Saturday, 14 January 2012 10:27

ኢቴቪ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ለባለሀብት ቢሸጥስ? ለህዝብ ጥቅም ስል ኢህአዴግ ልሆን ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

አንዳንድ ኢህአዴግ የማይመቻቸው ወገኖች (ከተቃዋሚም ጐራ ያልሆኑ) ገዢው ፓርቲ ቂመኛ ነው ብለው ሲያሙት እሰማለሁ፡፡ (ነው ግን?) ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በአፉ እንጂ በልቡ አያከብርም ሲሉትም ይደመጣል፡፡ (እራሱ መልስ ይስጥበት) ተቃዋሚ ፓርቲዎችማ ምን የማይሉት አለ - ኢህአዴግን፡፡ የሥልጣን ጥመኛ… የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌለው… (ሶማሊያ ገብቶ ወኔውን እያሳየ!)… መንበረ ሥልጣኑን ከእኔ ውጭ ማንም አይነካትም ብሎ የተፈጠመ (ምን ያድርግ?) ራሱ አርቅቆ ያፀደቀውን ህገ መንግስት የሚጥስ… (ለህዝብ ጥቅም ሲል ነዋ!)… በትልቁም በትንሹም አድንቁኝ ባይ… (እቺ እንኳን የሁሉም ሃበሻ አመል ናት)… ከአገር ጥቅም ይልቅ የፓርቲ ጥቅም የሚያስቀድም (ከኢህአዴግና ከጦቢያ ምረጥ መች አልነው?)… ባስ ሲልም አምባገነን ፓርቲ ወዘተ ወዘተ… እየተባለ ተወግዟል… ተኮንኗል (ያለስሙ ስም ተሰጠው እንዳልል በቂ ጥናት አላካሄድኩም) እነዚህን ሁሉ በመረጃ ላይ እንደተመሰረቱ “ሃሜቶች” ቁጠሩልኝና ወደ ቀጣዩ አጀንዳ እንለፍ፡፡

እንግዲህ በፖለቲካ ወጋችን… አቶ በረከት ስምኦን በ”ምርጫ ዘ ትዝታ 97” (ርዕስ የእኔ) መፅሃፋቸው “የዜሮ ድምር ውጤት” እንዳሉት አይነት ነገር እንዳይከሰት ለዚህ አምድ ስንል ሃቅ ሃቋን ብቻ እናወጋለን፡፡ እርምጃችንም በጥንቃቄ የተሰላ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ሁሌ አይሳካምና በመረጃ እጦት የተነሳ ከሃቅ የምንፋታበት አጋጣሚ አይጠፋም፡፡ ያኔ ወጋችን አሉባልታ ይሆናል፡፡ አሉባልታ ነው ብለን ግን ከማውጋት መታቀብ የለብንም፤ እሱኑ በሃቅ መከወን ነው - አሉባልታውን ማለቴ ነው፡፡ በቅርቡ ምን ተገነዘብኩ መሰላችሁ? ሃሜትና አሉባልታ የሌለበት ፖለቲካ በዓለማችን ታሪክ እንደሌለ፡፡ ቢኖርም እንደዚያኛው አይጥምም አይደምቅም፡፡ ይሄን ለማረጋገጥ ጥናትና ምርምር ማድረግ አያስፈልጋችሁም፡፡ የኢህአዴጋውያኑን ፓርላማ ዝም ብላችሁ ተመልከቱት፡፡ ዝም ዝም አላለባችሁም? “ኑሮና ፖለቲካ” በሚል በቅርቡ የወጣው የበሃይሉ የወግ መፅሃፍ ላይ ያነበብኩትን ለፈገግታ ያህል ላጋራችሁ፡፡

በየሰፈሩ ባሉ ቪዲዮ ማሳያ ቤቶች ፊልም የሚያዩ ታዳጊዎች የሚመለከቱት ፊልም ሳይስባቸው ወይም ሳይማርካቸው ሲቀር ምን ይላሉ መሰላችሁ? (መፅሃፉ እንደሚለው) “ፓርላማውን ለውጠው!” በምን ይለወጣል ልትሉ ትችላላችሁ… ሞቅ ሞቅ ባሉ የአክሽንና ሰስፔንስ ፊልሞች ነዋ!! አያችሁ ፓርላማው ተቃዋሚ ከሌለው ይፈዛል - “ፖለቲካ” አይኖረውም፡፡ ፖለቲካ የሌለበት ፓርላማ ደሞ ይታያችሁ! እኔ የምለው… ለምንድነው የፓርላማ ጭብጨባ የቀነሰው? ተቃዋሚዎች ከነበሩበት ጊዜ እኮ በ88.4 በመቶ መቀነስ አሳይቷል (መረጃው የተገኘው ከሁነኛ ምንጭ ነው) እኔማ የኢህአዴግ አባላት ሲያጨበጭቡ የነበረው ለተቃዋሚዎች ነበር ወይ አልኩኝ - ለፓርላማ ሳይሆን ለራሴ፡፡

ሳልዘነጋው በፊት አንድ መረጃ ባደርሳችሁ ደስ ይለኛል፡፡ የሆነ ቀን ሲመቸኝ “የፖለቲካ ገበናችን” የሚል ዶክመንታሪ ፊልም የመስራት ሃሳብ አለኝ፡፡ የሆነ ቀን ያልኩት በገንዘብ የሚደግፈኝ ባለሃብት እስካገኝ ብዬ ነው (ኢህአዴግ ሁሉንም ባለሀብት ወሰደብን እኮ!) በነገራችን ላይ የፊልሙን ርእስ መኮረጅ በኮፒራይት ህግ እንደሚያስቀጣ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ፡፡ (አንድ የፊልም ሲዲ ላይ “አላርፍ ያለች ጣት 100ሺ ብርና የ10 ዓመት እስር ታስቀጣለች” የሚል ማስጠንቀቂያ የሰማሁ መሰለኝ - ህገወጥ ሲዲ ለገዛ መሆኑ ነው) እና… የምሰራው ዶክመንተሪ ምን አይነት መሰላችሁ? ከፍተኛ ተወዳጅነትና ግብረ - ምላሽ (feed back) አግኝቷል እንደተባለው የኢቴቪ “አኬልዳማ” አይነት ፊልም ነው፡፡ ኢቴቪ ቢዝነስ አያውቅም እንጂ “አኬልዳማ”ን በየሲኒማ ቤቶቹ እያስከፈለ ማሳየት ይችል ነበር፡፡ ገቢው ደግሞ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ይውል ነበር (ራሱን በራሱ መደገፍ ማለት ይሄው አይደል!)

እኔ የምለው… ይሄ “አኬልዳማ” የተባለ ኢ-ልቦለድ ፊልም የውዝግብ ማባባሽያ ሆነ አይደለም እንዴ? (ይቅርታ አነጋጋሪ ሆነ ለማለት ፈልጌ ነው) እናም በፓርላማ ጉባኤ የኢህአዴግ ሃላፊዎች “አኬልዳማ”ን ደግፈው ሲከራከሩ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካዩ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ ፊልሙን ተቃውመው እንደተሟገቱ ሰምተናል፡፡ አይተናል፡፡ ውጤቱስ እንዳትሉኝና ዓይኔ እንዳይፈጥ ብቻ! አያችሁ የፖለቲካ ክርክር ዋናው ፋይዳው ውጤቱ ሳይሆን ሂደቱ ነው፡፡ ስለዚህ በክርክሩ ያሸነፈም የተሸነፈም የለም እላችኋለሁ፡፡ ግን የኢህአዴግ ሃላፊዎች “አኬልዳማ” የተሰራው ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንደሆነ አስረግጠው መናገራቸውን ያዙልኝ፡፡ (ለነገሩ ኢህአዴግ ህዝባዊ ፓርቲ እኮ ነው!) እንግዲህ ተቃዋሚዎች ፊልሙን የጠመዱት ተጠርጣሪዎች በፍርድ ሂደት ላይ ሳሉ “አሸባሪ” ተብለው ተፈረጁ ብለው ነው፡፡ ይሄ ደሞ ህገመንግስታዊ መብት ይጥሳል ባይ ናቸው፡፡ በእርግጥ ነጥብ አላቸው፡፡ (ለኔ!)

የኢህአዴግ ሃላፊዎች ግን ይሄን ነጥብ በአጭር መልስ አፍርሰውታል - “ለህዝብ ጥቅም ሲባል ነው!” በሚል፡፡ ከዚህ በኋላ ወዴት ትሄዳላችሁ? እኔ በበኩሌ አጀንዳዬን ለወጥኩ፡፡ እናም ለኢህአዴግ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ልሰንዝር፡፡ ተቃዋሚዎችን “ብርቅዬ” (endemic) ለማድረግ አስቧል እንዴ? ምን ላድርግ… በፓርላማ ያሉት አንድ ብርቅዬ የተቃዋሚ ተወካይ ብቻ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ተንገላታን እያሉ ነው - ተቃዋሚዎቹ፡፡ ኢህአዴግን አንድ አደራ የምለው ነገር አለ - ተቃዋሚዎችን “ብርቅዬ” እንዳያደርግብን!! ከጠፉ በኋላ ፍለጋው ብዙ መስዋእትነት፣ ብዙ የአገር ሃብት፣ ብዙ ዘመን… ይፈጅብናል፡፡ (ሰዶ ማሳደድ የምትለዋን አባባል ኢህአዴግ አያውቃትም እንዴ?)

እኔ የምለው ኢቴቪ ባለፈው ዓመት ከቴሌቪዥን ተጠቃሚዎች ማግኘት ከሚገባኝ ወይም ካቀድኩት ጋር ሲነፃፀር 26 በመቶ ያህል ብቻ ገቢ ነው የሰበሰብኩት ማለቱን ሰምታችኋል? (ሲበዛበት ነው አልወጣኝም) ለዚህም የቴሌቪዥን ተጠቃሚው ህዝብ ለመክፈል ያለው ዝግጁነትና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ እንደ ምክንያት የቀረበ ሲሆን የቲቪ ዓመታዊ ክፍያ (60 ብር) በቀን ሲሰላ 15 ሳንቲም ብቻ እንደሆነ የኢህአዴግ ሃላፊዎች ለፓርላማ ተናግረዋል፡፡ እነኬንያ ለቴሌቪዥን ፈቃድ ብዙ ዶላር ያስከፍላሉም ተብሏል፡፡ (ግን ፕሮግራማቸውስ እንዴት ነው?)

ለነገሩ ኢቴቪ ሥር ነቀል ለውጥ ካላመጣ ገቢው ወደ 10 በመቶም ሊወርድ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ለፍ/ቤት ማስረጃ የሚሆን ፊልም እያሳየን… እንዴት ገቢው አይቀንስም? ለዚህ እኮ ነው ህዝቡ 30 እና 40 ብር ከፍሎ ሲኒማ ቤት እየገባ አክሽን፣ ሮማንቲክ ኮሜዲ፣ ሮማንስ ወዘተ የአማርኛ ፊልሞችን የሚኮመኩመው፡፡ እኔ እንደውም የኢቴቪ ደንበኞች ጨዋ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ የሌላ አገር ህዝብ ቢሆን እኮ ኢቴቪን ፍ/ቤት ይገትረው ነበር - “የመረጃ ማሰራጫ ጣቢያውን የፕሮፓጋንዳና የጥላቻ ማሰራጫ ጣቢያ አደረገው” በሚል፡፡ (በዚያ ላይ የህዝብ ንብረት ነው ይባል የለ!)ልብ አድርጉ! እኔ የኢቴቪ ደንበኞች ፍ/ቤት ይክሰሱት አልወጣኝም፡፡ እቺን ሰበብ አድርጐ “ደንበኞቼን በማነሳሳት” ብሎ ኢቴቪ እኔኑ ቢከሰኝስ? ከሽብርተኝነት ጋር እንደምንም ሊያጠጋጋውም ይችላል… በኋላ የማን አለህ ይባላል፡፡ እኔም እቺን አውቄ አዲስ ፕሮፖዛል ለመንግስት አርቅቄአለሁ፡፡ ማነህና ነው ለመንግሥት ፕሮፖዛል የምታረቀው ለሚሉኝ “አክራሪ ኢህአዴጐች” አጭር መልስ አለኝ - እኔ ህዝብ ነኝ፤ ፕሮፖዛሉም የሚረቀቀው ለህዝብ ጥቅም ሲባል ነው፡፡ ወንድ ከሆነ ኢቴቪ በዚህ ይክሰሰኝ - ገና ክሱ ሲጀመር እረትቼው ቁጭ ነው! (ኢህአዴግ ህዝባዊ ፓርቲ ነዋ!) በነገራችን ላይ መንግስት በእጁ ላይ የነበረውን የመጨረሻ የቢራ ፋብሪካ (ሜታ ማለት ነው) ለታዋቂው የእንግሊዝ የአልኮል መጠጥ ኩባንያ በመሸጥ ከቢራ ንግድ ሙሉ በሙሉ ራሱን እንዳወጣ ሰምቼ ሙሉ ሌሊቱን ቢራ ስጠጣ አደርኩላችሁ ብላችሁ ምን ትላላችሁ? እንዴ አሁን እኮ ወደ ትክክለኛው የመንግስት ሚናነቱ እየመጣ ነው - (የ”ዘበኝነት” ሚና አልወጣኝም) ህዝብ የማስተዳደር ሚና ለማለት እንጂ! ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ሰሞኑን አክሰስ የተባለው የጥናትና ምርምር ተቋም ባወጣው ሪፖርት፤ እስከ 40 በመቶ በማሻቀብ በዓለም የሁለተኛነት ደረጃን የተቆጣጠረው የአገራችን የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ መንግስት በቁጥጥሩ ሥር ያሉትን የልማት ተቋማት ወደ ግል ንብረትነት ማዛወር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ ተቋማቱ እነማን መሰሏችሁ? ኢትዮ ቴሌኮም (የምትታለብ ላም ወይም የገንዘብ ማተምያ ማሽን ተብሎ የነበረው ማለቴ ነው) አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትና ባንክ ናቸው፡፡ አክሰስ ከእኔ ይውጣልኝ ብሎ ነው እንጂ መንግስት በተለይ ባንክንና ቴሌኮምን እንደ ቢራ ፋብሪካዎቹ በቀላሉ ይሸጣቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ (ምናልባት አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ካሰለፈ በኋላ ይሸጠው ይሆናል!)ችግሩ ደግሞ መንግሥት/ኢህአዴግ አሁን አገር በቀሉ የምርምር ተቋም አክሰስ ያቀረበውን ምክር ተቀብሎ የልማት ተቋማቱን ፕራይቬታይዝ ቢያደርግ ሌላ ተመሳሳይ ጥያቄ ደሞ ይከተላል፡፡ እነ ዓለም ባንክና IMF ዝም ብለው የሚቀመጡ ይመስላችኋል? ኢህአዴግ ፊት ከሰጣቸው ስልጣንህንም ለባለሀብት ሽጠው (privatize አድርገው) ይሉታል፡፡ ለነገሩ እንኳን እነሱ እኔም ራሴ ዝም አልልም፡፡ ኢቴቪን በተመለከተ ያረቀቅሁት ፕሮፖዛል ተረሳ እኮ! ደግነቱ ፕሮፖዛሉ አጭር ነው - ኢቴቪ እንደነ ሜታ ቢራ ለባለሃብት ይሸጥ የሚል ነው፡፡መቼም ኢህአዴግ ሰው የሚለውን በመስማት አይታማም አይደል? ድንገት ከሰማና አስፈላጊ መስሎ ከታየው ደግሞ ያረሳሳና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተግባራዊ ያደርገዋል እንጂ  ቢሞት ወዲያው አይፈፅመውም፡፡ ለአንዳንዶች ይሄ እንደ ድክመት ቢታያቸውም ለእኔ ግን አሪፍ ስትራቴጂ ናት፡፡ ኢህአዴግ (ማለቴ መንግሥት) ድንገት ተሳስቶ እንኳ ኢቴቪን ፕራይቬታይዝ ካደረገ ግን ትልቅ ሰርፕራይዝ አለኝ - ለህዝብ ሳይሆን ለራሱ ለኢህአዴግ፡፡ ግዴለም ብዙ ሳላጓጓ አሁኑኑ ልንገራችሁ - ኢቴቪ የተሸጠ እለት እኔ የኢህአዴግ የአባልነት ካርዴን እወስዳለሁ! በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ አባላትንና ደጋፊዎችን ቁጥር በአንድ ከፍ አደርጋለሁ (እጨምራለሁ) ማለት ነው፡፡ 7 ሚሊዮን ደጋፊዎች ካሉት እኔ ስጨመር ከ7 ሚ. በላይ እያለ መናገር ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እኔ አባል ስለምሆንለት ብቻ ኢቴቪን እንዳይሸጠው፡፡ ኢቴቪን መሸጥ ያለበት ለህዝብ ጥቅም ብሎ ነው!! ከዚያ እኔም ለህዝብ ጥቅም ብዬ ኢህአዴግ እሆናለሁ! በፖለቲካውም በኑሮውም የጥጋብ ዘመን እመኛለሁ!! (ለህዝብ ጥቅም ስል)

 

 

Read 2381 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:30