መአት መስማቱን እኛም ለመድነው፡፡ እኔ የምለው…ግርም አይላችሁም! ‘ቦለቲከኞቹ’ … አለ አይደል… “እኛ ከእናንተ የተሻለ ሀሳብ አለን…” ከመባባል ይልቅ… “እናንተ እኮ እንዲህ እንዲህ ለማድረግ ስውር ዓላማ ያላችሁ…” …ምናምን መባባል የሚያቆሙት መቼ ነው? አሰኝቷችሁ አያውቅም!
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…እኛን የእንትና ደጋፊ፣ የእንትና ተላላኪ ምናምን አስብለው የጎሪጥ መተያያት ከጀመርን በኋላ እነሱ በጎን ገጥመው ቁጭ! የእኔ ቢጤው ደግሞ ወዳጆቹን አጥቶ ቁጭ!
“እንዲህ ተጠማምደው ድንገት ፊት ለፊት ቢገናኙ ምን ይሆኑ ይሆን!…” ተብሎ የሚሰጋላቸው ሰዎች ምን ቢሆኑ ጥሩ ነው…..‘አዲስ’ ፍቅር ይጀምራሉ፡፡
ምን አለፋችሁ… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነገር ሆኖ ቁጭ!
ከዛማ ምን አለፋችሁ…ነገርዬው “አዲስ ፍቅር ይዞኛል…” ይሆንና እኛ “ጉርምርሜ…” ስንባል “ያሆ በሌ!” ስንል የከረምነው አጨብጭበን ቁጭ፡፡
እናማ… “እንዲህ ዞረው እንትን ለእንትን ለሚገጥሙት እኛን ለምን ያቆራርጡናል!” ብለን ለአንድዬ ‘እናሳጣቸዋለን’፡፡ ይህ ነገር ለእኛ ነው ጎበዝ ጠንቀቅ በል… ሲባባሉ “እነኚህ ሰዎች ‘ተላለቁ’…” ስንል እነሱ ግን ትከሻ ለትከሻ ገጥመው በብሉ ሌብል ምናምን ‘ይለቃለቃሉ’!
ነገርዬው… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነዋ!
እኔ የምለው ዞረው ሊገጥሙ የእርግማኑ፣ የዘለፋው መአት ምንድነው፡፡ (ሀሳብ አለን… አንዳንድ ወንበር ላይ ያላችሁ ሰዎች፣ እባካችሁ ቋንቋችሁን ኤዲት አድርጉልን፡፡ አሀ… ለነእንትና የታሰበው ‘ሞራል መስበሪያ’ እኛንም ጨረፍ ሊያደርግ ይቻላላ!)
ታላቁ መጽሐፍ… “ሳውል፣ መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?” ይላል፡፡ እናማ መመለሳችሁ ላይቀር እርስ በእርስ አትረጋገጡማ! ለእኛም አትትረፉን!! ቂ…ቂ….ቂ…
ደግሞላችሁ…እንትናዬን እንደ እንትና…አለ አይደል… ለዓይኗ የሚያስጠላት ነገር የለም፡፡ …እንደሚባለው “ዓለም ላይ የሚቀረው የመጨረሻ ወንድ ቢሆን እንኳን ዘወር ብዬ አላየውም…” ምናምን የምትል አይነት ነች፡፡ “አሁን ይሄንንም የምታገባ ሚስት ትኖር ይሆናል እኮ!” ምናምን እያለች ስታንቋሽሸው ትኖራለች፡፡
ድንገትላችሁ….ነገሩ ሁሉ ይገለበጥና በየት ይገናኙ በየት አንድዬ ይወቀው … ተጣብቀው ቁጭ! እሷ ባማችው ቁጥር እኮ እናንተ ስንትና ስንት ‘አሜንድመንት’ ጨምራችሁበታል!
እሱን ስታይ መንገድ እንዳልተሻገረች ሁሉ… አለ አይደል….አንድ ቀን ሳይደውል ካለፈ አገር ምድሩ ይደበላለቃል፡፡
ነገርዬው… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነዋ!
ይቺን ስሙኝማ… እሱዬው እናት አባቷ ሳያዩ በድብቅ በእሷ ፈቃደኝነት ጠልፏት ሊሄድ የቤተሰቡ ደንበኛ የሆነ ባለታክሲን ይጠራዋል፡፡ ሁለቱ መኪና ውስጥ እንደ ገቡም እሱዬው… “ከከተማ ለመውጣት ምን ያህል ታስከፍለናለህ?” ይለዋል፡፡
ባለታክሲውም “ግዴለም፣ ምንም አላስከፍላችሁም…” ይለዋል፡ እሱዬው ግራ ይገባውና “ሥራ አይደለም እንዴ! ለምንድነው የማታስከፍለን?” ይለዋል፡፡ ባለታክሲ ምን ቢል ጥሩ ነው... “አባቷ አስቀድመው ከፍለውኛል፡፡” አሪፍ አይደል! ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ይላችኋል እንዲህ ነው፡፡
የገዛ ልጁን ጠለፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስፖንሰር የሚያደርግ ስንትና ስንት አባት ይኖራል!
የአባትነት ሚና ‘ማሻሻያዎች’ ተደርገውበታላ!
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
እናላችሁ… “እንደው ባል እንኳን ባይመጣላት ለወጉ እንኳን ጠልፏት የሚሄድ ሰው ይጥፋ!”  የሚሉ ወላጆች ቢኖሩ አይገርምም፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የወላጅ ሚና እኮ ተገለባብጦ… አለ አይደል… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነገር ሆኗል፡፡
እናላችሁ… ለአስተማሪዎች “እባካችሁ ልጄ አጉል ነገር እንዳትለምድ፣ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር እንዳትውል ተከታተሉልኝ…” የሚሉ ወላጆች ‘ዝርያቸው’ ለመጥፋት ተቃርቧል፡፡
 ልክ ነዋ…“ልጄን ተቆጣህብኝ…! ብሎ እንትንዬውን ከጎኑ ‘ላጥ’ አድርጎ አስተማሪው ግንባር ላይ የሚደግን ‘አባት’ አለበት የሚባልበት አገር ነው እኮ! የአሥራ ምናምን ዓመት ልጇ ሲጋራ ስታጨስ በመያዟ የተጠራች ‘እናት’… “እኔ አስተምሩልኝ እንጂ ሲጋራ ታጭስ አታጭስ ተከታተሉልኝ አልኩ!”  ወይ… የምትልበት አገር ሆኗል ይባላል፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
እሷዬዋ እጮኛዋን ከቤተሰቦቿ ጋር ታስተዋውቀዋለች፡፡ አባቷ ስለ እሱ የበለጠ ለማወቅ ወደ አንድ ክፍል ይወስደዋል፡፡ የልጅቱ አባት የናጠጠ ሀብታም ነበር፡፡
“እሺ፣ እቅዶችህ ምንድናቸው?”
“የኃይማኖት ምሁር ነኝ፡፡”
“በጣም ጥሩ ነው፣” አለ አባትየው፡፡ “ግን ልጄ ጥሩ ቤት እንድታገኝ ምን ለማድረግ አስበሀል?”
“እኔ ጥናቴን እቀጥላለሁ፣ እግዚአብሔርም ሁሉንም ነገር ያደርግልናል፡፡”
“መልካም፣ የጋብቻ ቀለበትስ እንዴት እድርገህ ነው ልትገዛላት ያሰብከው?”
“እኔ ጥናቴን እቀጥላለሁ፣ እግዚአብሔርም ሁሉንም ነገር ያደርግልናል፡፡”
“ስለ ልጆችስ ምን ታስባለህ?” አለ አባትየው፡፡ “ልጆችህን በምን መልክ ለማሳደግ ነው ያሰብከው?”
“አያስቡ፣ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያደርግልናል፣” ሲል እጮኛ ሆዬ መለሰ፡፡
ውይይቱ በዚህ መልክ ቀጠለ፡፡ ሁለቱ እጮኛሞች ተሰናብተው ሲሄዱ እናትየው አባትየውን ስለ ልጃቸው እጮኛ ምን መረጃ እንዳገኘ ትጠይቀዋለች፡፡
አባትም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…ሥራም ሆነ ዕቅዶች የሉትም፡፡ ግን ጥሩው ነገር ምን መሰለሽ፣ እኔ እግዚአብሔር መስየዋለሁ፡፡”  ቂ…ቂ…ቂ…
ዘንድሮ በእንትናዬ ሰልካካ አፍንጫ ሳይሆን በአባቷ ካዝና እየተማረከ አባወራ የሚሆን መአት ነው፡፡ እናማ…የአባት አንጀት አይጨክንም በማለት… “እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ያደርግልናል…” የካዝናውን ስፋትና ርዝመት እያሰበ ነው፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
ስሙኝማ… የአባት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አባት ልጁ ስለ አልኮል መጠጥ መጥፎነት ሊያስረዳው እየሞከረ ነበር፡፡
እናማ…አንዲት ትል በንጹህ ውሀ ውስጥ፣ አንዲት ትል ደግሞ በውስኪ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ውሀ ውስጥ ያለችው ትል ምንም አትሆንም፡፡ ውስኪ ውስጥ የነበረችው ግን ተንፈራፍራ ሞተች፡፡
አባትዬውም ወደ ልጁ ዘወር አለና… “እሺ የእኔ ልጅ፣ አሁን ያየኸው ምንን ያሳያል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጅ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው….
“የሚያሳየውማ አልኮል ከጠጣህ ትላትሎቹ በሙሉ እንደሚሞቱ ነው፣” አለና አረፈው፡፡
‘የዘንድሮ ልጆች’ ከመቼው ነገር እንደሚይዙ የሚገርም ነው፡ እናማ…እንደ ድሮው በሎሊፖፕና በደስታ ከረሜላ የሚታለል ልጅ ያለበት ዘመን እያለፈ መሆኑን ልብ ማለት ነው፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
ብቻ…ለበጎም ይሁን ለክፉ… ብዙ ነገሮች እየተለዋወጡ መሆኑን ማወቅ ደግ ነው፡፡ የዚሀ አገር አንድ ትልቅ ችግር የሚመስለኝ ዘመን፣ ከዘመን ጋርም የሰዉ አመለካከትና አስተሳሰብ እየተለወጠ መሆኑን ነገሬ አለማለታችን፣ ወይም ‘ነገሬ ለማለት’ ፈቃደኛ አለመሆናችን ይመስለኛል፡
ለደግ፣ ለደጉ… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ያምጣልን!
መልካም የጥምቀት በዓል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2978 times