Saturday, 24 January 2015 11:52

በጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ንብረት የወደመባቸው ድርጅቶች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቀረቡ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

    በጣይቱ ሆቴል ላይ በደረሰው የቃጠሎ አደጋ ንብረታቸው የወደመባቸው አስራ አንድ ድርጅቶች ቃጠሎው ወቅት በታሪካዊው ሆቴልና በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ላደረገው ርብርብና በተለያዩ አካላት ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቀረቡ፡፡ የድርጅቱ ተወካዮች ከትናት በስቲያ በሆቴሉ ግቢ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በቃጠሎ አደጋው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶችና ጥሬ ገንዘብ እንዲሁም ምትክ ሊገኝላቸውና በገንዘብ ሊገዙ የማይችሉ መረጃዎች ወድመውባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በቃጠሎው ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ የወደመና አንዳችም ንብረት ለማዳን ያልቻሉ ቢሆንም በቃጠሎው ወቅት የአካባቢው ህብረተሰብ፣ በሆቴሉ ውስጥ የነበሩ እንግዶችና የውጪ አገር ዜጎች፣ የፖሊስ አባላትና የጣይቱ ሆቴል አስተዳደር ላደረገላቸው ድጋፍና እሳቱን ለማጥፋት ላሳዩት ከፍተኛ ርብርብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በአደጋው ንብረታቸው የወደመው የአስራ አንድ ድርጅቶች ተወካዮች፣ “የሴሌብሪቲ ኢትዮጵያ ቱር” ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ካሣና የ“አዲስ ተስፋ ኢንተርቴይንመንት” ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተስፋ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ አደጋው ሙሉ ንብረታቸውን ያወደመና ምትክ ሊያገኙላቸው የማይችሉ መረጃዎችን ያጠፋባቸው እጅግ አስከፊ አደጋ ነው ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ፣ የሆቴሉ እንግዶችና ፖሊስ በጋራ አደጋው ከዚህም የከፋ ጉዳት ሳያደርስና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የተቻለው በእነዚህ ወገኖች ትብብር በመሆኑ ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል፡፡ በቃጠሎው ወቅት በሆቴሉ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች የሆኑ ቱሪስቶች ለእሳት አደጋ ሰራተኞች ሙያዊ እገዛ በማድረግና እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ከሚያደርጉት የአካባቢው ወጣቶችና የእሳት አደጋ ሰራተኞች ጋር በመተባበር ላደረጉት እገዛና ድጋፍ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የጣይቱ ሆቴል አስተዳደር በቃጠሎው አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው አስራ አንዱ ድርጅቶች የሆቴሉን የመኝታ ክፍሎች በማስለቀቅ በጊዜያዊ ቢሮነት እንድንገለገልበት ስለፈቀደልን ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ያሉት የድርጅቶቹ ተወካዮች፤ በቃጠሎው ሳቢያ በደረሰው ጉዳት ህብረተሰቡ እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተዛዘን ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ያረጋገጠበት አጋጣሚ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም የደረሰውን የቃጠሎ አደጋ ወደ ህዝቡ እንዲደርስ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባልም ብለዋል፡፡ በአደጋው ሙሉ በሙሉ የወደሙ ድርጅቶችን የማቋቋም ፕሮግራም በቀጣይነት የሚሰሩ መሆናቸውንም በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡

Read 1464 times