Saturday, 17 January 2015 11:16

ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል! ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል

Written by 
Rate this item
(19 votes)

   ከእለታት አንድ ቀን ከባድ የበረዶ ዘመን መጣና እፅዋትና እንስሳትን በቅዝቃዜ ጨረሰ፡፡ በየእለቱ ሞቶ የሚያድረው ነብስ እጅግ እየረከተ መጣ፡፡ ይሄኔ የባህር አሳዎች መመካከር ጀመሩ፡፡ ከነዚህ አሳዎች መካከልም በጣም እሾካማ የሆኑ አሳዎች አሉ፡፡
አንደኛው አሳ፤ ለሌኛው አሳ፡-
“እስከመቼ ድረስ ዝም ብለን ተቀምጠን በበረዶ ቅዝቃዜ እናልቃለን? ለምን ቢያንስ ተጠጋግተን፣ ተቃቅፈን አንተኛም?” ይለዋል፡፡
ሁለተኛው አሳም፤
“ተቃቅፈንና ተጠጋግተን መተኛቱ ለምን ይጠቅመናል?” ሲል ይጠይቀዋል?
አንደኛው አሳ፤
“በበረዶ ባህር ውስጥ ተራርቀንና ተለያይተን ከሚቀዘቅዘን ተጠጋግተን ብናድር አንዳችን ለአንዳችን ሙቀት እንሰጣለን፡፡ ስለዚህም እርስ በርስ እንክብካቤ የመደራረግ እድል እንፈጥራለን” አለው፡፡ በዚህ ሃሳብ ተስማሙ፡፡ አጠገብ ላጠገብ ሆነው ተኙ፡፡ ሆኖም አንድ ችግር ገጠማቸው፡፡
ሲጠጋጉ ሁሉም እሾሃማ ቆዳ ስለሆነ ያላቸው ያንዱ ቆዳ የሌላኛውን እየወጋው፣ እንደቆንጥር እየጠቀጠቀው ፈፅሞ ለመተኛት አዳገታቸው፡፡ ቢለያዩ ቅዝቃዜው ሊገላቸው ሆነ፡፡ ቢቀራረቡ እሾክ ለሾክ ሆኑና ሊወጋጉ ሆነ፡፡ ምርጫቸው ከሁለቱ አንዱን ማድረግ ሆነ፡- ወይ ተለያይቶ በበረዶው ቅዝቃዜ ማለቅ፤ ወይም ደግሞ እንደምንም እሾክ ለእሾክ ተቻችሎ የጐድን ውጋቱን ችሎ ማደር፡፡
በሁለተኛው ምርጫ ተስማሙ፡፡ ብዙ ሳይገላበጡ፣ ሙቀት እየተለዋወጡ ክፉውን የበረዶ ጊዜ ማለፍ! ጐረቤት ለጐረቤቱ የጐን ውጋት እንዳይሆን መጠንቀቅ፡፡ ውጋቱ ቢኖርም ቁስል ቢፈጠርም ታግሶ፣ ችሎ ማደርን መልመድ! በዚህ ዘዴ ህያው ሙቀት እየተሰጣጡ ያንን ዘመን ተሻገሩ፤ ይባላል!
ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል!
ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል
በሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ያንዱን ችግር ችሎ፣ አንዱ ያንዱን ቁስል አክሞ መከራን በትእግስት አልፎ፣ ቢቻልም እሾኩን ነቅሎ፤ ህያው ሙቀት ፈጥሮ አገር ማዳን ባለመቻሉ፤ ብዙ እድልና አጋጣሚ አምልጧል፡፡ ጥቃቅን ችግሮችን በወቅቱ ለማለፍ ባለመቻሉ የመፈረካከስ፣ የመሰነጣጠቅ ከናካቴውም የመበታተን አደጋ ደርቷል፡፡ የእኔ ትልቅ ነኝ …እኔ ትልቅ ነኝ ፍትጊያ ለብዙ መከራ ዳርጓል፡፡ የእኔ ልዋጥ እኔ ልዋጥ ሽኩቻ (Big Fish - Small Fish Theory እንዲሉ ፈረንጆች) ለብዙ አበሳ አጋልጧል፡፡ አገርና ህዝብን ማስቀደምና የጋራ ቤት የሚሰራበትን ወቅት ለየግል ፍልሚያ በመጠቀም አያሌ የአዝመራ ጊዜዎች ባክነዋል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ከትላንት የእርስ በርስ አለመግባባት፣ ከትላንት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትርምስ ማን ተጠቀመ? የሚለውን ነው፡፡ ዛሬም ከትላንት ለመማር አልረፈደም፡፡ አንድን ወቅት የዓለም ፍፃሜ አድርጐ መፈረጅ ወደ ተስፋ-መቁረጥ ነው የሚያመራው፡፡ ይልቁንም ሁሉን ነገር በትላንት በዛሬና በነገ ሰንሰለት ላይ እንዳለ ክስተት እያዩ፣ በትእግስትና በፅናት መጓዝን ለማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ አገር “በእድገት ላይ ነን ተብሎ ሊፃፍባት አይችልም፡፡ ወይም እንደ ንግድ በአዲስ መልስ ሥራ ጀምረናል” አይባልባትም፡፡ ዲሞክራሲ የተከለከለች የበለስ ፍሬ የማትሆነው ሁሉን ነገር እንደ ሂደት እያያያዝን ካየን ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ዲሞክራሲ እንዳለመኖሩ፤ በተናፅሮ የምናገኘውን ዲሞክራሲ ለመጨበጥም ብዙ ድካም ይጠይቃል - በድሮው ቋንቋ ያለመስዋዕትነት ድል የለም - እንደ ማለት ነው፡፡ ከማማረር መማር ነው ነገሩ!” ጥርስ ነጭ ይሁን አይሁን፤ ግን ይጠንክር” ይላሉ አበው፡፡ አንድም፤ “በካፊያው ምን አስሮጣችሁና ገና ዝናቡ አለ አይደለም ወይ” የሚለውን ልብ ብሎ ማሰብ ነው፡፡
ዲሞክራሲን፤ ፍትሐዊነትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ እውነተኛ ምርጫን፣ እኩልነትትን፣ ዲፕሎማሲን፣ ለማግኘት አያሌ አመታትን አሳልፈናል፡፡ እንደ አፍ እንደማይቀልም፣ አውቀናል፡፡ ተገንዝበናል፡፡ አንድም የራሳችንን የሽኩቻ ባህላዊ አሽክላ በቀላሉ ለመላቀቅ ባለመቻል፤ አንድም ደሞ ከውጪ የሚመጣብንን ጫና ለመመከት ባለመታደል፣ ጠንክረን ዳር የመድረስ ነገር የህልም ሩጫ ሲሆንብን ከርሟል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “እውነት በጣም እፁብ በመሆኗ በውሸት የክብር ዘቦች መጠበቅ ይኖርባታል” ያለውን እንኳ ለመፈፀም መቻቻል አልሆነልንም፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ያላግባብ የመበልፀግን አባዜ አስቀድሞ ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ወዲህ እየለፈፉ ወዲህ እየዘረፉ አይሆንም፡፡ ከልብ የማናደርገውን ነገር በአዋጅ ብንናገረው ግማሽ-ጐፈሬ ግማሽ-ልጭት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ሕግ ለሁሉም እኩል የሚሰራባት አገር ታስፈልገናለች! “ድካማችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ” የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ሟርት የማይበዛባት አገር ታስፈልገናለች! በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ አገር ይለወጣል ከሚል አስተሳሰብ የፀዳች አገር ታስፈልገናለች! ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ሲጮህ የማናይባት አገር ታስፈልገናለች! ራሱ ሰርቆ አፋልጉኝ ይላል እንደተባለው አይን-አውጣ፣ ሌባ እያየን ዝም የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ባንድ በኩል የራሳችንን ድምፅ ብቻ መልሰን ለማዳመጥ ዝግጁ ከሆን፣ በሌላ በኩል እኔ ያልኩትን ብቻ አዳምጡ ካልን፤ የትላንትናን ዜማ ብቻ የምንደግም ከሆነ፤ “ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል”፤ “ቀጥቃጭ ሲያረጅም ዱልዱም ይቀጠቅጣል” የሚሉትን ተረቶች ስናሰላስል መክረማችን ነው!

Read 6019 times